-ፓርቲው ከ33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ጋር ተለያየ
በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የተቃውሞ ሠልፍ ያካሄደው ሰማያዊ ፓርቲ፣ በመጪው እሑድ በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተዘጋጀው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ተቃውሞ አቀረበ፡፡
ሁለተኛውንና በርካታ ሰዎች እንዳሚሳተፉበት ሲገልጽ የከረመውን ሰላማዊ ሠልፍ የሚያካሄደው ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደነበር ፓርቲው አስታውቆ፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተደራቢነት በዕለቱ ሠልፍ እንደሚያደርግ ያስተላለፈው ጥሪ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ያስተላለፈውን፣ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነትን እናውግዝ›› የሚል የሠልፍ ጥሪ የተቃወመው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲያስተዋውቅና ጥሪ ሲያደርግ መክረሙን ገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ ቀድሞ ማሳወቅ ለሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ ማስገባቱን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌታሁን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹እኛ በጠራነው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ሌላ ሠልፍ እንዲጠራ መፍቀድ መንግሥት በትንሹ የከፈተውን ቀዳዳ ለመዝጋት ፈልጐ ነው፤›› የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ በተመሳሳይ ቦታና ሰዓት ሰላማዊ ሠልፍ መጥራት ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ እንዳልሆነላቸውና መንግሥት የጉባዔውን ሠልፍ እንዲሰርዝ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት የተጠሩ ሁለት የተለያዩ ዓላማና ይዘት ያላቸው ሰላማዊ ሠልፈኞች ሲገናኝ ወደ ግጭት ሊያመሩ ስለሚችል፣ መንግሥት ፓርቲው ቀድሞ መጥራቱንና ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን በመገንዘብ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ ፓርቲው ነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ መግለጫ ማውጣቱን ኢንጂነር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ ለበርካታ ወራት አንድነት ፓርቲን ጨምሮ ከ33 ፓርቲዎች ስብስብ ጋር ኅብረት ፈጥሮ ሲሠራ የቆየ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ከስብስቡ እንዲወጣ መደረጉ ተሰምቷል፡፡ ከ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብ መገለሉን በሚመለከት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት ኢንጂነር ይልቃል፣ ‹‹የሚያግባባን ነገር ሲገኝ በጋራ ሆነን ለመሥራት ተስማማን እንጂ፣ ማንም ተባራሪና አባራሪ የለም፡፡ መሰብሰባችን በስምምነት እንጂ የሕግ ድጋፍ ኖሮት የተደረገ ስምምነት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሲሰጡ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብና ፖለቲካ የሚመጥን የፖለቲካ ፓርቲ አለ ብለን አናምንም፤›› ማለታቸውና ሰማያዊ ፓርቲ እየጣረ ያለው ክፍተቱን ለመሙላት መሆኑን መናገራቸው ሌሎቹን ማስከፋቱ ይነገራል፡፡
የ33 ፓርቲዎች ስብስብ፣ ‹‹እንዴት እንደሌለን እንቆጠራለን?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ እንደነበር መስማታቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ለምን እንደተናገሩ ጠርተው ሳያናግራቸው ስንቶቹ ተሰብስበውና በስንት ድምፅ ወስነው አብረው መቀጠል እንደማይችሉ ሳይገለጽላቸው ስለመለያየት ማውራት፣ ለእሳቸው የልጆች ጨዋታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ ከወጣን ከ33 ፓርቲዎች ስብስብ ውስጥ ሰው የሚያውቀውና ስሙ የሚታወቅ ፓርቲ ይኖራል እንዴ?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነትን በአደባባይ መናገር ስላልተለመደ እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ለምን ተናገረ?›› በሚል አብሮ አለመሥራትን ማወጅ፣ ሕዝቡን ተስፋ ከማስቆረጥ ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ኢንጂነር ይልቃል ጠቁመዋል፡፡
No comments:
Post a Comment