Saturday, August 31, 2013

ርዕስ በምርቃት፤ የማን ሙት አመት? (ስለ ሙስሊም ጉዳይ፤ ስለ አገር ጉዳይ)

ሁለት ዓመት ሊሞላው እየተንደረደረ ያለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ንቅናቄ ሂደት በተለያየ ወቅት የተለያዩ ጎላ ብለው የሚታዩ ክስተቶችን እያስተናገደ አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል። እነዚህ ጎላ ያሉ ክስተቶች አንዳንዴ ብቅ የሚሉት ከወደ መንግስት በኩል ሲሆን እኔም ጨረፍ አድርጌ ለማለፍ የምሞክረው ይህንኑ ከመንግስት በኩል ጎላ ብሎ ብቅ ያለውን ወቅታዊ ዘመቻ ነው። እንደሚታወቀው ይህ የሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ወደ መጀመሪያ አካባቢ ከመንግስት እውቅና ተነፍጎት ለጥቂት ጊዜ ከቆየ በኃላ የህዝቡን አካሄድ “ሸውደን” ማለፍ አንችላለን በሚል ድምዳሜ “ሰላማዊና ህገመንግስታዊ ” ስለመሆኑ ከመንግስት በኩል ይፋዊ ያልሆነ (በቃልና በደብዳቤ) ሙገሳ “ተችሮለት” ከመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር “ንግግር” ተጀመረ። በቅፅበትም መንግስት በይፋ እውቅና ያልተሰጣቸውን እነኚሁ ጥያቄዎች “ትክክለኛ” መሆናቸውንና “በአጥጋቢ ሁኔታ መመለሳቸውን” በይፋ በመገናኛ ብዙሃን ማስለፍለፍ ጀመረ። በተጓዳኝም ሰላማዊ የነበሩት የኮሚቴው አባላት ባንድ ጀንበር የ “አሸባሪነት ” ካባ ተደረበላቸው። ይሄ ኮሚቴውን “የመነጠል” ዘመቻ እስከ ቀትር አላስጉዝ ሲል: ወዲያው ጥያቄው “የጥቂት አክራሪዎች” ስለመሆኑና “ሰፊው ሙስሊም” ሕብረተሰብ ከመንግስት ጋር ስለምሆኑ ሰፊና ረጅም ዘመቻ ተከፈተ። ሙስሊሙን የመከፋፈል መሆኑ ነው። በዚህም ወቅት አንዳንድ ግልሰቦችን የተለያየ ቆብ አስለብሰው በቴሌቪዥን ላይ እያመጡ ስለ መንግስት ጥሩነት አስለፈፉ። እነዚሁን ግለሰቦች አንዴ ኮፍያ አንዴ ጥምጣም አንዴ ጋቢ አንዳንዴም አረንጉአዴ ነገር እያለበሱ: ሲላቸው “አንዳንድ ያዲሳባ ወይንም የምንትስ አካባቢ” ነዋሪዎች: ሲላቸው ደግሞ “የታወቁ የሃይማኖት ምሁራን” ወይንም ያገር ሽማግሌ: ገፋ ሲልም “የአህሉ ሱና ወልጀመአ” አባላት እያሉ ያቀርቧቸው ነበር። “የአህሉ ሱና ወልጀመአ” ማለት መንግስት “አህባሽ” የምትለዋን መገለጫ ለመደበቅ የዘየዳት የሽወዳ ቃል መሆኗ ነው። የሚገርመው አነዚሁኑ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦችን በስብሰባውም በቃለመጠይቁም በውይይቱም ባውደጥናቱም “በግንዛቤ ማስጨበጫውም” በወዘተውም በሁሉም ላይ ተናጋሪ መሆናቸው ነው። አንዳንዶች ምነው መንግስታችን ስንት ድራማ መስራት እየቻለ ለዚህ የሚሆኑ ሌሎች ሰዎችን መጨመር አቃተው? ይሉ ነበር። (በቅርብ ግዜ እንደወጡ ዘገባዎች ከሆነ መንግስት ሰላዮቹን እስራኤል ድረስ እየላከ በእስልምና ትምህርት አሰልጥኗል።)

ይሄው ረጅም ግዜ የወሰደው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ትንሽ እንኳ ጠብ ብሎ መንግስት የፈልገውን የመከፋፈል ሴራ ሊያሳካ ይቅርና ይብሱኑ ሙስሊሙ ኅ/ሰብ “ይሄ ነው ወይ መንግስት?” “እነዚህ ናቸው ወይ ያገር መሪዎች?” እያለ ይጠይቅ ገባ። በተያያዥነትም ተጠናክሮ የቀጠለው የፖሊስ ወከባ፣ አይን ያወጣ ዝርፊያ (በተለይም የኪስ ገንዘብ ነጠቃና የሞባይል ስልኮች ቅሚያ) እና ቅጥ ያጣው መረን የለቀቀው የደህንነቶች ዛቻና ማስፈራሪያ (intimidation) በሥራና በንንግድ ቦታ እየመጡ ማሸማቀቅ፣ በየቢሮው እየገቡ የፌስቡክ አካውንቶችን አስገድዶ ማስከፈት በተለይም ባንድ ወቅት በሰፊው ሲያኪያሄዱት የነበረው የሌሊት ቤት ሰበራና ዝርፊያ ከሁሉም በላይ ተጠናክሮ የቀጠለው እስር፣ ቶርችና ግዳያ: ሙስሊሙን ኅ/ሰብ ከማበሳጨትና ከማሳዘን አልፎ: የመብት ትግል ሙቀትን ከሩቁ የሚሸሹ፣ ከመንግስት ጋር “መነካካትን” የማይፈልጉ፣ እንዲሁም መጀምሪያ አካባቢ በመንግስት ተደናብረው የነበሩ ዜጎችን እስከነአካቴው ጥርግርግ ብለው ትግሉን እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል። የመንግስት ምኞት በዚህ ዘመቻ የትግሉን “አንቀሳቃሾች ማደንና” በጊዜ ሂደት መረቡን በጣጥሶ ትግሉን ማዳከምና ማክሰም ቢሆንም የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር። ከአመት በፊት መሪዎችን በማሰር ትግሉን ለማዳፈን ያሰበው መንግስት በድጋሚ በዚህ ዘመቻውም ሊሳካለት አልቻለም። መንግስት በሙስሊሞች ላይ ሲያሴር የነበረውን “የመከፋፈል” አጀንዳ አንዳልተሳካለት ያረጋገጠው ክስተት የታየው በቅርቡ በተከበረው የኢድ በዓል ላይ ያካሄደው የጅምላ (indiscriminate) ጭፍጨፋ ሲሆን ሴት፣ ሕፃን፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ ሳይል ለስለላና ለጥቆማ የላካቸውን ጀሌዎቹን ሳይቀር ያለርህራሄ የደበደበት ሂደት ነበር።
መንግስት በሙስሊሞች ላይ ያለውን ካርታ ተጫውቶ ጨርሷል፣፣ አሁን የሚቀረውን የመጨረሻ ካርድ በክርስቲያኑ ሕብረተሰብ ላይ መዟል። የወያኔ ውሸት ፍርድ ቤት እንኩአን ለድራማ አይመችም ብሎ ውድቅ ያደረገውን “ጥያቄው እስላማዊ መንግስት መመስረት ነው” የምትለዋ ቧልት፣ “በጠቅላይ ሚንስትርነት ማዕረግ ተመድቤ እየሰራሁ ነው” በሚሉት ግለሰብ (አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ) አጋፋሪነት አንደገና ተቀስቅሳ ክርስቲያኑን ለማስበርገግ ሰፊና የተቀናጀ ዘመቻ ተጀምሯል። (እዚህ ጋር የኬንያው ፕሬዝደንት ለረመዳን ሙስሊም ዜጎቻቸውን እንኩዋን አደረሳችሁ ለማለት አብረው የረምዳን አፍጥር መዓድ ሲቋደሱ፣ የኛው “መሪ” ግን ለኢድ በዓል በዋልታ በኩል ያስተላለፉት መልክት “ዋ! እንገላለን” አይነት መሆኑ ከኬንያ ጋር ያለንን ርቀት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ወደጉዳያችን፣) ይህ እጅግ አደገኛ የወያኔ “የክፉ ቀን” ካርድ በብዙዎች ዘንድ አንዲህ በቀላሉ ይመዘዛል የሚል ግምት አልነበረም። እነዚህ ጨቋኞች የፈልጉትን ለማግኘት አገሪቱ ዶግ አመድ ብትሆን ደንታም እንደሌላቸው በግልፅ የታየበት ወቅት ላይ ደርሰናል።ይህ ዘመቻ በአገር ውስጥና በውጭ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚገኙበት አካባቢ በስፋት አንዲካሄድ የታቀደ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ አንደነ ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ፣ ሰንደቅ አና ሌሎችም ጋዜጦች ልክ አንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቅንጅት እየሰሩበት ነው። እንደምታስታውሱት አንዴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ አገር ዕረፍት ላይ ናቸው ሲላቸውም ቤተመንግስት ውስጥ እያገገሙ ነው፣ ክብደት የቀነሱት በአዲሱ ዳይት ነው፣ ነገ አዲሳባ ሊገቡ ነው ወዘተ በማለት ህዝብን እንዲያደናግሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሲወጡ የነበሩ ጋዜጦች፣ አሁን ደግሞ አዲሱን ተልዕኮዋቸውን ለመወጣት አየሰሩ ይገኛሉ።
የዛሬ ዓመት አካባቢ“እነ አሕመዲን ጀማል ይቅርታ ጠየቁ” በሚል ርዕስ “አሕመዲን ጀማልን ጨምሮ በእስር በሚገኙት ሥምንት አባላት ፊርማ ደብዳቤው ለምክር ቤቱ እንደደረሰም ምንጮች ተናግረዋል፡፡” በማለት ስለታሰሩት የሙስሊም ኮሚቴ አባላት ሕዝቡን ለማደናገር የሞከረው አዲስ አድማስ ዘንድሮ ደግሞ “በ22 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ያስተዳደረ ሙስሊም የለም” የሚል መፈክር ሙስሊሞች ይዘው ወጡ ብሎናል። ጥያቄው “የስልጣን” ለማስመሰል ሆን ተብላ የተጨመረች መሆኗ ነው። ሪፖርተር ደግሞ በበኩሉ በ”ክቡር ሚኒስትር” አፃፃፍ ዘይቤ አይነት (satire) “የሙስሊሞች ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ፖለቲካዊ መፍትሔዎች” በሚል ርዕስ የፈበረክውን ልብወለድ “እውነት” አስመስሎ ለማቅረብ ሞክሯል። ይህንን የወያኔ ዘመቻ ልዩ የሚያደርገው በውጭ ያሉ የስርዓቱ ደጋፊና በመንግስት በጀት የሚደግፉ ድረገፆችና ሬድዮችን አቀናጅቶ መንቀሳቀሱ ነው። እነዚህ ድረገፆችና ሬዲዮ ፕሮግራሞች ከፍተኛና ሀልፊነት የጎደለው የስም ማጉደፍ ዘመቻ በሙስሊሙ ወገናችን ላይ የከፈቱ ሲሆን ግልፅ የሆነ የሙስሊም ጥላቻ “በአክራሪ” ስም ይሰበክባቸዋል። በተለይም በየድረገፆቹ አስተያየት መስጫ አምዶች ላይ ስማቸውን ቀያይረው እስላምና ሙስሊሞች ከምድረገፅ መጥፋት አንዳለባቸው በግልፅ ይወተውታሉ።ክርስቲያኑን ሕብረተሰብ ልትታረድ ነው እያሉ ከማስፈራራት አልፈው ትግራይ ኦንላይን በተባለው ድረገፅ “ተነስ” ተደራጅ ሳትቀደም ቅደም የሚል ግልፅ የጥፋት ጥሪ አስተላልፈዋል። ባንድ ወቅት የሙስሊሙን ጥያቄ ከዓባይ ግድብ፣ ግብፅና ናይል ፖለቲካ ጋር ለማሳሳብ ሌት ተቀን ሲታትሩ የነበሩ አሁን ፊታቸውን በቀጥታ ሙስልሙን ወደማጥቃት አዙረዋል። በተለያዩ የኢንተርኔት ገፆች የተገኙ ከእውነት የራቁና ምንም ሳይንሳዊ መስረት የሌላቸው “ጥናታዊ ፅሁፎች” በአማርኛ እየተተረጎሙ በድምፅና በፅሁፍ ያቀርባሉ። በተለያየ ወቅት “ከፓልቶክ” መድረክ ላይ “ተቀዱ” የተባሉ በማን አንደተንገሩ የማይታወቁ አፀያፊ ንግግሮች ከባዕድ አገር ከተፈፀሙ ቪድዮች ጋር እየተቀናበሩ ክርስቲያኑን የማስበርገግና ፍትሃዊ የሆነውን የሙስሊሙን ጥያቄ የማጠልሸት ዘመቻ ላይ ውለዋል። በአሜሪካን አገር በአክራሪ ነጭ ዘረኞች በሚመሩ ቤተክርስቲያናት አማካይነት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ፈሶባቸው የሙስሊም ጥላቻን ለማስፋፋት የሚሰሩ የተለያዩ ፅሁፎችና የሚዲያ ውጤቶች ላገራችን ሕዝብ እየተፈተፈቱ ያቀርባሉ።
ወያኔን ወደዚህ አደገኛ ውሳኔ ካደረሱት ነገሮች መካከል ሁለቱን አሁን መጥቀስ እፈልጋለሁ። አንደኛው የሙስሊሙን ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ማዳፈን እንደማይችል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ሲሆን፣ እንቅስቃሴውን ለመምታት ሰላምዊ ሂደቱ መደናቀፍ አለበት ብሎም ያምናል። እስካሁን ድረስ እልህ አስጨራሽ ትንኮሳዎችን ተቋቁሞ ሰላማዊነቱን ማስጠበቅ የቻለውን የሙስሊሞች ትግል ወደ አገራዊ ብጥብጥና የሃይማኖት ግጭት ካመራ ፣ መንግስት “ሰላምን” በማስጠበቅ ሰበብ የገደለውን ገድሎ (የፖለቲካ ተቃዋሚውንም ጭምር) የቀረውን ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ማድረግ እችላለሁ፣ ፣ በተጨማሪም ከምዕራባውያን “ለፀረሽብር ትግሉ” የማይነጥፍ ገንዘብና መሳሪያ አገኛለሁ። እንዲሁም ማንኛውም የፍትህ የዲሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄዎች እስከወዲያኛው ተዳፍነው ይቀራሉ ከሚል ቅዥት ሲሆን። ሁለተኛውና ተያያዥ የሆነው ምክንያት ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን የሙስሊሙን ሰላማዊ ትግል የመኮረጅና የመደግፍ አዝማሚያ መንግስትን በጣም ስጋት ላይ ስለጣለው ነው። ለዚህም ነው የመንግስት ባለስልጣናት ከሀይለማርያም ደሳለኝ እስከ ሽመልስ (ሼምየለሽ) ከማል ስለ “ፓርቲዎችና አክራሪዎች ጋብቻ” የሚያወሩት። ይህ ክርስቲያኑን የማስበርገግና የማነሳሳት ዘመቻ ፓርቲዎች ላይ ተፅዕኖ የማሰደርና ከሙስሊም ወገናቸው እንዲርቁና በተቃራኒውም እንዲቆሙ ግልፅ የሆኑ ጥሪዎች የተካተቱበት ነው። ይህው በክርስቲያኑ ላይ የተከፈትው የማስፈራራት ዘመቻ በሙስሊሞች ላይ የሚያርፈውን የግፍ ዱላ በማጠናከር የሚታገዝ ነው። ሙስሊሙን በበለጠ የማጥቃት አጠቃልይ ዘመቻ በቅርቡ የተጀመር ሲሆን እስርና ግድያውን ለማስፋፋት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ከራሱ ከመንግስት ባለስጣናት አፍ እየተነገር ነው።አቶ ኃይለ ማርያም “ትግስታችን አልቁዋል” ሲሉ አቶ በረከት ደግሞ ህዝቡ መንግስት ቦንብና መትረየስ አንዳለው አያውቅ ይመስል “መንግስት ኃይል አለው ጉልበት አለው” ብለዋል። (አይዝዎ አቶ በረከት ሳር ሳይሆን የሰው ሕይወት አጭዳችሁ ለዚህ መብቃታችሁ; እሱንም ለማስጠበቅ ባደባባይ መቶዎችን እንደረሸናችሁ ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል።) ሙስሊሙ በግፍ ብዛት ሲማረርና የወገን ያለህ ሲል ክርስቲያኑ ደግሞ ሙስሊም ወገኑን ይብሱኑ እንዲፈራው፣እንዲጠላው ጭራሹንም “ይገባቸዋል” እንዲልና አመቺ ሆኖ ሲገኝም በጥቃቱ እንዲተባበር ለማድረግ ያለመ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው። ይህ የመንግስት እቅድ ከተሳካ በክርስቲያኑና ሙስሊሙ ሕብረተሰብ መካከል ሊፈጠር የሚችለው የሃሳብ ልዩነትና ተቃርኖ ምን አይነት አስቃቂ ጉዳት ባገራችን ላይ ሊያደርስ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ስለዚህም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን መሰሪ ተንኮል ላገሪቱና ለራሱ ደህንነት ሲል በአንድነት በመቆም ማክሸፍ መቻል አለበት።
ምርቃት
የማን ሙት ዓመት? የማን ራእይ?

ሰሞኑን የመንግሥትና ደጋፊ ሚዲያዎችን ያጨናነቀው የታላቁ መሪ ሙት ዓመት ዝክር ነበር። ይህ ወደ ወር አካባቢ የፈጀው ሽርጉድ የመንግስትንና የህዝብ የስራ ሰዓትን ከመሻማት አልፎ የዕለት ተለት እንቅስቃሴዎችን አስተጓግሎ እንዲሁም ጥቂት የቀሩ ራዕዮችን ለአቶ መለስ አስረክቦ ቀዝቀዝ እያለ ያለ ይመስላል። እኔ አንዳንዴ ሳስበው ያለ መለስ ራእይ ያገራችን ግብርና ኢንዱስትሪ ትምህርት ጤና ሙዚቃ ጥበብ ሚሊተሪ አንደው ሁሉ ነገራችን የት ይሆን አንደነበር ሳስብ “ይዘገንነኛል”፣ በምድር ሳሉ ያላየናቸው “ራዕዮች” ወደዚያኛው ከሄዱ በኋላ መዥጎድጎዳቸውም አንዲሁ ። እድሜ ለሳቸው (ፅ ፅ! ይቅርታ ሞተዋል ለካ? ለነገሩ አንድ ግለስብ በቴሌቪዥን ቀርቦ ከገድላቸው አንዱ የሆነውን ” አህሉ ሱና ወልጀመአ ማህበር ያቋቋሙልን” ብሎ ሲያሞግስ “ገነት” መግባታቸውን መስክሮልናል።) አዎን እድሜ ለሳቸው ያገሪቱን ወታደራዊ ሃያል አሽመድምደው “ለጠላት” ካገለጧት በኋላ፣ ለምን ዝግጅት አልነበረም? ተብለው ሲጠየቁ፣ ያው እንደተለምደው በቃላት አክሮባት ጥበባቸው ፣ “በቴክኒክ ዝግጁ ባንሆንም በታክቲክ ግን የተሻለ አቅም ፈጥረናል” ሲያብራሩም “ደካማ ወታደርና የዛገ ታንክ ቢኖረንም ለዚያ ይወጣ የነበረውን ለልማት በማዋልችን የተሻልን ነን” አሉንና 80 000 ወጣት ዜጎችን አስጨርሰው በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ያገር ገንዘብና ሀብት አስባከኑ። ለጦርነቱ ከወጣው አጅግ ባነሰ ገንዘብና ያለምንም ሊባል በሚችል የሰው ይህወት ጠንካራ መከላከያ ቀድሞውኑ ቢኖር ኖሮ ያሁሉ ሕልቆመሳፍርት ሕይወትና ንብረት ባልተማገደ ነበር። ይህንን ለማወቅ ላቅምአዳም/ሔዋን መድረስ ብቻ በቂ ነበር። እንግዲህ እኒህ ጠቅላይ ነበሩ የወታደራዊ መሃንዲስ ባለራእይነት የተሸለሙት። እሺ ይሁን ግድ የለም፣ ግን የጋሽ ዘበርጋን ራእይ (ምኞት) ለጠቅላዩ ሲሰጥብኝ ግን አኔ በቃ! ብያለሁ።
ነገሩ አንዲህ ነው፣ ያደኩበት ሰፈር የማገዶ እንጨት በሸክም የሚያመጡ አቶ ዘበርጋ የሚባሉ ሰው ነበሩ፣ አፈሩ ይቅለላቸውና። ናም ያዲሳባ ደን እየተመንጠረ የሳቸውም ጉዞ አየራቀ መጣ። ከእድሚያቸው መግፋት ጋር በቀን ሁለቴ መሄድ እያቃታቸው መጣ። ያኔ ጋሽ ዘበርጋ ተመኙ በጣም ተመኙ ሃስብና ራዕያቸው ሁሉ የሰፈራችን ሜዳና ጋራ በደን ለመሸፈን፣(የዛሬን አይርገውና ያኔ ብዙ ክፍት ቦታና ሜዳ ነበር በየሰፈሩ) አሳቸው ወደጫካ ከሚሄዱ ጫካውን ወደራሳቸው የማምጣት “ራእይን ሰንቁ”። ብዙዎች በድህነታቸውና ባለመማራቸው የሚንቋቸው ጋሽ ዘቤክስ፣ ለብቻቸው ከቀበሌ ከፍተኛ እየተመላለሱ፣ ጠማሞቹን የቀበሌ ሹማምንት አሳምነው ራእያቸውን አሳኩ። ሜዳውን ሁሉ አስፈቅደው ችግኝ በችግኝ አደረጉት። እኛም በልጅ ልባችን እየረገምናቸው የሰፈራችንን ሜዳ ለችግኝ አስረክበን ኳስ ለመጫወት ሩቅ መሄድ ጀመርን። እናም ጠቅላዩ በሞቱ ባመቱ የጋሽ ዘቤ ራእይ እንዲሁ ለሌላ ሲሰጥ የኛ ሰፈር ልጆች ዝም ብለን አናይም! አራት ነጥብ። እኔ ምለው? ጠቅላዩ “ሞቱ” ከተባለ ጀምሮ በየሚዲያው በየቢሮው በየሰብሰባው በየመንገዱ በየወረዳ በኤምባሲዎች ጭምር ፎቶዋቸና ራእያቸው፣ እንዲሁመ የግብርና የኢንዱስትሪ የትምህርት የጤና የሙዚቃ የስነጥበብ የሚሊተሪ እንደው የሁሉም መሃንዲስ ተደርገው እየቀረቡ፣ አሁን “በቁም” ያሉት ሚኒስትር አንድም ቦታ ወይ ስማቸው ወይ ፎቶዋቸው ወይ “ራአያቸው” ሳይነሳ ዓመቱ ሲከበር፣ አሁንም እኔ ምለው የማን ሙት ዓመት ነው “አያከበርን” ያለነው? ማን ነው አንደሙት ስሙ የተርሳው? ማንንስ ነው አንደ ሕያው በየቀኑ የሚወሳው? ኧረ ለመሆኑ በየትኛው አገር ነው ያለው ተረስቶ የሞተው የሚነሳው? ህወሓት በሚመራው።
ሰላሙ ነኝ ቸር ያሰማን!
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=6928

No comments:

Post a Comment