Monday, August 19, 2013

አስተምርሆ በሁሉም ላይ የሚደርስ ግን ደግሞ ጥንቃቄ ልናደርግ የሚገባን አርቲስት ኢዮብ መኮንን ለሞት ያበቃው ስትሮክ (Stroke)

ሁሉም ሰዉ ሊያነበዉ የሚገባ

- በዓመት ለ40 ሚሊዮን ሰዎች ሞት መንስኤ ነው
– ለድንገተኛ ሞት እና አካል ጉዳት ይዳርጋል
– ማንን ያጠቃል? ወንዶችን ወይንስ ሴቶችን?
– መነሻው እና መፍትሄውስ ምንድን ነው?

የግንባታ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ የሆኑት አቶ ግዛቸው ጉደታ ከ25 ዓመት በላይ አገራቸውን በግንባታው ዘርፍ አገልግለዋል፡፡ የዛሬን አያድርገው እና የእሳቸው ሞያዊ አሻራ ያረፈባቸው ትልልቅ ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ህክምና ተቋማት እና የመንግስት ድርጅቶች በርካታ እንደሆኑ በኩራት ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ግን አቶ ግዛቸው እንደበፊቱ የውብ ህንፃዎችን ዲዛይን ተቆጣጥሮም የማሰራት አቅማቸውን አጥተዋል፡፡ ምክንያቱም አቶ ግዛቸው ከየካቲት 8/2002 ዓ.ም ካጋጠማቸው ድንገተኛ አደጋ በኋላ መንቀሳቀስ ተስኗቸዋል፡፡
አንደበታቸውም አልፈታ ብሎ የሚናገሩት በግድ ነው፡፡ በዕለቱ የገጠማቸው አደጋም ህይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ቀይሮታል፡፡ በዚህም የተነሳ አቶ ግዛቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ይህቺን ቀን ሁሌም ያስታውሷታል፡፡ በየዓመቱም አስበዋት ይውላሉ፡፡
በጠንካራና ታታሪ ሰራተኝነታቸው ይታወቁ የነበሩት አቶ ግዛቸው ሁሌም እንደሚያደርጉት በዚያች ‹‹የተረገመች›› በሚሏት ቀን በጠዋት ነበር በስራ ቦታቸው ላይ የተገኙት፡፡ አልፎ አልፎ ከሚያስቸግሯቸው የደም ግፊት ህመም በስተቀር ሙሉ ጤነኛ የነበሩት አቶ ግዛቸው በዕለቱ ግን ከጠዋት ጀምሮ አንዳች የመጫጫን ስሜት ይሰማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ትኩረት አልሰጠሁትም እንጂ ከሳምንታት ጀምሮም ሰውነቴ ድክም ይልብኝ ነበር፡፡ ብርድ ብርድም የማለት ስሜትም ያስቸግረኝ ነበር›› ይላሉ፡፡ አቶ ግዛቸው በዕለቱ ሰዓታትን ከፈጀው እና በጭቅጭቅ የተሞላ ከነበረው የድርጅት ስብሰባ በኋላ ድንገት የበረታ ህመም ይሰማቸው ጀመር፡፡
‹‹ህመሙ ሲበረታብኝ 8 ሰዓት አካባቢ ፍቃድ ጠይቄ ወደ ቤት ሄጄ ለማረፍ ወስኜ መንገድ እንደጀመርኩ ነገሮች ተለዋወጡ›› የሚሉት አቶ ግዛቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ በድንገት መንገድ ላይ ራሳቸውን ስተው ወደቁ፡፡ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች እርዳታ በቅድሚያ ሆስፒታል እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ከዚያች ቀን በኋላ ራሳቸውን ለአንድ ወር ስተው የቆዩ ሲሆን ሲነቁ በህክምና ባለሞያዎች እና ቤተሰቦቻቸው በፊት ሰምተውት የማያወቁትን ችግር ስም ጠሩላቸው፡፡
‹‹ስትሮክ አጋጥሞህ ነበር›› ብለው ለአንድ ወር ራሳቸውን እንዲስቱ ያደረጋቸው ስትሮክ የሚባለው ድንገተኛ ችግር እንደሆነ ገለፁላቸው፡፡ ችግሩ ጥሎባቸው ያለፈው ጠባሳ ወደ ተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ሊያመራቸው እንደሚችል የሰጉት ሐኪሞችም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ውጪ አገር እንዲሄዱ የሚረዳ ማስረጃ ሰጧቸው፡፡ አቶ ግዛቸው ለህክምና ወደ ህንድ በማምራት በርካታ ገንዘብ ከስክሰው ብዙ ህክምና ማግኘት ቢችሉም እጅ እና እግሮቻቸው ዳግም መስራት እንደማይችሉ ሲነገራቸው በእሳቸውም ሆነ በቤተሰባቸው ላይ የደረሰው ድንጋጤ እና ሀዘን ከፍተኛ ነበር፡፡
አንደበታቸው እንደፈለጉት አልፈታ ብሎ እና ሁለት እግራቸውና እጃቸው አልታዘዝ ብሎ ቤት መዋል ከጀመሩ ሁለት ዓመት ያለፋቸው አቶ ግዛቸው ‹‹ስትሮክ በድንገት መጥቶ በግማሽ ገድሎኝ ሄዷል፡፡ መስራት እየቻልኩ የልጆቼ ጥገኛ አድርጎኛል፡፡ ሀብት እና ንብረቴንም አሳጥቶኛል፡፡ የሰው ሸከምም አድርጎኛል›› በማለትም ያማርራሉ፡፡ ‹‹ቀደም ባሉት ዓመታት ስለስትሮክ ሰምቼ አላውቅም ነበር፡፡ ሞኝ በራሱ ይማራል እንደሚባለው እኔም ሲደርስብኝ አወኩት›› ይላሉ አቶ ግዛቸው፡፡
አቶ ግዛቸውም ሆኑ ቤተሰቦቸው በድንገት ስለተከሰተባቸው የስትሮክ ችግር ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ያደረጋቸው ጥናቶችም ስትሮክ በብዙዎች የማይታወቅ ነገር ግን ብዙዎችን እየጎዳ ያለ ችግር መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ድርጅቱ ስትሮክ እያደረሰ ካለው የአካል ጉዳት እና ድንገተኛ የሞት አደጋ በመነሳት ለስትሮክ ህመም ‹‹ድንገተኛ መቅሰፍት›› የሚል መጠሪያ ሰጥቶታል፡፡ በአገራችንም ስትሮክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አቶ ግዛቸው የብዙዎችን በር እያንኳኳ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ስለስትሮክ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ነው፡፡ 

የስትሮክ ሀ…ሁ
ስትሮክ ወይንም ‹‹ሴሬብራል ቫስኩላር አክሲደንት›› አንጎል እና የደም ስር ላይ ከሚደርሱ ህመሞች አንዱ ነው፡፡ ባለሞያዎች ስትሮክ ድንገተኛ የሆነ አንጎል ውስጥ የደም ስርጭት መዛባት ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስትሮክ በአንጎላችን ውስጥ የደም ስርጭት መቀነስን ወይንም መጨመርን ተከትሎ የሚከሰት ህመም መሆኑ ይነገራል፡፡ በዓለም ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደመጣ የሚነገርለት ስትሮክ በዓመት በርካታ ሰዎችን ለድንገተኛ ሞት እንዲሁም አካል ጉዳት እየዳረገ ይገኛል፡፡
በዓለም ላይ ያለው የስትሮክ ህመም ስርጭት በትክክል አይታወቅም፡፡ ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት በአንጎል እና በደም ስሮች ላይ በሚከሰቱ ህመሞች ዙሪያ ያደረጋቸው ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ስትሮክ በተለይ በአደጉ አገሮች ከልብ ህመም እና ከካንሰር በመቀጠል ሶስተኛ የሞት መንስኤ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
በአሜሪካን አገር ለምሳሌ ስትሮክን ጨምሮ በአንጎል እና በደም ስር ላይ የሚደርሱ ህመሞች በዓመት ከ200,000 በላይ ሰዎችን ለሞት ይዳርጋሉ፡፡ በእንግሊዝም ስትሮክ ተመሳሳይ ስፋት ያለው ጉዳትን ያደርሳል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በተለይ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ብቻ በስፋት ይታይ የነበረው ስትሮክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮችም በስፋት መታየት ጀምሯል፡፡ በተለይ አፍሪካ እና ደቡብ አሜሪካ ላይ ስትሮክ ብዙ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በስትሮክ እና ተያያዥ ህመሞች በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት በመጪዎቹ ዓመታት በዓለም ላይ ከሚከሰተው የስትሮክ ችግር ከፍተኛውን ቁጥር (75 ከመቶ) የሚይዙት የታዳጊ አገራት ዜጎች እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ አሁንም ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት በዓለም ላይ ከሚከሰተው ከስትሮክ ህመም ጋር የተያያዘ ሞት አብዛኛው ስለበሽታ ባለማወቅ እና ህክምናውን በቶሎ ባለማግኘት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ስትሮክ በአንጎል ውስጥ የሚከሰት ድንገተኛ የደም ስርጭት መዛባት ችግር ሲሆን በዋናነትም የሚጎዳው የአንጎል ሴሎችን ነው፡፡ እንደ ባለሞያዎች እምነት አንጎል ላይ የሚደርስ ጉዳት ደግሞ ጉዳቱ እንደደረሰበት የአንጎል ክፍል፣ እንደ ጉዳቱ መጠን እና የስርጭት ስፋት ሌሎች የነርቭ ስርዓቶችን በመጉዳት ለተለያዩ ችግሮች ያጋልጣል፡፡
የአሜሪካን የህክምና ባለሞያዎች ማህበር ዓመታዊ ጆርናል የስትሮክ ህመም ሶስት ዋና ዋና ደረጃዎች እንዳሉት ይገልፃል፡፡ በዚህም መሰረት ድንገተኛው ስትሮክ በዋናነት የሚጎዳው አንጎላችንን ነው፡፡ አንጎል ላይ የሚደርስ ጉዳት ደግሞ በመቀጠል የደም ስሮቻችን እና የነርቭ ስርዓትን ይጎዳል፡፡ እነዚህ ጉዳቶች ደግሞ በአብዛኛው ሰዎች ለድንገተኛ ሞት እንዲጋለጡ የሚያደርግ ሲሆን አልፎ አልፎ ደግሞ እንደ አቶ ግዛቸው ሰዎችን ለከፍተኛ አካል ጉዳት በመዳረግ የሰዎችን እና የሰዎች የህይወት አቅጣጫ በማስቀየር ለበርካታ ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ይዳርጋል፡፡
የስትሮክ መምጪያ መንገዶች
አቶ ግዛቸውን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ስለስትሮክ ህመም መንሰኤም ሆነ ለህመሙ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ ነገሮች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ነው፡፡ በስትሮክ ህመም ህክምና ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉት ዶ/ር አንቶኒዮ ጉቲሬዝ የስትሮክ ህመም መንስኤ ምን እንደሆነ በትክክል እንደማይታወቅ ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ዋና ዋና አጋላጭ ምክንያቶችን በሚል የሚከተሉትን ነገሮች በመንስኤነት ያቀርባሉ፡፡
እንደ ዶ/ር አንቶኒዮ ገለፃ በአንጎል ውስጥ በሚከሰት ድንገተኛ የደም ስርጭት መዛባት የሚገለፀው ስትሮክ የሚከሰተው የደም ስሮች መጥበብን፣ በተለያዩ ምክንያቶች የደምስሮች በድንገት መቀደድን እና ደም በዘፈቀደ አንጎል ውስጥ መፍሰስን፣ በተለያዩ ምክንያት በሚከሰት የደም መርጋት ችግር የተነሳ ወደ አንጎል የሚደረገው የደም ስርጨቱን ማስተጓጎልን፣ የደም ስሮች በድንገት መኮማተርን ተከትሎ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ህመሞች የተነሳ የደም ዝውውር መስተጓጎል፣ በተለይ ደግሞ በደም ግፊት እና በስኳር ህመም መጠቃትን ተከትሎ አንጎል ውስጥ ያለው የደም ፍሰት ስርዓት መዛባት፣ በተለያዩ የደም ስር ህመሞች መጠቃት እንደ ዶ/ር አንቶኒዮ ገለፃ የስትሮክ ዋነኛ መምጫ መንገድ ነው፡፡ እንደ የዓለም ጤና ድርጅት እምነት የደም ግፊት ህመም፣ የልብ በሽታ፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የተለያዩ የነርቭ በሽታዎች፣ አዘውትሮ ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጦችን ማዘውተር፣ የስኳር ህመም፣ የዕድሜ መግፋት፣ የሰውነት ክብደት መጨመር እና የሰውነት ስብ ክምችት መብዛት፣ በተለይ ሴቶች ላይ ደግሞ የተለያዩ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች በብዛት መጠቀም እና በደማችን ውስጥ የቀይ ደም ሴሎች ከመጠን በላይ መብዛት ለስትሮክ ዋና ዋና አጋላጭ ምክንያቶች እንደሆኑ ይጠቁማል፡፡
‹‹ከሁሉም በላይ ግን የደም ግፊት እና በቁጥጥር ስር መዋል ያልቻለ ስኳር ህመም ለስትሮክ ዋነኛ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በተለየ መልኩ ደግሞ የአመጋገብ ባህላችን፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ረጅም ሰዓት ተቀምጦ መዋል የስትሮክ ዋነኛ መንስኤ ነው›› ይላሉ የስትሮክ ህመም ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አንቶኒዮ፡፡
እንደ ዶ/ር አንቶኒዮ ገለፃ ቀደም ባሉት ዓመታት ስትሮክ ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ ብቻ ይከሰት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ወጣቶችንም ሆነ ጎልማሶችን በስፋት እያጠቃ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ስትሮክ ከሴቶች ይልቅም በብዛት በወንዶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ከላይ በመንስኤነት ከተጠቀሱ ነገሮች በተጨማሪ ስትሮክ በዘር የመተላለፍ ዕድሉም ከፍተኛ እንደሆነ ዶ/ር አንቶኒዮ ይናገራሉ፡፡
ማወቅ ደጉ
በህክምና ባለሞያዎች በተደጋጋሚ የሚነገር አንድ አባባል አለ፡፡ ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› የሚል አባባል፡፡ ታዲያ ማንኛውንም በሽታ ሳይከሰት በፊት መከላከል የሚበረታታ ሲሆን ከተከሰተ በኋላም በቶሎ ህክምና ማግኘት የበሽታውን ስፋት ይቀንሳል፡፡ በቶሎ ህክምና ማግኘት የሚቻለው ደግሞ የህመሙን ምልክቶች ማወቅ ሲቻል ነው፡፡
ታዲያ እንደ አቶ ግዛቸው ብዙ ሰዎች ስለስትሮክ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ስለሆነ ችግሩ ከደረሰባቸው በኋላ እንጂ ቀደም ብሎ ስለሚያሳየው ምልክቶች ብዙም አያውቁም፡፡ በዚህም የተነሳ በቀላሉ መታከም በሚችሉ ህመሞች ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ እንመለከታለን፡፡ ብዙ የህክምና ባለሞያዎች ስትሮክ ግልፅ የሆነ የህመም ምልክት እንደሌለው ቢናገሩም ዶ/ር አንቶኒዮ ግን የስትሮክ ህክምና ምልክቶችን የህመሙን አይነት፣ መንስኤ እና ጉዳት የደረሰበት የአንጎል ክፍል መሰረት በማድረግ የተለያዩ የህመሙን ምልክቶች ይዘረዝራሉ፡፡
እንደ ዶ/ር አንቶኒዮ ገለፃ ስትሮክ በሶስት ይከፈላል፡፡ አንጎል ውስጥ የሚገኙ ደምስሮች ግድግዳ መጥበብን ተከትሎ የሚከሰተው ስትሮክ የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአንጎል ደምስሮች በመበሳት የተነሳ የሚከሰት ነው፡፡ ወደ አንጎል የሚደርሰው ደም እጥረት ደግሞ ሶስተኛ ነው፡፡
እንደ ዶ/ር አንቶኒዮ ገለፃ በተለይ የደም ግፊት እና የስኳር ህመም ባለባቸው ሰዎች ላይ በድንገት የሚከሰት የራስ ምታት ህመም፣ በተደጋጋሚ ማስመለስ፣ የማቅለሽለሽ ስሜትን ማስተናገድ፣ የማጅራት አካባቢ ህመም እና የማጅራት መገታተር፣ ድንገተኛ ፊት መጣመም እንዲሁም እጅ እና እግር መዛል እና የጡንቻዎች መዛል፣ በድንገት ግማሽ ወይንም ሙሉ የአካል ክፍል መደንዘዝ፣ የእጅ፣ የእግር እና የፊት ህመም የህመሙ ዋነኛ ምልክቶች ናቸው፡፡
በተለይ ስትሮክ ከመከሰቱ በፊት ባሉት ሳምንታት በድንገት ብርድ ብርድ ማለት፣ የጡንቻዎች ህመሞች፣ የሰውነት በቀላሉ መድከም፣ የመናገር ችግር እና የአንደበት መያያዝ ችግር መከሰት፣ መንተባተብ፣ ጆሮ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ተከትሎ የሰዎችን ንግግር ለመስማት እና ለመረዳት መቸገር፣ አካላዊ ሚዛን ለመጠበቅ መቸገር፣ ሲንቀሳቀሱ መንገዳገድ፣ የእጅ እና የእግር ጡንቻዎች መንቀጥቀጥ፣ የእይታ አቅም መቀነስ (የእይታ የጥራት መቀነስ እና ብዥታ) እንዲሁም ሽንት እና ሰገራን መቆጣጠር አለመቻል የስትሮክ ህመም ዋነኛ ምልክቶች ናቸው፡፡
አቶ ግዛቸው ደግሞ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ከእነዚህ ህመሞች በተጨማሪ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት በተደጋጋሚ ራስን መሳት፣ እንቅልፍ ማጣት ወይንም እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት በተለይ ሌሊት ላይ ደግሞ መቃዠት እንዲሁም የድብርት ስሜት በተደጋጋሚ ይሰማቸው እንደነበረ ይናገራሉ፡፡
ስትሮክ እና አንጎል
እንደሚታወቀው የሰውነታችንን አሰራር በዋናነት የሚቆጣጠረው አንጎላችን ነው፡፡ አንጎላችን ደግሞ ስራውን ለመስራት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የሚያገኘው በደም አማካኝነት ነው፡፡ በማንኛውም ሰዓት የደም አቅርቦት ችግር ሲከሰት አንጎል ተግባሩን በአግባቡ ለመወጣት ይቸገራል፡፡ ስለዚህ ወደ አንጎል የሚደረገው የደም ስርጭት በማንኛውም ሰዓት የተስተካከለ መሆን አለበት፡፡
አንጎላችን ድንገተኛ የደም ስርጭት ችግር ሲገጥመው በቅድሚያ የተለያዩ አማራጮችን በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ያደርጋል፡፡ በሌሎች የደም ስሮች አማካኝነት ወይንም በመጥበብ እና በመበሳት ለችግር የተዳረጉ ደም ስሮችን በማስፋት የተከሰተውን የደም እጥረት ችግር ለመቅረፍ ይሞክራል፡፡ እነዚህ አማራጮች ካልሰሩ ግን አንጎል የሚያስፈልገውን የኦክስጅን አቅርቦት ለማግኘት ስለሚቸገር በርካታ የአንጎል ሴሎች መሞት ይጀምራሉ፡፡
የአንጎል ሴሎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ደግሞ እንደ አቶ ግዛቸው የተለያዩ ሰውነት ክፍሎች ላይ አልታዘዝ የማለት ችግር ያስከትላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ እጅ እና እግር ዋነኛ ተጎጂዎች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ አልጋ ቁራኛነትን ያስከትላል፡፡ የሳንባ ምች እና የሰውነት ቆዳ መቆሳሰል ደግሞ የስትሮክ ህመምን ተከትለው ከሚከሰቱ ህመሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ታሞ ከመማቀቅ…
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ስትሮክ መዘዘ ብዙ ህመም ነው፡፡ በድንገት ለሞት እና ለአካል ጉዳት ይዳርጋል፡፡ አስቸጋሪ ባህሪ ያለው ስትሮክ መቼ እንደሚከሰት በትክክል አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ስኳር እና የደም ግፊት ህሙማን በማንኛውም ሰዓት ለስትሮክ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የስኳር ህመም እና የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች በማንኛውም ሰዓት ጥንቃቄዎችን ማድረግ አለባቸው፡፡ አመጋገባቸው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከቅባታማ ምግቦች ይልቅ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ማዘውተር፣ አካላዊ እንቅስቃሴን በየዕለቱ ማዘውተር፣ ዓመታዊ የጤና ምርመራን ማድረግ እና ቶሎ ቶሎ ባሞያዎች ማማከር ተገቢ ነው፡፡
በዶ/ር ፋሎስ ሚጋን የተባሉ የህክምና ባለሞያ ደግሞ ንዴት የደም ግፊት ዋነኛ ምንጭ እንደሆነ የደም ግፊት መጨመር ደግሞ በተለይ ወደ አንጎላችን የሚሄደውን የደም ዝውውር በማዛባት ለስትሮክ እንደሚያጋልጡ ይጠቁማሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ስሜቱን የመቆጣጠር ክህሎትን ሊያዳብር እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡
እንቅልፍ ማጣትን ተከትሎ ወይምን በተደጋጋሚ መናደድ በራሱ ለድብርት ስሜት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ስንናደድ እናዝናለን፡፡ በተደጋጋሚ ስናዝን ደግሞ ቀስ በቀስ ለድብርት ስሜት ልንጋለጥ የምንችልበት እድል ከፍተኛ ነው፡፡ በተመሳሳይ ንዴት ለሌሎች የስነ አዕምሮ ችግሮችም ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ስትሮክ ደግሞ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሲጋራ አለማጨስ፣ የአልኮል መጠጦች አወሳሰዳችንን ጤናማ ማድረግም ይመከራል፡፡ እንግዲህ አቶ ግዛቸውን ጨምሮ ብዙ በድንገተኛው የስትሮክ ህመም ተጠቅተው ለአካል ጉዳት እና ለድንገተኛ ሞት የተጋለጡ ሰዎች ስለስትሮክ ቀድመው የሚያውቁበት አጋጣሚ ቢኖር ኖሮ እነዚህ ጉዳቶች አይፈጠሩም ነበር፡፡ አቶ ግዛቸውም ሀብትና ንብረታቸውን አያጡም ነበር፡፡ ስትሮክ በድንገት ተከስቶ እጅ እና እግራቸውን በማሰር እንዲሁም አንደበታቸውን በመለጎም የሰው እጅ እንዲያዩና የልጆቻቸው ጥገኛ እንዲሆኑ አያደርጋቸውም ነበር፡፡ አገራቸውንም በሞያቸው ብዙ ማገልገል ይችሉ ነበር፡፡ እርሶም በማንኛውም ሰዓት ለዚህ ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ያውቃሉ? ካላወቁ ጥንቃቄ ያድርጉ ባለሞ ያዎችንም ያማክሩ፡፡ ካልሆነ ግን ዋጋውን ለመክፈል ይዘጋጁ፡፡

No comments:

Post a Comment