Wednesday, August 28, 2013

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የመጀመሪያ ቀን ውሎ

28 AUGUST 2013



 ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ከሃይማኖት ተቋማት አልፎ በወጣቶችና በሴቶች አደረጃጀቶች ላይ አነጣጥሯል›› የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
‹‹በቀላሉ እንደሚፈታ ተስፋ አለን›› የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 
‹‹አገራችን ስትታመም መድኃኒቷ እኛ ነን›› የእስልምና ጠቅላይ ጉዳዮች ምክር ቤት
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየታየ የሚገኘው ሃይማኖትን ተገን ያደረገ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ደረጃው ይለያይ እንጂ በሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንደሚታይ፣ በአሁኑ ወቅት ከሃይማኖት ተቋማት በመውጣት ወጣቶችና ሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መረቡን የማስፋት እንቅስቃሴ መስተዋሉን፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ገለጹ፡፡ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በመተባበር አገር አቀፍ የሰላም እሴትን ለማጎልበት ከነሐሴ 21 እስከ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. አዘጋጅቶና በመካሄድ ላይ ባለው ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ጉባዔው፣ ‹‹ሃይማኖቶች አብሮ የመኖር እሴት በማጎልበትና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን›› በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ጉባዔው እየተካሄደ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእስልምና ሃይማኖትን ተገን በማድረግ በኢትዮጵያ አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን የመፍጠር ዘመቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን፣ ይህንንም ለመቅረፍ የመንግሥት ጥረት ብቻ በቂ ባለመሆኑ ከአገሪቱ የእምነት ተቋማት ጋር መሠራት እንዳለበት በመንግሥት እምነት ተይዟል ብለዋል፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ ከእስልምና ውጭ ባሉ እምነቶች ውስጥ አክራሪነት መኖሩን፣ የእስልምና እምነትን ተገን አድርጎ በስፋት የሚስተዋለው አክራሪነት ከአሁኑ ካልተቀለበሰ እሳቱ ወደሌሎቹም ይዛመታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 
በዚህም መሠረት በሁሉም ክልሎች የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ጉባዔዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን፣ የተደረጉትን ውይይቶች አገር አቀፋዊ መልክ ለማስያዝ ጉባዔው እንዲካሄድ መወሰኑን ዶ/ር ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ሥር ሰደው ከመንገሳቸው በፊት ቀድሞ በእንጭጩ መመከት ካልተቻለ የዚች አገር ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ እንደሚሆን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ 
‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ኢትዮጵያዊ መነሻ የለውም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ባህሪው ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ሆኖ እየተዛመተ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአብሮ መኖር እሴት ለዘመናት የቆየ መሆኑን፣ ነገር ግን አክራሪነትና ጽንፈኝነት ሊያስከትለው የሚችለው የእርስ በርስ ግጭት ኢትዮጵያውያን የማያውቁት በመሆኑ፣ የአብሮ መኖር እሴታቸው ፋይዳን በትኩረት ያለመረዳትና ያለመገንዘብ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ 
‹‹በእንጭጩ የቤት ሥራችንን ካልሠራን በድህነት አረንቋ ላይ አክራሪነት የሚወልደውን ብጥብጥ ነው ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው፤›› ብለዋል፡፡ የአንድን ሃይማኖት ነፃነት መጋፋትና የሌሎች ሃይማኖቶችን መኖር አለመቀበል፣ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አመለካከት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህንን ለመዋጋትና በእንጭጩ ለመቅጨት አገር አቀፍ ጉባዔው መሰናዳቱን ዶ/ር ሽፈራው ገልጸው፣ በጉባዔውም በአምስት ነጥቦች ላይ ውይይት ተደርጎ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡ 
እነዚህም በኢትዮጵያ የሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር ታሪክና ፋይዳው፣ በኢትዮጵያ የነበሩ መንግሥታትና የሃይማኖት ብዝኃነትና አያያዝ፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት መነሻውና መድረሻው ምንድን ነው፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ ለማስፋት ትኩረት ያገኙና የተጋለጡ አካባቢዎችን መለየት፣ መከላከልና የሃይማኖት ተቋማት በኢትዮጵያ ጥልቅ የሆነውን የብዝኃነት እሴትና በሰላም አብሮ መኖርን ለማጐልበት ምን መሠራት ይኖርባቸዋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ዳሰሳዎችና ውይይቶችን በማካሄድ፣ በመጨረሻ የጋራ ኃላፊነት የሚወስድበት ጉባዔ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ 
የጉባዔው ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሲሆን፣ ጉባዔው በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የእምነት ተቋማት አባል የሆኑበት ነው፡፡ ጉባዔውንና በአገሪቱ ስለሚስተዋለው አክራሪነትና ጽንፈኝነት የየእምነቱ መሪዎችና ተጠሪዎች ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ 
የእስልምና ጠቅላይ ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሼክ ከድር ሙሐመድ በኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖቶች ገዢ መጽሐፍ መንፈሳዊ መልዕክት አንድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሃይማኖትን በጥበብ እንጂ በኃይል ማስፋፋት አይቻልም፣ አንዱ ሃይማኖት ሌላውን ሃይማኖት ያክብር፤›› የሚሉ የፈጣሪ ትዕዛዞችን የሁሉም ሃይማኖት መጻሕፍት ይሰብካሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ መልዕክት አሁን ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጋር ገጠመ ማለት ነው እንጂ፣ መንግሥት ስለ ሰላምና አብሮ መኖር እንዲሁም ስለ ሃይማኖት እኩልነት ተናግሮታልና እኛም እንናገረዋለን ብለን አይደለም እዚህ የተገኘነው፤›› ብለዋል፡፡ 
‹‹ሃይማኖት ሰላም ነው፣ አገራችን ሰላም ትፈልጋለች፡፡ ሰላም የሚለው ቃል የፈጣሪ ስም ነው፤›› የሚሉት ሼክ ከድር፣ ‹‹አገራችን ስትታመም መድኃኒቷ እኛ ነን›› በማለት የእስልምና ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ሰላም ኃላፊነት ወስዶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ 
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሚያነሱት ጥያቄ ተመልሷል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሃይማኖቱ መሪዎችን የተመለከተ ጥያቄ ብቻ እንደነበራቸው፣ ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የሃይማኖቱ መሪዎችን የመምረጥ ሥርዓት በተለየ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ተካሂዶ በተገቢው መመለሱን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እስልምናን ተገን በማድረግ የሚነሱ ጉዳዮች የሃይማኖቱ አይደሉም የሚሉት ሼክ ከድር፣ በ2004 ዓ.ም. በርካታ መስጂዶች በኃይል ተደፍረው ጅሃድ ታውጇል ብለው፣ ይህ የእስልምና እምነት ጥያቄ አይደለም በማለት በእምነቱ ጥላ ሥር የሚካሄድ ነው ያሉትን ጽንፈኝነት አውግዘዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ ‹‹መጀመሪያ የአገራችሁን ሰላም እሹ፣ ፈልጉ፤›› በማለት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምርና ቤተ ክርስቲያኗም በጉባዔው የተገኘችው ይህንን ለማስተማር ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፡፡ ኹከት ካለ ሁሉንም ነው የሚመታው፡፡ እገሌ ብቻ ይመለከተዋል የሚባል አይደለም፡፡ ለአገሪቱ የሰላምን ብርታት እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡ 
‹‹የኢትዮጵያን ሰላምና የዕድገት ጭላንጭል የሚፈታተኑ የሁላችንም ተቃራኒ ናቸው፡፡ ጐጂዎች ናቸው፡፡ ይህንን የመቋቋም ኃላፊነትና ግዴታ አለብን፤›› በማለት የቤተ ክርስቲያኗን አቋምና ኃላፊነት ተናግረዋል፡፡ በተጀመረው ጉባዔና በቀጣይም የሃይማኖት ተቋማት በሚኖራቸው ሚና ላይ ፅኑ እምነት እንዳላቸው የገለጹት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹ሰላም ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ብዙ ስለሆነ የሚስተዋለው ችግር በቀላሉ እንደሚፈታ ተስፋ አለኝ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ 
‹‹ለዚህም የየእምነታችን ተከታዮችን የአገራችሁን ሰላም ጠብቁ ብለን መስበክ የምንችልበት ሰፊ መድረክ አለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ የሁለቱ አባቶች መልዕክትና አቋም በሌሎቹ የሃይማኖት አባቶችም ተንፀባርቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጉባዔውን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር በአክራሪዎችና በጽንፈኞች ላይ መንግሥት በሕጉ መሠረት ዕርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ አክራሪነትን ጨምሮ ማንኛውንም ኹከት በሚፈጥሩ ላይ መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ጉባዔው ከሦስት ቀናት ውይይት በኋላ ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በመቀጠልም የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጽንፈኝነትን በመቃወም የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በመጪው እሑድ ዕለት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ 

No comments:

Post a Comment