Written by መንግሥቱ አበበ
- በዓለም ላይ 140 ሚ. ልጃገረዶች የግርዛት ሰለባ ናቸው
- 92 ሚ. ያህሉ አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ
የሴትነት ግማሽ አካሏ ተቆርጦ የተቀበረባትን ያቺን ዕለት በፍፁም አትዘነጋትም፤ ዛሬም ድረስ ድርጊቱ ትናንት የተፈፀመ ያህል ነው የምታስታውሰው፡፡ ዛሬ ግን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምሥጋና ይግባውና ለጦንጤና በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ሴቶች ተስፋ ሰጪ የምሥራች የሆነ የሕክምና ጥበብ ብቅ ብሏል፡፡ ምሥራቹን ላቆየውና ወደ ጦንጤ ታሪክ ልምራችሁ፡፡ አያቷ፣ “የሚደረግላት ግርዛት፣ የተከበረች ሴት እንድትሆን፣ በጓደኞቿ ፊት እንዳታፍርና ወደፊት ደግሞ ባል የማግኘት ዕድሏን ከፍ እንደሚያደርግላት፤ እንዲሁም፤ በጣም ጠቃሚ ነገር ስለሆነ የሚያስጨንቅና የሚያስፈራ ነገር የለም” በማለት ጐጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዲፈፀሙባት አግቧቧት፣ አባባሏት፣ አሳመኗት፡፡
ጦንጤ፣ በዚያች ዕለት ስለሆነችው ነገር መናገር አትፈልግም፡፡ ምክንያቱም ትዝታዋ በጣም መራርና የሚያሳምም ነው፡፡ ከዚያ በፊት በታላቅ እህቷ ላይ ተመሳሳይ የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞ በጣም ብዙ ደም ስለፈሰሳት ማላዊ ሆስፒታል ተወስዳ ደም ተሰጥቷት እንደነበር ስለምታውቅ በጣም ፈርታ ነበር፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልቻለችም - ምስኪን ታዳጊ!
የዓለም ጤና ድርጅት፣ ግርዛትን፣ “የሴት ብልትን ውጫዊ አካል (ከንፈር) ግማሽ ወይም በሙሉ ማንሳት፤ ምንም የሕክምና ጥቅም ለሌለው ነገር በሴት ብልት ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ዓይነት ጉዳት” በማለት ይገልፀዋል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት የተለያዩ ማኅበረሰቦች ሴትን ልጅ “በጨዋነት” ለማሳደግ ይጠቅማል ብለው የሚያምኑበትና ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ጐጂ ባህላዊ ልማድ ነው፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት፤ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም 140 ሚሊዮን ልጀገረዶችና ሴቶች የዚህ ጐጂ ባህል ሰለባ ናቸው፡፡ 10 ዓመትና ከዚያም በላይ ዕድሜ ካላቸው የድርጊቱ ሰለባዎች መካከል 92 ሚሊዮን ያህሉ አፍሪካውያን መሆናቸውን ሪፖርቱ ጨምሮ አመልክቷል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት ድርጊቱ እንደተፈፀመና በረዥም ጊዜም የሚያስከትለው የጤና ጉዳት በርካታ ነው ይላሉ - በካሊፎርኒያ የሳን ማቴዎ የማህፀን ስፔሻሊስት ዶ/ር ማርሲ ቦወርስ፡፡ እንደ ጦንጤ ሁሉ በርካታ ሴቶች ከተገረዙ በኋላ ለዓመታት ይሰቃያሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግርዛቱ ጥሎባቸው የሚያልፈው ተጽእኖ፣ ፍርሃት ስለሚፈጥርባቸውና ቁስሉም በየጊዜው ስለሚያመረቅዝ እንደሆነ ዶ/ር ቦወርስ ይናገራሉ፡፡ የሐኪሟን ሐሳብ ጦንጤም ትጋራዋለች፡፡ ጦንጤ በአሁኑ ወቅት የ35 ዓመት ሴት ናት፡፡ ይሁን እንጂ ግርዛቱ በፈጠረባት ተጽእኖ ትዳር አልመሠረተችም - ሴተ ላጤ ናት፡፡ ምክንያቱም ሕመሙ ቋሚ ነው ትላለች ጦንጤ፡፡ ስለዚህም ማንም ሰው ቢሆን ብልቷ አካባቢ እንዲደርስ አትፈቅድለትም - ሐኪም እንኳ ቢሆን፡፡
ዶ/ር ቦወርስ፤ ሕመም፣ የበርካታ በሽተኞቻቸው ዋነኛ ችግር መሆኑን ለ”አፍሪካ ሪነዋል” መጽሔት ገልፀዋል፡፡ “የአብዛኞቹ ሕሙማን፣ የሴት ልጅ ከፍተኛው የወሲብ ስሜት ኅዋስ የሆነው ቂንጥር (Clitoris) በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ተቆርጧል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ለሽንትና ለወር አበባ መውጪያ፣ ለግብረ ሥጋ ግንኙነትና ለልጅ መውለጃ ትንሽ ቀዳዳ ብቻ አስቀርቶ፣ ሁለቱ ከንፈሮች ተስበውና ተወጥረው ብልትን እንዲሸፍኑ ተደርገው ይሰፋሉ” ይላሉ፡፡
ሐኪሟ ሴቶቹ የተስተካከለ ሕይወት እንዲመሩ ለበሽተኞች የግርዛት ተቃራኒ የሆነ “Reversal surgery” የሚሠሩ የሴት ብልትና ቂንጥር ጠጋኝ ቀዶ ሐኪም ናቸው፡፡ በግርዛቱ ምክንያት በቂንጢር አካባቢ የሚፈጠረውና ስፍራውን የሚሸፍነው ኅዋስ ጠባሳ፣ ለቀዶ ሕክምና ምቹ አይደለም፡፡ ነገር ግን የብልታቸው ከንፈሮች ተወጥረው የተሰፉትን ሴቶች፣ ስፌቱን በመተርተር፣ ከተሰፋበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ችግር እንዲሸኑና የወር አበባ እንዲፈሳቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲሁም ሳይሰቀቁ ወሲብ መፈፀምና ልጅም መውለድ ይችላሉ፡፡
ቀዶ ሕክምናው የበሽተኞቹን ስቃይ በማስቀረት ረገድ መቶ ፐርሰንት ውጤታማ መሆኑን ሐኪሟ ተናግረዋል፡፡ “እነዚህ ሴቶች ቀዶ ሕክምናውን ሲያደርጉ የሚደሰቱበት ዋነኛው ምክንያት ከስቃይና ከጭንቀት የሚገላግል እፎይታ ስለሚሰማቸው ነው” ብለዋል ዶ/ር ቦወርስ፡፡
የተገረዙ ሴቶችን እንደገና የመጠገን ቀዶ ሕክምና (Reconstructive surgery) ከተጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ ነገር ግን ቂንጥር እንደገና የመጠገን ቀዶ ሕክምና በፈረንሳዊው የሽንትና የፊኛ ስፔሻሊስት (Urologist) በዶ/ር ፒየር ፎልዴ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም የተጀመረ ነው፡፡ ዘዴው፣ ጠባሳውን ህዋስ በመክፈት ከስር የተቀበሩትን የነርቭ ህዋሳት ከጤነኛ ህዋሳት ጋር በማያያዝ ጠባሳው ስፍራ፣ አዲስ ጤነኛ ህዋስ እንዲያቆጠቁጥ ማድረግ ነው፡፡ አዲሱ ዘዴ፣ በግርዛቱ የተነሳ የሚመጣውን የማመርቀዝ ሕመም ይቀንሳል፡፡ ከዚህም በላይ ሴቶቹ፣ የወሲብ እርካታ መልሰው እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ አንዳንድ ሴቶች ይህንኑ ከፍተኛ የእርካታ ስሜት (Orgasm) ማጣጣም ችለዋል፡፡
ዶ/ር ፎልዴ፤ በርካታ ቀዶ ሐኪሞች ባሰለጠኑበት ቡርኪናፋሶ ደግሞ ሕክምናው ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ነው፡፡ ቀደም ሲል በ2001 መንግሥት አጠቃላይ ሆነ የሴት ብልት ቀዶ ሕክምና (Repair) ጀምሮ እንደነበር ብሔራዊው ፀረ-ግርዛት ኮሚሽን ሪፖርት አመልክቷል፡፡ በዚሁ ወቅት በአፍሪካ የቂንጥር ጥገና ቀዶ ሕክምና ያለምንም ችግር በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን ሰባት የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በሴኔጋል ዳካር በዶ/ር ፎልዴስና የማናንጃይት ዕጢ ካንሰር ባለሙያ (oncologist) በሆኑት ሴኔጋላዊው ዶ/ር አብዱል አዚዝ ካሴ ሠልጥነው በቅርቡ ሰርቲፊኬት ተቀብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዶ/ር ቦወርስ፤ የዶ/ር ፎልዴ ተማሪ ነበሩ፡፡ ለጦንጤ ኢኮሉባ የቀዶ ሕክምና በነፃ የሠሩትም እኚሁ ሐኪም ናቸው፡፡ እንዲሁም ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው ሴቶች ከሚበረከተው ከእያንዳንዱ ድጋፍ እኩል ከራሳቸው ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ከዓለም አቀፉ ፀረ-ሴት ልጅ ግርዛት ዘመቻ ኔትዎርክ ጋርም በመተባበር፣ ቀዶ ሕክምናው በሁሉም የአፍሪካ አገራት እንዲዳረስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
የፀረ-ሴት ልጅ ግርዛት ዘመቻ ኔትዎርክ የተቋቋመው እንዲህ ነው፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት በሚፈጽሙ ማህበረሰቦች ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱት ሕፃናትና እናቶች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ሆነ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ በአፍሪካ የሴት ሐኪሞች ቡድን ዓለም አቀፍ የፀረ-ሴት ልጅ ግርዛት ዘመቻ ኔትዎርክ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በ1998 ዓ.ም አቋቋሙ፡፡ ድርጅቱ፣ በኒውዮርክም ፀረ-ሴት ልጅ ግርዛት ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡ ምነው? የሥልጣኔ ባለቤት በሆነችው አሜሪካም እንዲህ ያለው ነገር ይፈፀማል? እንዳይሉ፡፡ ምክንያቱም የሴት ልጅ ግርዛት ከሚፈጽሙ ማኅበረሰቦች ወደ አሜሪካ የሚገባው የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡
ዓለምአቀፉ ኔትዎርክ በደቡባዊ ናይጄሪያ በምትገኘው ሃርኮት ወደብ ግርዛት ለተፈፀመባቸው ሴቶች ቀዶ ሕክምና የሚያደርግ ሆስፒታል እያሠራ ነው፡፡ የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ Restoration Hospital ተብሎ የሚሰየም ሲሆን፣ ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ሆስፒታሉ የምትሄድ ማንኛውም የግርዛት ሰለባ የሆነች ሴት ቀዶ ሕክምናው በነፃ ይሠራላታል፡፡ “በአሁኑ ወቅት ቀዶ ሕክምናውን ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠባበቁ 400 ሴቶች አሉን፡፡ እኛ ለቅቀን ስንሄድ ሕክምናውን በነፃ የሚሰጡ የአገር ውስጥ ሐኪሞች እያሰለጠን ነው” ያሉት አሜሪካ ያለው የኔትዎርኩ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ዶ/ር አበሪ ኢኪንኮ ናቸው፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ በአፍሪካ ያሉ አብዛኞቹ ሴቶች ለቀዶ ሕክምናው መክፈልም ሆነ ብዙ ርቀት ተጉዘው መታከም አይችሉም፡፡ ስለዚህ፤ ለሆስፒታሉ እውን መሆን ለሚያስፈልግ አቅርቦትና ዝግጅት ገንዘብ በኒውዮርክ ተሰብስቦ ወደ ናይጄሪያ ይላካል፡፡ የድርጅቱ ተስፋ የሆነው “ሪስቶሬሽን ሆስፒታል”፣ በግርዛት ሳቢያ ብዙ ቀናት በማማጥ የሚከሰተውን ፌስቱላ ጨምሮ ሌሎች የብልት ሕክምናዎችንም ለሴቶች በነፃ ይሰጣል ብለዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት አገራት ቁርጠኝነታቸውን እንዲጨምሩና ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ድርጅቱ የሴትን ግርዛት ለማስቀረት በመላው ዓለም ያስተላለፈው ጠንካራ ውሳኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀባይነት ያገኘው ኖቬምበር 26 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር፡፡
ውሳኔው ተቀባይነት እንዲያገኝ የላቀ ሚና የተጫወቱት የመጀመሪያዋ የቡርኪናፋሶ ሴት ቻንታል ኮምፓዎሬ፤ የአፍሪካ አገራት ውሳኔውን ተቀብለው እንደሚፈርሙና ክልከላውንም በኃላፊነት እንደሚያስፈፅሙ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ዓለም አቀፍ ጥረት ከተጀመረ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ፣ እነሆ አሁን ብዙ ማኅበረሰቦች ለውጡን እየተቀበሉት ነው፡፡ በ2011 በአፍሪካ ብቻ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ማኅበረሰቦች፣ ግርዛቱ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ፣ ሴት ልጆቻቸውን ከማስገረዝ ታቅበዋል፡፡ የሴት ልጅን ግርዛት የሕዝብ ጤና ጉዳይ በማድረግና አንዳንድ ጊዜም በወጣት ልጃገረዶችና ሴቶች ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ጐጂ ባህላዊና ልማዳዊ ተጽእኖ መሆኑን በማሳየት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ግለሰቦች እየበረከቱ በመምጣታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩን ለማስቀረት የሚደረጉ ትምህርታዊ ጥረቶች ተቀባይነት እያገኙ ነው፡፡
ግርዛትን ለማስቀረት ዓለም አቀፍ ተስፋ ቢኖርም፤ እስካሁን ድርጊቱ ለተፈፀመባቸው በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ሴቶች መፍትሔ ለማፈላለግ የተሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ ነው፡፡ ግርዛትን እንደገና የማስተካከሉ ቀዶ ሕክምና (ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ) እንደ ጦንጤን ላሉ ወጣት ሴቶች፣ “ከእግዜር የተላከ” የተራቀቀ ሳይንሳዊ የሕክምና ጥበብ ውጤት ነው፡፡ “የሴትነት ግማሽ አካሌን ቆርጠው ወስደውብኛል፡፡ ያንን አካሌን በማጣቴ በጣም ይሰማኛል፡፡ እንደገና ሙሉ አካል ያላት ሴት መሆን እፈልጋለሁ” ብላ ነበር ጦንጤ፡፡ የተመኘችው ስለተሳካላት እንኳን ደስ ያለሽ! ልንላት ይገባል፡፡ የዚህ ጐጂ ባህልና ልማድ ሰለባ ለሆኑ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶችና ሴቶች፣ አዲሱ የማስተካከያ ቀዶ ሕክምና መፍትሔ ይሆን ይመስለኛል፡፡ ያገራችን ሴት ሐኪሞች፣ በፀረ ግርዛት ዙሪያ የምትንቀሳቀሱ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና መንግሥት፣ ምን ትላላችሁ?
No comments:
Post a Comment