28 AUGUST 2013 ተጻፈ በ ታምሩ ጽጌ
-ወረዳዎችም የቤት ለቤት ቅስቀሳ ላይ ናቸው
የሰባት ሃይማኖቶች ስብስብ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ለማውገዝ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ፡፡
በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ ለምን ሰላማዊ ሠልፍ አስፈለገ ተብሎ ለቀረበ ጥያቄ በተሰጠ ምላሽ፣ የሕግ ጉዳይን ለሕግ በመተው አክራሪዎችና ጽንፈኞችን ማውገዝ የግድ ነው በማለት የጉባዔው ተወካዮች አስረድተዋል፡፡
ሰላማዊ ሠልፉ መነሻው ከተለያዩ የእምነት ተቋማት ወይም ከመኖሪያ ቤት ሆኖ፣ መድረሻና መሰባሰቢያው መስቀል አደባባይ መሆኑን ያስታወቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንና የወንጌላውያን አቢያተ ክርስቲያናት ኅብረት ናቸው፡፡
የጉባዔው ተወካዮች እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አሉ፡፡ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች አንዱ የአንዱን ሳይንቅ ወይም ዝቅና ከፍ ሳያደርግ፣ ዓለምን በሚያስገርምና በሚያስደምም ሁኔታ በመከባበር፣ በመቻቻልና በሰላም አብረው ኖረዋል፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሠረታቸው ውጭ አገር ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ተግባራት እየታዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ቀላል ፈንጂዎችን በማጥመድ ሆቴሎችን፣ ሬስቶራንቶችን፣ ቤንዚን ማደያዎችንና የሕዝብ ትራንስፖርቶችን በፍንዳታ እንዲወድሙ ከማድረግም ባለፈ፣ የንፁኃንን ሕይወት ሲቀጥፉ እንደነበር ያስታወሱት የጉባዔው ተወካዮች፣ ጽንፈኝነቱና አክራሪነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን በሚያሳይ ተግባር፣ በአንድ የሃይማኖት አባት ላይ ግድያ መፈጸሙንና በሌሎች ላይ የዛቻና ማስፈራሪያ መልዕክት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ድርጊት ሥጋት የፈጠረባቸው ምዕመናን በተለያዩ ክልሎች ባደረጓቸው ሰላማዊ ሠልፎች ድርጊቱን ማውገዛቸውን የገለጹት ተወካዮቹ፣ ጊዜው የዘገየ ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥሪያ ቤቶችና የተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች መቀመጫና የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባም፣ ሠልፉ መደረጉ አስፈላጊ በመሆኑ ጥሪውን ለማስተላለፍ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ለሰላማዊ ሠልፉ ጥሪ በዋናነት ምክንያት የሆናቸው ሁሉም የእምነት ተቋማት በየቤተ ዕምነታቸው፣ በ116 ወረዳዎች ከሚገኙ ምዕመናንና በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ባደረጉት ውይይት፣ ምዕመናኑ ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ ሠልፍ ወጥተው መግለጽ እንዳለባቸው ግፊት በማድረጋቸው መሆኑን የጉባዔው ተወካዮች ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ነሐሴ 15 እና 16 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደረገ የማጠቃለያ ውይይት ከአስተዳደሩ ፈቃድ በመገኘቱ፣ ሠልፉ እንዲደረግ ውሳኔ ላይ መደረሱን ተወካዮቹ አውስተዋል፡፡
የእስልምና ዕምነት መሪው ሼክ ኑሩ ላይ ግድያ ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሕግ ተይዞ በመታየት ላይ እያለ ሰላማዊ ሠልፍ መጥራቱ ከሕግ አግባብነት ጋር ስላለው ሁኔታ ተጠይቀው፣ ‹‹ሕጉ በሕግ ይሄዳል፤ እኛ ደግሞ እንደ ሃይማኖት አባትነታችን በሃይማኖት አባት ላይ ግድያ ሲፈጸም ዝም ብለን ማየት የለብንም፡፡ የሃይማኖት እኩልነት በሌለበት ጊዜ ተከባብሮና ተቻችሎ የኖረን ሕዝብ የሃይማኖት እኩልነት ባለበት ጊዜ፣ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ተግባር ሙከራዎች መኖር የለባቸውም፡፡ በመሆኑም የሕግ ጉዳይን ለሕግ ትተን ኅብረተሰቡ ትናንትና ከአባቶቹና ከእናቶቹ የወረሰውን የሃይማኖት መቻቻልና መከባበር ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲያካሂድ እንመክራለን፡፡ መወገዝ ያለበትን ጽንፈኝነትና አክራሪነትን እናወግዛለን፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሃይማኖት እኩልነት፣ መከባበር፣ መቻቻልና ሌላው እሴት በአንድ ጊዜ ይደረመሳል የሚል እምነት ወይም ሥጋት እንደሌላቸው የገለጹት የጉባዔው ተወካዮች፣ ብቅ ጥልቅ የሚሉትን የአክራሪነትና የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎች ሕዝቡን እንደማይጠቅሙ በመረዳት እንዲያወግዛቸው ለማድረግ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በዕውቀት ላይ መሠረት ያደረገ ሃይማኖታዊ ትምህርት በየቤተ ዕምነታቸው እንደሚያስተምሩ የገለጹት ተወካዮቹ፣ ኅብረተሰቡ ያለውን መከባበርና መቻቻል ደግሞ በተቋማቱ ጉባዔ በኩል አንድ ላይ ተሰባስበው መግለጽ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍቅርና ሰላም በአንድነት በማሳየት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚሯሯጡ አንዳንድ ጽንፈኞችንና አክራሪዎችን በጋራ ‹‹እረፉ›› በማለት ሊያወግዛቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
‹‹በማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የፖለቲካ ጉዳይ እንዲፈጸም አንፈልግምን›› ያሉት ተወካዮቹ፣ በሕገ መንግሥቱ ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ መሆናቸው ከመደንገጉም ባሻገር፣ የሥራ ክንውናቸውም ስለማይገናኝ፣ የሃይማኖት ተቋማት በነፃነት እምነታቸውን እያራመዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩ የሕዝብ ጉዳይ መሆኑንና ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ እንደሌላቸው የገለጹት የጉባዔው ተወካዮች፣ ሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች በሰላማዊ ሠልፉ ላይ በመገኘት የአክራሪነትና ጽንፈኝነት እንቅስቃሴውን እንዲያወግዙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሰላማዊ ሠልፉ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ እንደሌለውና ጉዳዩ የኅብረተሰቡ ጉዳይ በመሆኑ በአደባባይ ወጥቶ ማውገዝ እንዳለበት በተወካዮቹ ቢገለጽም፣ ቅስቀሳው በወረዳ ተመራጮች ቤት ለቤት እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የሃይማኖት ተቋማቱ ተወካዮች የሰላማዊ ሠልፉን በመገናኛ ብዙኃን ከገለጹ በቂ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የፖለቲካ ጉዳይ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ ነገር ግን እነሱ ከሰጡት መግለጫ በተጨማሪ የወረዳ ተመራጮች ‹‹እሑድ ሰላማዊ ሠልፍ በመስቀል አደባባይ ስለሚደረግ አክራሪዎችን ለማውገዝ እንድትወጡ፤›› የሚል መልዕክት ለነዋሪዎች እያስተላለፉ ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment