ጄኔራል ታደሰ ብሩና ማንዴላ |
ሻምበል ጉታ ዲንቃ በንጉሡ ዘመን የፖሊስ መኮንን ነበሩ። ማንዴላን በከፍተኛ ሚስጥር እንዲጠብቁ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ጄኔራል ታደሰ(የማንዴላ አሰልጣኝ በወቅቱ ኮ/ል የነበሩ)፣ኮ/ል ፍቃደ እና ሻምበል ፈቃደ ውስጥ ነበሩ።ዛሬ የ76 አምቱ የእድሜ ባለፀጋ ሻምበል ጉታ ዲንቃ ለሸገር ሲናገሩ እንዲህ አሉ።
'' ማንዴላን እንድጠብቅ ኃላፊነት የተሰጠኝ እኔ ነበርኩ።ማንዴላ የሚያድሩበት እና ወታደራዊ ስልጠና የሚወስዱበት የኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ቦታ በተለይ እርሳቸው የሚገኙበት ቦታ 'የፈንጅ ወረዳ' ነበር የሚባለው።ከአራታችን በቀር ማንም ወደ እርሳቸው ቦታ ዝር ማለት አይችልም። ሲተኙ መስኮት ከፍተው ነው የሚተኙት።አንድ ቀን ታድያ አብሮኝ ከሚሰራው የፖሊስ ባልደረባዬ በጥብቅ እንደሚፈልገኝ ነገረኝ።ጣይቱ ሆቴል ተቀጣጠርን እና ሃሳቡን ገለፀልኝ።'' ካሉ በኃላ አሁን አዲስ አበባ ላፍቶ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ሻምበል ጉታ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል-
''ጣይቱ ሆቴል የወሰደኝ ሰው ለጊዜው 2000 ፓውንድ በወቅቱ አስቡት 2000 ፓውንድን እና ሰጥቶ እንዲህ አለኝ- 'ሁለት ዕድል ከፊታችን ተቀምጧል።ሊያመልጠን አይገባም።ከፍተኛ ገንዘብ እናገኛለን።ቀጥሎም ወደ ውጭ ሀገር የመሄድ ዕድል አለን።ከአንተ የሚጠበቀው ማንዴላ በተኛበት ዛሬ ሌሊት በመስኮት ገብተህ በገመድ አንቀህ ግደል እና ውጣ እንደወጣህ መኪና ተዘጋጅቶ ይጠብቅሃል ከእዚህ የውትድርና ሕይወት እንገላገላለን' አለኝ። እኔም ጉዳዩን ከሰማሁ በኃላ በጉዳዩ የተስማማሁ መስዬ ቀጥታ ለጀኔራል ታደሰ ነገርኩኝ። ጉዳዩ በሚስጥር ተይዞ ይህንን ያደረጉት ሰዎች ተደረሰባቸው እና ከሀገር እንዲወጡ(እንዲባረሩ) ተደረጉ ይህ ሚስጥር ለዘመናት ከእኔ ጋር የኖረ ነው።ጉዳዩን ማንዴላም አያውቁትም።'' ብለዋል።
ኔልሰን ማንዴላ በወቅቱ እንደ ሻምበል ጉታ ዲንቃ አይነት ታማኝ የኢትዮጵያ የፖሊስ መኮንን ባይገጥማቸው ኖሮ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታሪክ ሂደትም ሆነ የነፃነት ትግሉ ታሪክ ሌላ መልክ በያዘ ነበር።ይህ ጉዳይ እጅግ ትልቅ ጉዳይ ነው።የኢትዮጵያ ፖሊስ ለአፍሪካ ያደረገው አስተዋፆ የሚያጎላ፣ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪክ ያደረገችው ትልቅ አስተዋፆ በመሆኑ በኢትዮጵያ የዜና አገልግሎቶች ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶት የዓለም አቀፍ የዜና ሽፋን እንዲያገኝ ጥረት ማድረግ ለኢትዮጵያ ፋይዳው ብዙ ይመስለኛል።
በመሆኑም ቢያንስ ለሻምበል ጉታ ዲንቃ የኢትዮጵያ ፖሊስ ጠርቶ ከማዕረግ እስከ ሽልማት ከእዚህ ባለፈም ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት እና ማንዴላ በሕይወት ዘመናቸው ሳሉ ሻምበል ጉታ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሄደው እንዲያገኙዋቸው ማድረግን ሁሉ ይጠይቃል።ጉዳዩ የደህንነት ሚስጥር የነበረ በመሆኑ በወቅቱ ግድያውን ሊፈፅም የሞከረው አካል ወይንም ሀገር (ማንነቱን ሻምበል ጉታ አልገለፁም (የተባረሩት ዜጎች የየት ሀገር እንደነበሩ አልገለፁም) ዛሬ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ጥላ እንዳያጠላ ስጋት ስለሚሆን ዜናው በተፈለገው ደረጃ ለዓለም ሕዝብ እንዳይደርስ የሚደረጉ ስውር ስራዎች እንደማይጠፋ ማጤን ሌላው ሥራ ሊሆን ይችላል።
በመጨረሻም ሻምበል ጉታ ዲንቃ ለሕዝብ ወጥተው ዛሬ ላይ ምንም ምስጢርነት የሌለውን ጉዳይ ለሕዝብ በመንገራቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
(ምንሊክ ሳልሳዊ)
No comments:
Post a Comment