Monday, October 7, 2013

ሰባ አምስት ሺህ ዶላር ለሚያሸልመው ውድድር ኢትዮጰያውያን ወጣቶች ተጋብዘዋል (reporter)

ሰባ አምስት ሺህ ዶላር ለሚያሸልመው ውድድር ኢትዮጰያውያን ወጣቶች ተጋብዘዋል


ከ15 እስከ 22 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን ሥራ ፈጣሪዎች በአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ለውጥን ማምጣት የሚያሥችሉ ፈጠራዎችን እንዲያከናውኑ እየተደረገ ነው፡፡
በመሆኑም ዋና ጽሕፈት ቤቱን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው አፍሪካ ሊደርሺፕ አካዳሚ፣ ሥራ የመፍጠር ብቃት ያላቸውን አፍሪካውያን ወጣቶችን እያበረታታና እየደገፈ ይገኛል፡፡ አካዳሚው ‹‹ዘ አንዚሻ ፕራይዝ›› በተሰኘው ማበረታቻና ድጋፍ መስጫ ሽልማቱ አማካይነት ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ አሸናፊ ወጣቶችን መሸለም ከጀመረ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡   
በዘንድሮው ውድድርም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትሳተፍ በውድድሩ አዘጋጅ በአፍሪካ ሊደርሺፕ አካዳሚ ተጋብዛለች፡፡ በዚህም መሰረት ከ32,000 በላይ አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አባላቱን በማስተባበር ውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ የማኅበሩ አባል ያልሆኑ ወጣቶችም (ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 22 የሆኑ) በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማኅበሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ 
ማኅበሩ ወጣቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር፣ በእንዲህ ዓይነት ዕድሎች ወጣቶች እንዲሳተፉ የተለያዩ ነገሮችን ያመቻቻል፡፡ የሚፈጠረው የውድድር መንፈስ፣ አባላቱን፣ ሌሎች ወጣቶችን ለበለጠ ውጤት የሚያነቃቃና የሚያሸጋግር እንደሚሆን ይታመናል፡፡  
በዚህ ውድድር ላይ መካፈል የሚፈልጉ ወጣቶች እስከ ህዳር 2006 ዓ.ም. ድረስ መመዝገብ ይችላሉ፡፡ በውድድሩ ምርጥ 12 ውስጥ መግባት የቻሉ ወጣቶች ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ለፈጠራ ሥራቸው አጋዥ የሆኑ ሙያዊ ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ የውድድሩ አላማ ሽልማት መስጠት ብቻ ሳይሆን በየዓመቱ ከተፎካካሪ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች መካከል የተሻሉ የፈጠራ ሥራ ናቸው የተባሉትን በተለያየ መንገድ እንዲደገፉ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲሆን አንዱ ሁኔታ ከድርጅቶች ወይም ከባለሃብቶች ጋር በመገናኘት፣ የወጣቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ገበያ ወጥተው ወጣቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ 
በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ የሚሆኑ ከአንድ እስከ ሦስት የሚወጡት የፈጠራ ባለቤት ወጣቶች ከገንዘብ ሽልማቱ ከፍ ያለውን ድርሻ እንደየደረጃው (25000፣ 15000 እና 12000 ዶላር) ይሸለሙና የተቀሩት ዘጠኙ ደግሞ የቀረው ገንዘብ ይሰጣቸዋል፡፡ ለውድድሩ የሚቀርቡት የፈጠራ ሥራዎቹ ውጤት በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ ለውጥ ታስቦ፣  ፈጠራው ፍጹም አዲስ ሐሳብ መሆኑንና በሌሎች አገሮች ለተመሳሳይ ችግርም አማራጭ መፍትሔ መሆን እንደሚችል ሲታመንበት አሸናፊ ተርታ ውስጥ ይካተታል፡፡ ለውድድር ብቁ የሚሆኑ ዘርፎችም ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ አካባቢ ጤና ጥበቃ፣ ኢነርጂና ውኃ ተብለው ተከፋፍለዋል፡፡ 
ይህ ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው አፍሪካ ያሉ ወጣቶችን የሚያበረታታና በወጣቶች ዘንድ ሥራ ፈጠራ እንዲበረታታ የሚያስችል ነው፡፡
በመጠናቀቅ ላይ ባለው 2013 በተካሔደው በአንዚሽ ፕራይዝ ውድድር ከ32 አገሮች የተውጣጡ ዕድሜያቸው ከ 23 በታች የሆኑ 400 ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚያም ውስጥ ከ10 አገሮች የተውጣጡ 12 ምርጥ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የተዘጋጀላቸውን የገንዘብ ሽልማት ወስደው፣ ፈጠራቸውን ማዳበር የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ለመውሰድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናሉ፡፡  
የ2013ቱ ውድድር አሸናፊዎች የዩጋንዳና የታንዛኒያ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ዘርፎች የፈጠራ ሥራ አለን የሚሉ ወጣቶች WWW.anzishaprize.org ላይ ቢገቡ ሁሉንም መረጃዎች ማግኘት ይችላሉ፣ ምዝገባውንም በዚያው ማካሄድ ይችላሉ፡፡
ወጣት አፍሪካውያን ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ተብሎ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው አፍሪካን ሊደርሺፕ አካዳሚ አማካይነት የተጀመረው የዚህ ዓመታዊ የንግድ ሥራ ፈጠራ ውድድር የተሰጠው ‘ዘ አንዚሻ ፕራይዝ’ መጠሪያ በኪስዋህሊ ቋንቋ ‹‹አዲስ ሐሳብ አፍላቂነት›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 የተመሰረተውና ዋና ጽ/ቤቱን ካናዳ ቶሮንቶ ያደረገው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለዚህ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 

No comments:

Post a Comment