Tuesday, August 27, 2013

ኢሕአዴግ እሁድ በአ.አ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ፤ ድምጻችን ይሰማ “መንግስት ሙስሊሙን እየዘለፈ ነው” አለ

 (ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዛሬ እንደዘገበው “አክራሪዎች በእምነት ስም የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቃወም እሁድ ነሃሴ 27/2005 ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ” ብሏል። በሌላ በኩል ድምጻችን ይሰማ “አክራሪነትን ለመዋጋት ተብለው በተዘጋጁ ስብሰባዎች ጸረ እስልምና የሆኑ ዘለፋዎች እተበራከቱ ነው!” ሲል ተቃውሞውን አሰማ።
ኢሕአዴግ የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ የጠራው ሰልፍ ሁሉም የሀይማኖት ተከታዮች በሰላም አብሮ ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ሲል ድምጻችን ይሰማ በበኩሉ “ለእስልምና ጥላቻ ያላቸው የመንግስት ሃላፊዎችና ካድሬዎች አጋጣሚውን የእስልምናን ሃይማኖት ለማራከስ ተግባር እያዋሉት ነው” ብሎታል።
“ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በእምነት ስም የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ጥረት የሚያደርጉ አካላትን በመቃወም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡” ሲል የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሲዘግብ ድምጻችን ይሰማ በበኩሉ “መንግስት አክራሪነትን ለመዋጋት በሚል እያዘጋጃቸው ባሉ ስብሰባዎች የእስልምና ሃይማኖት ላይ ዘለፋዎች እየተሰነዘሩ ነው፡፡ በየክፍለ ከተማውና ወረዳዎች ለካድሬዎች እና የሀይማኖት አባቶች ተብለው በሚካሄዱ ስብሰባዎች ‹‹የእስልምና ሃይማኖት የአክራሪዎች መፈልፈያ ነው››፣ ‹‹እስልምና የሚባል ነገር ነው ሰላም የነሳን›› ከሚሉ ተነስቶ ሌሎችም በርካታ ስድቦች እና ዘለፋዎች እየተንጸባረቁ ነው፡፡ በተለይ ባለፈው ረቡእና ሐሙስ የአዲስ አበባ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ባዘጋጀውና በስድስት ኪሎ ስብሰባ ማእከል በተደረገው ስብሰባ ሲንጸባርቅ የነበረው ስሜት ሕዝቡ ያወረዳቸው የመጅሊስ ሹመኞችን ጨምሮ ኢማሞችን ሁሉ አንገት ያስደፋ እንደነበር ታውቋል፡፡ ብዙዎችንም የመንግስትን አካሄድ በድጋሚ እንዲያጤኑት የጋበዘ ሆኗል፡፡” ብሏል።


“የሁሉም ሀይማኖት ተከታዩች በተገኙበት የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የሀይማኖት ተከታዮቹ አብሮ በሰላም ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት ቦርድ ሰብሳቢ ርዕሰ ደብር በርሁን አርአያ ገልጸዋል” ሲል ዜናውን ያተተው ኢቲቪ የሀይማኖት እኩልነት ባልተከበረበት ወቅት ጭምር ህዝቡ ጠብቆ ያቆየውን የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ጥቂት አክራሪዎች ለማደፍረስ መሯሯጣቸውን ለመቃወም ሁሉም የሀይማኖት ተከታዮች በዕለቱ እንደሚሳተፉ ርዕሰ ደብር በርሁን አርአያ ጠቁመዋል ካለ በኋላ እሁድ 27/2005 በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የሁሉም ቤተ እምነት መሪዎች እና ተከታዮቻቸው የሰላም መልእክቶችን በመያዝ ከየአቅጣጫው ወደ መስቀል አደባባይ ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል” ሲል ዘገባውን አጠናቋል።
ድምጻችን ይሰማ በበኩሉ “በዚህ በቢሮ ሀላፊው አቶ ጸጋዬ ሀይለማርያምና በደህነነት መስሪያ ቤት ሀላፊዎች በተመራው ስብሰባ የተገኙና ቀድመው ንግግር የሚያደርጉበት አጀንዳ የተሰጣቸው የፓርቲ ካድሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ የእስልምናን ሃይማኖት የሚያራክሱ ንግግሮች ሲያደርጉ ከመታየታቸውም በላይ አንዳንዶች ለእስልምና ያላቸውን ጥላቻ ከመግለጽ ጭምር አንኳ አልተቆጠቡም፡፡ የሱና ምልክት የሚንጸባረቅባቸው አካላትን መንግስት ሊታገላቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት እነዚህ ካድሬዎች የእስልምና ሃይማኖት መንፈሳዊ ተግባራትን ሁሉ የአክራሪነትና አሸባሪነት መገለጫዎች አድርገው ሲፈርጇቸው ተደምጧል፡፡ አቶ ጸጋዬ ኃይለማርያም ከመንግስታዊው ሃይማኖት የማጥመቅ ዘመቻ ጀምሮ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ሲዘልፉና በሙስሊሞች መካከል የልዩነት እሾህ ለመትከል ሲሯሯጡ የቆዩ ግለሰብ እንደሆኑ በድምጽ ማስረጃ ጭምር መጋለፁ ይታወሳል፡፡” ብሏል።
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=6736

No comments:

Post a Comment