Friday, October 4, 2013

ለፈውስ ያልነው ለሞት!(መታሰቢያ ካሣዬ)

ለፈውስ ያልነው ለሞት!
እነፓራሲታሞል ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ
እንደ አለም ጤና ድርጅት ትርጓሜ፤ መድሃኒቶች በርካታ ንጥረ ነገሮችን የያዙ በሽታን ለማከም የሚረዱና ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በፋብሪካ ደረጃ እየተመረቱ ገበያ ላይ የሚውሉና በጤና አገልግሎት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ኬሚካሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በተገቢው ጊዜና ሁኔታ፣ በትክክለኛው መጠንና በባለሙያ ትዕዛዝ ሲወሰዱ የታለመላቸውን ግብ በመምታት በሽታን ለመከላከል፣ለማከምና ህመምተኛውን ወደ ጤናማ ሁኔታ ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መድሃኒቶች በዘፈቀደና ያለባለሙያ ትዕዛዝ አሊያም ከታዘዘው መጠን በላይ ወይም በታች ሲወሰዱ ፈውስነታቸው ቀርቶ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ መርዞች ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡ መድሃኒቶች ነፍስን የመታደጋቸውን ያህል ህይወትን ሊቀጥፉ ይችላሉ፡፡ ለህመም ማከሚያና ማዳኛ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ፈዋሽ ናቸው የሚባሉት የታለመላቸውን ግብ በአግባቡ መምታት ሲችሉ ነው፡፡

ይህንን ተግባር በሚያከናውኑበት ወቅት አላስፈላጊ ውጤቶችን (የጎንዮሽ ጉዳቶችን) ሲያስከትሉ ይችላሉ፡፡ መድሃኒቶች በጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረጉት የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከጠቀሜታቸው አንፃር ተመዝኖ ጉዳቱ ያነሰ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በመሰረቱ ሁሉም ዓይነት መድሃኒቶች የየራሳቸው የሆነ የጎንዮሽ ጉዳቶች (side effects) አሏቸው፡፡ ይህም መድሃኒቶቹ በሚይዟቸው ንጥረ ነገሮችና በሚሰሩባቸው ኬሚካሎች መነሻነት የሚከሰት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ መድሃኒቶች በሃኪም ትዕዛዝ መሰረት የሚወሰዱና ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ ቢወሰዱ አደጋ ላይ የሚጥሉ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ ውጪ (prescription) ውጪ የማይሸጥና ቢሸጡ የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ የመድሃኒት ዓይነቶችም አሉ፡፡ የዚህ አይነት መድሃኒቶች የሚታዘዙትም በመደበኛ የህክምና ባለሙያ ሳይሆን የስፔሻላይዜሽን ዕውቀት ባላቸው የህክምና ባለሙያዎች ነው፡፡
እነዚህ ዓይነት መድሃኒቶች ሱሰኝነት ወይንም የመድሃኒት ጥገኝነትን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ያለሃኪም ትዕዛዝ ወይንም ያለመድሃኒት መሸጫ ወረቀት (prescription) ሲሸጥ የተገኘ የመድሃኒት ዕደላ ባለሙያ (pharmacist) በሙያ ሥነምግባር ጉድለት የሚጠየቅ ሲሆን ከህግ ተጠያቂነትም አያመልጥም፡፡ በአደጉት አገራት መድሃኒቶችን ያለሃኪም ማዘዣ ወረቀት መሸጥ የሚያስከትለው ቅጣት ቀላል ባለመሆኑ የመድሃኒት እደላ ባለሙያዎች (pharmacist) በእጅጉ ጥንቁቅ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ያለሃኪም ትዕዛዝ የመድሃኒት እደላ ባለሙያው ከህመምተኛው በሚያገኘው መረጃ መሰረት ሊሰጣቸው የሚችላቸው የመድሃኒት አይነቶችም አሉ፡፡ እነዚህ መድሃኒቶችም ቢሆኑ ለህመምተኛው ጊዜያዊ መፍትሄ የሚሰጡና የህመም ስሜትን ለማስታገስ የሚረዱ ከመሆን በዘለለ የሚሰጡት ጠቀሜታ እምብዛም መሆኑን ህመምተኛው በግልፅ ሊያውቅ ይገባል፡፡
የመድሃኒት እደላ ባለሙያው፤ ህመምተኛው መድሃኒቶቹን ለተወሰኑ ጥቂት ቀናት ወስዶ ለህመሙ መፍትሄ ካላገኘ ወደ ህክምና ባለሙያ ዘንድ ሄዶ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባው በግልፅ ሊነግሩ እንደሚገባ ህጉ ይደነግጋል፡፡ ለራስ ምታት፣ ለጉንፋን፣ ለሆድ ቁርጠትና መሰል ቀለል ያሉ በሽታዎች በፋርማሲ ባለሙያዎች ታዘው የሚወሰዱ መድሃኒቶች በራሳቸው እጅግ የከፋ ጉዳትና እስከሞት ሊያደርስ የሚችል የሚደርስ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እንደ አስፕሪን፣ፓራሲታሞል፣ፓናዶልና አድቪል ያሉ ያለ ሃኪም ትዕዛዝና ያለመድሃኒት ማዘዣ ወረቀት በቀላሉ እየተገዙ ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶች አለአግባብ ከተወሰዱ በጤና ላይ ከባድ ጉዳት ከማስከተላቸውም በላይ ህመምተኛውን ለሞት ሊዳርጉትም ይችላሉ፡፡ እንደ ጤና ድርጅቱ መረጃ፤ በዓለም ዙሪያ ፓራሲታሚል ያለአግባብ የሚወስዱ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡
እነዚህ ለቀላል የህመም ስሜት ማስታገሻነት ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶች ይህን መሰል እጅግ የከፋ አደጋ ማድረሳቸው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ ራስ ምታት፣የሆድ ቁርጠት፣ቀለል ያሉ ሳል፣አለርጂና መሰል የጤና ችግሮች በአብዛኛው እንደ ቀላል ችግር የሚታሰቡና እምብዛም ትኩረት የማይሰጣቸው የበሽታ ዓይነቶች ቢሆኑም የማጅራት ገትር፣የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች ፣የልብ በሽታ፣የጉሮሮ ቫይረስ፣የኩላሊት፣ የጨጓራና የአንጀት በሽታዎች ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህመምተኛው ከመድሃኒት መደብሮች በቀላሉ እየገዛ የሚጠቀማቸው መድሃኒቶች ለህመም ስሜቱ ማስታገሻና ጊዜያዊ መፍትሄ ሰጪ በመሆናቸው ከህመም ስሜቱ በመታገሱ ዋነኛውን ትልቁን ችግር ችላ ይለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም ችግሩ መፍትሄ ሳያገኝ ቀርቶ ስር እየሠደደ በመሄድ በቀላሉ ሊድን ለማይችል የጤና ችግር አሊያም ለሞት ሊያበቃው ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለቀላል ራስ ምታት፣ ለመጫጫንና ለተለያዩ የህመም ስሜቶች ማስታገሻ እየተባሉ በዓለማችን ዙሪያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት እንደ ፓራሲታሞልና ፓናዶል መሰል የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በተደጋጋሚ የሚወስዱ ሰዎች ለመድሃኒቶቹ ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ካልወሰዱ በስተቀር ጤናማ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ ቀስ በቀስም የህመም ስሜታቸው በተቀሰቀሰ ቁጥር መድሃኒቶችን መውሰዳቸው በመድሃኒቶቹ ላይ እንዲጣበቁና ጥገኝነታቸውም እየጨመረ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ ጥገኝነታቸው በጨመረ ቁጥርም የሚወስዱትን መድሃኒት መጠን እንዲጨምሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ህመምተኛውን ለሌላ እጅግ የከፋ ጉዳት ለሚያስከትልበት የጤና ችግር የሚያጋልጠው ይሆናል፡፡
የፋርማሲ ባለሙያው ከህመምተኛው በሚያገኘው መረጃ መሰረት የሚሰጣቸውና ለቀላል ህመም ማስታገሻ እየተባሉ የሚወሰዱት መድሃኒቶች ትላልቅ የጤና ችግሮችን በመደበቅ በወቅቱ ታይተው ምርመራና ህክም እንዳያገኙ በማድረግ ህመምተኛውን ከባድ ለሆነ የጤና ችግር ይዳርጋሉ፡፡ የመድሃኒት ዕደላ ባለሙያዎች እነዚህን መድሃኒቶች ለህመምተኛው በሚሸጡበት ወቅት ህመምተኛው በመድሃኒቶቹ ተጠቅሞ መፍትሄ ካላገኘ ወይም ህመሙ እየተባባሰ የሚከሰትበት ከሆነ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንዳለበት የመንገር ሙያዊ ግዴታ እንዳለባቸውና ህመምተኞችም በቀላል ገንዘብ ተገዝተው የሚወሰዱት እነዚህ መድሃኒቶች የከፋ ችግሮችን ሊያስከትሉ የሚችሉ መሆናቸውን ተገንዝበው ጥንቃቄ ሊያደርጉና ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ መረጃው አሳስቧል፡፡ ነፍሳችንን እንዲታደግ የወሰድነው መድሃኒት መጥፊያችን እንዳይሆን ትኩረትና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡

No comments:

Post a Comment