Wednesday, August 14, 2013

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ‹‹ጽንፈኞች›› ጋር እየተንቀሳቀሱ ነው ያሏቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስጠነቀቁ



ፌኮ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ሕጋዊ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቀ
በኢድ አል ፈጥር በዓልና ከዚያ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሱትን ተቃውሞዎችና ግጭቶች ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹ጽንፈኞች›› ካሏቸው ጋር በመሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገር ለማወክ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በመግለጽ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጡ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን የመንግሥትን ወቀሳና ማስጠንቀቂያ ውድቅ በማድረግ መላው ኢትዮጵያዊ ትግሉን እንዲያጠናከር ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በአገሪቱ እየተስተዋለ የሚገኘውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ተቃውሞ አስመልክቶ ‹‹ጽንፈኞች በሃይማኖት ስም በመንግሥት ሥራ ጣልቃ እየገቡ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ጽንፈኞች የሃይማኖት አባቶችን በመግደል፣ በማሸማቀቅ፣ ሕዝበ ሙስሊሙን መፈናፈኛ አሳጥተን የራሳችንን እምነት በኃይል እንጭናለን በሚል እሳቤ ሁከት እየፈጠሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹መንግሥትን መቆጣጠር ይገባል፡፡ የሸሪዓ ሕግን መንግሥት መተግበር አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም ዓይነት እምነትም ሆነ ሃይማኖት አይኖርም፤›› በሚል እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ይህ ሁሉ ነገር እየሆነ በትዕግሥት ጉዳዩን ሲከታተል መቆየቱን የሚገልጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹መንግሥት ይህንን ያደረገበት ምክንያት ጽንፈኞቹን ከእስልምና እምነት ተከታዮች ለመለየት ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ጽንፈኞችን›› ለይቶ ለማውጣት መንግሥት የመረጠው ትዕግሥትና ያደረገው ጥረት ውጤታማ በመሆኑ፣ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ እንደተጀመረና ይህም ከዚህ በኋላ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ከጽንፈኞች ጋር ጋብቻ ፈጥረው የአገሪቱን ሰላም ለማወክ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እየተሰጣቸው ያለውን ማስጠንቀቂያ የማይቀበሉ ከሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወስድባቸዋል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ተቃውሞ በተመለከተ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ተመሳሳይ መግለጫና ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ እምብዛም ሲናገሩ አይስተዋሉም ነበር፡፡ 
የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ግን መንግሥት ጠንከር ያለ ዕርምጃ ለመውሰድ አቋም የያዘ አስመስሎታል፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹መንግሥት የሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይግባ›› የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ላይ በመንተራስ እያቀረቡ የሚገኙትን ተቃውሞና ጥያቄ በመደገፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 
በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖትና መንግሥት አንዱ በአንዱ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ከሚነሳው ተቃውሞ ጀርባ ጽንፈኝነትና የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላ ዓላማ መኖሩን በመግለጽ እያስጠነቀቀ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግሥትን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ የእስልምና እምነት ተከታዮች እያነሱ የሚገኙትን ተቃውሞ በመደገፍ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ይገኙበታል፡፡ 
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹መንግሥት በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መንገድ ብቻ የዜጐችን የእምነት ነፃነት በማክበር፣ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት አለበት፤›› ብሏል፡፡ 
መንግሥት የሙስሊሙ ኅብረተሰብን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ከመመለስ ይልቅ ጣልቃ ገብነቱን የሚቃወሙ የእምነቱን ተከታዮች በአሸባሪነት በመፈረጅ ማሰር፣ መደብደብና መግደልን መፍትሔ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ይህ የመንግሥት ተግባር ለአገር ሰላምና ደኅንነት አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡
መንግሥት የሙስሊሙ ኅብረተሰብን ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች በመደፍጠጥ ጭካኔና ሰብዓዊነት የጐደለው ተግባር እየፈጸመ ነው በማለት ኦፌኮ ባወጣው መግለጫ አውግዟል፡፡ 
በማከልም፣ ‹‹ሙስሊሙም ሆነ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግን -ሕገ መንግሥታዊ ድርጊት በመገንዘብ ትግሉን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ አጠናክሮ በመቀጠል አንድነቱንና ለሰላማዊ ትግል ትብብሩን ይግለጽ፤›› ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡ 

No comments:

Post a Comment