Thursday, October 10, 2013

የሪፖርተር ማኔጂንግ ኤዲተር በደቡብ ክልል ፖሊስ ተወሰደ

የሪፖርተር ማኔጂንግ ኤዲተር በደቡብ ክልል ፖሊስ ተወሰደየሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር መላኩ ደምሴ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ አዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ከሚገኘው የሪፖርተር ቢሮው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የፖሊስ ኃይል አባላት ተይዞ ወደ ሐዋሳ ከተማ ተወሰደ፡፡

የፖሊስ አባላቱ የያዙት የፍርድ ቤት ማዘዣ እንደሚያመለክተው፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ ‹‹የደቡብ ክልል ሦስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ከኃላፊነት ተነሱ›› በሚል ባተመው ዜና ምክንያት ጋዜጠኛ መላኩ ለጥያቄ መፈለጋቸውን ይገልጻል፡፡ አዘጋጁ በቅድሚያ አምቼ አካባቢ በሚገኘው በቦሌ ክፍለ ከተማ በፖሊስ ማዘዣ የተወሰደ ሲሆን፣ በኋላም ለክልሉ ፖሊስ አባላት ተላልፎ መሰጠቱ ታውቋል፡፡
የክልሉ ኃላፊዎቹ ተነስተዋል በሚል ሪፖርተር ጋዜጣ የዘገበው ዜና ስህተት መሆኑን በማመን በቀጣይ ዕትሙ እሑድ ጳጉሜን 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ላይ ዜናው በወጣበት የጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ ማስተካከያ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በሐዋሳ የሚገኘው የሪፖርተር ባልደረባም ይህንን ዘገባ በማጠናቀርና በመዘገብ ለሠራው ስህተት ዝግጅት ክፍሉ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱ ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment