Wednesday, October 9, 2013

ሜዳ ዉስጥ የንስሮቹ ተጫዋቾች እርስ በርስ በጣም ይሰዳደቡ ነበር፤ያልተሰደበ ተጫዋች ቢኖር አንድ ጆን ኦቢ ሚኬል ብቻ ነዉ፤

እሁድ ጥዋት ላይ አዲስ አበባ ገቡ፤የተያዘላቸዉ ግዮን ሆቴልን አልወደዱትም፤አሮጌ ነዉ..በዛ ላይ ለእግራችን ጥሩ ማሳረፊያ አይሆንም ብለዉ ወደ ቸርችል ሆቴል ሄዱ፤ልብ በሉ ጨዋታዉ 10 ሰአት ሊደረግ ነዉ መከረኛዉ ሲያሲያ ቡድኑን ረፋድ ይዞ ከች ያለዉ…
ወደስታድየም 8.30 ላይ መጡ፤አቻ ከወጡ ከአፍሪካ ዋንጫ እንደሚወጡ ያቁታል፤ከምድቡ ጊኒ ኢትዮጲያን 4-1 ስላሸነፈች በግብም የተሻለች ነች…ግን እምብዛም ለጨዋታዉ ጉጉት አይታይባቸዉም፤
ቶም ሴንት ፊት ጮሌ አሰልጣኝ ነዉ፤ስራ አልነበረዉም..ከናይጄሪያ ጋር ተጫዉቶ አቻ ቢወጣ ለሱ አሪፍ የስራ ድልድይ መሆኑን ቀድሞ አዉቆታል፤ቡድኑን የተረከበዉ ከኦኔራ ነዉ.ጣጠኛዉ ኦኔራ በናይጄሪያ 4-0 ተሸንፍዋል፤እናም ቶም ሴንት ፊት ይህንን ለመቀልበስ አሰላለፉን እንዲህ አደረገዉ..አስታዉሱ ይህ ጨዋታ ለአጥቂዉ ሳላሀዲን ከቅጣት መልስ የመጀመሪያዉ ነዉ፤
ይድነቃቸዉ ኪዳኔ…ደጉ ደበበ..አይናለም ሀይሉ…አበባዉ ቡታቆ…አሉላ ግርማ…
አዲስ ህንጻ..አስራት መገርሳ…አዳነ ግርማ…ጫላ ድሪባ
ፍቅሩ ተፈራ..ሳላሀዲም ሰኢድ
ጨዋታዉ 2-2 ተጠናቀቀ..ናይጄሪያ ወደቀች፤ግን ምንም አልመሰላቸዉም..እንደዉም ከጨዋታዉ በሁዋላ ማደርም አላስፈለጋቸዉም፤12 ሰአት ያልሞ የአዲስ አበባ ቆይታ አድርገዉ ምሽቱን ተመለሱ፤ሲያሲያ በዛዉ ተሰናበተ!!ይህ ከ2ት አመት በፊት የነበረዉ ጨዋታ ነዉ!!
ከዚህ በሁዋላ የረስተንበርጉ ጨዋታ በወሳኝነቱ የሚጠቀስ ነዉ፤ከኒልስፕሪት ወደ ረስተንበርግ ዋልያዉና ንስሩ አብረዉ ነበር የተጉዋዙት….አይሮፕላን ዉስጥ ከመገባቱ በፊት ተጫዋቾቹ በተለይ ከሚካኤልና ሞሰስ ጋር ፎቶ ተነስተዋል፤አሞካቺ ከነ ትይዩ ካለዉ ወንበር ላይ ነበር የተቀመጠዉ…የጡንቻዉ ፈርጣማነት የሚያስገርም ነዉ..ቁጥብ ባለ ሁኔታ..አፍሪካ በቴክኒክ ደረጃ የላቁ ተጫዋቾችን እንደከዚህ ቀደሙ ማፍራት እንዳልቻለች አወራኝ..ስለጨዋታዉ ማዉራት ግን እምበዛም አልፈለገም፤
ሜዳ ዉስጥ የንስሮቹ ተጫዋቾች እርስ በርስ በጣም ይሰዳደቡ ነበር፤ያልተሰደበ ተጫዋች ቢኖር አንድ ጆን ኦቢ ብቻ ነዉ፤(የባንክ አካዉንት እያዩ ይሆን የሚሳደቡት)በጭራሽ አይከባበሩም፤በተለይ ኡቼ በጣም ይሳደባል፤ይህንን ነገር ከነገሩኝ የዋልያዉ ተጫዋቾች አንዱ–ዛሬ አሸንፈናቸዉ ምን እንደሚሆኑ ማየት ነበር የናፈቀኝ አለኝ፤
የጨዋታዉ ምርጥ 11 የኢትዮጲያ ብሂራዊ ቡድን ተሰላፊዎች አዳዲስ ፊቶችን ያካተተ ነበር;ያ ብቻ ሳይሆን 4ት በረኞችን በ3ት ጨዋታ ያሰለፈ  ቡድን ሁንዋል…
ሲሳይ ባንጫ (አዲስ ህንጻ)
አበባዉ..ደጉ..ቢያድግልኝ…አሉላ
ጌታነህ..አዲስ..ዳዊት …ዩሱፍ
ኡመድ ኡክሪ  ሳላሀዲን ሰኢድ
ቪክተር ሞሰስ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን አግብቶ ጥል በጥል የሖኑት ናይጄሪያዎች አሸነፋ፤
ጨዋታዉ ማለቂያ ላይ ቪክቶር ሞሰስ ቢያድግልኝ ኤልያስ ጋር ማልያዉን ተቀያየረ፤እናም አንዲህ አለዉ፤
በርታ አሪፍ ደረጃ ትደርሳለህ!!!
ይህን ጨዋታ በሬድዮ ሳስተላልፍ ሁለት ተጫዋቾች አብረዉኝ በየመሀሉ አስተያየታቸዉን እየሠጡ አስተላልፈዋል፤ጀማል ጣሰዉ በቅጣት..አዳነ ግርማ በጉዳት ጨዋታዉን አልገቡም፤እናም በሬድዩ (97.1) አስተላለፉ..ጨዋታዉ ሲያልቅ ህልሙ በመጀመሪያዉ ጨዋታ የተቀጨበት ጀማል እምባዉን አዉጥቶ አለቀሰ!!የኢ.ፌ.ዴሪ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሀኖም ቡድኑ ከሜዳ ወደ ሆቴል እየሔደ ባለበት ጊዜ ስልክ ደዉለዉ ከ40 ደቂቃ በላይ 10 የሚጠጉ የቡድኑ አባላትን አነጋግረዋል!!
ከ4ት ቀናት በሁዋላ ናይጄሪያ አዲስ አበባ ላይ ሲጫወት በ3አመት 3ተኛዉን ጨዋታ ከዋልያዉ ጋር ያደርጋል ማለት ነዉ፤

No comments:

Post a Comment