Saturday, October 12, 2013

የአገሪቱ ብቸኛ የአስከሬን ምርመራ ክፍል ሥራውን አቋረጠ

Written by  ሰላም ገረመው
ብቸኛዋ ኩባዊት ባለሙያ የስራ ውላቸውን ጨርሰዋል
ሆስፒታሉ አስከሬን አልቀበልም ብሎ ማስታወቂያ ለጥፏል
በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ስር በሚገኘው የአገሪቱ ብቸኛ የአስክሬን ምርመራ ክፍል ሲሰሩ የቆዩ ኩባዊት የህክምና ባለሙያ የስራ ውላቸዉን አጠናቅቀው ስለተሰናበቱ የምርመራ አገልግሎቱ ተቋረጠ፡፡ ለስድስት አመት የስራ ውል እየተፈራረመ በሚያስመጣቸው ኩባዊ ባለሙያዎች አማካኝነት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የአስክሬን ምርመራ ክፍል፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲያገለግሉ ከቆዩት ኩባዊት ዶክተር ጋር የተፈራረመው ውል ለሁለት አመት ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በወቅቱም፣ በአስከሬን ምርመራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ባለመኖራቸው ከኩባ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ለማስመጣት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ በማለት አንድ የሆስፒታሉ የስራ ሃላፊ መናገራቸዉ ይታወሳል፡፡ የኩባዊቷ ሃኪም የወር ደሞዝ 6ሺ ብር እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሦስት ሳምንት በፊት መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም ባለሙያዋ በመታመማቸው ለሶስት ቀናት የአስከሬን ምርመራ ተቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በርካታ የሟች ቤተሰቦችና ሃዘንተኞች ለቀብር ስነ ስርዓት መንገላታቸውን እንደዘገብን ይታወቃል። ይሁን እንጂ፣ ኩባዊቷ ሃኪም የስራ ውላቸዉ ተጠናቅቆ ሰሞኑን ሲሰናበቱ ምትክ ባለሙያ ባለመዘጋጀቱ አገልግሎቱ የተቋረጠ ሲሆን፣ ሆስፒታሉ ለምርመራ የሚመጡ አስከሬኖችን እንደማይቀበል የሚገልፅ ማስታወቂያ ለጥፏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራ ሊካሄድባቸዉ የሚገቡ አስከሬኖችን ለማስቀመጥ የሚያስችል የማቆያ ስፍራ ስለሌለው በሆስፒታሉ ውሳኔ አልተስማማም፡፡ የፖሊስና የሆስፒታሉ ሃላፊዎች ተነጋግረውም ነው፣ ሆስፒታሉ ትናንት አስከሬኖችን መቀበል የጀመረው። ሆስፒታሉ መቼ የምርመራ ባለሙያ እንደሚያገኝና መቼ አገልግሎቱን እንደሚጀምር የታወቀ ነገር የለም፡፡

No comments:

Post a Comment