(ከኢየሩሳሌም አርአያ)
በአባይ ወልዱ የሚመራውና ሰባት ከፍተኛ የሕወሐት ባለስልጣናት የተካተቱበት ቡድን በአሜሪካ አራት ከተሞች
ባካሄደው ስብሰባ በተለይ በላስቬጋስ ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠመው በስፍራው የተገኙ ምንጮች አስታወቁ። ቡድኑ
በዋሽንግተን ኢትዮጲያ ኤምባሲ በጀመረውና በመቀጠል በላስቬጋስ፣ ሲያትልና ካሊፎርኒያ ከተሞች ባካሄደው ስብሰባ
“አላማ” አድርጎ የያዛቸው ጉዳዮች እንደነበሩ የጠቆሙት ምንጮች፣ እነሱም፥ “የመለስ ፋውንዴሽን፣ የአባይ ግድብና
የ40/60 የቤቶች ግንባታ.” ሲሆኑ፣ ለነዚህ ማስፈፀሚያ “ገንዘብ አዋጡ” የሚለው ዋናው ግብ እንደነበር
አስረድተዋል። በተለይ ደግሞ « በትግራይ ተወላጁ ዘንድ ሕወሐት የለም፣ ተከፋፍሏል፣ ተዳክሟል፣ ፓርቲው ሰው
የለውም፤» የሚለውን እራሱ ቡድኑ በማንሳት ለገዛ ጥያቄው መልስ ሲሰጥ « ሕወሐት አሁንም ሃይል አለው፤
አልተዳከመም» በማለት አድራጊ- ፈጣሪ በመሆን ስልጣኑን በበላይነት ተቆጣጥሮ እንደያዘና ቡድኑ የመጣውም
“አይዟችሁ” ለማለት እንደሆነ መገለፁን በቅርብ የተከታተሉት ምንጮች አስታውቀዋል። ቡድኑ በተጨማሪም ፥ «
ልማት አልምተናል፤ ትግራይ እየለማ ነው፤ ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገነው ነው» ከማለቱ ባሻገር « በትግራይ ተወላጁ
ላይ አደጋ ተደቅኗል፤ የሙስሊሙ፣ የትምክህተኞችና የሽብርተኞች አደገኛ እንቅስቃሴ እያንዣበበ መሆኑን፣…
የተደቀነብህን አደጋ ከጎናችን ሆነህ ተከላከል፤ ያለበለዚያ ግን ሊያጠፉህ ነው፤» ሲሉ መናገራቸውን የገለፁት ምንጮች
አክለውም፣ « አባላት የሆናችሁ ተወደደም ተጠላ መሬትና መኖሪያ ቤት እንሰጣችኋለን፤ ለዚህም ከእኛ ጎን መሰለፍ
አለባችሁ» በማለት ሊሸነግሉ መሞከራቸውን ጠቁመዋል።
ከዋሽንግተን ስብሰባ (ለሁለት
ተከፍሎ ነው የተካሄደው) በኋላ
ወደ ሶስቱ ከተሞች ተከፋፍለው
እንደሄዱ ሲታወቅ፥ ሲያትል አቶ
ብርሃነ ማረት፣ እንዲሁም
ላስቬስጋስ አባይ ወልዱና
ተክለወይኒ አሰፋ መሄዳቸው
ታውቋል። በተለይ በላስቬጋስ
ጠንካራ ተቃውሞ የገጠማቸው
እነአባይ ስብሰባው ከቀኑ 2፡00
ሰዓት ይጀመራል ተብሎ ከአራት
ሰዓት በኋላ ዘግይቶ አመሻሽ ላይ
መጀመሩን ምንጮች ገልፀዋል።
ስብሰባው ሲጀመር ከላይ
የተገለፁትን ጉዳዮች ያደመጠው
ተሰብሳቢ ተከታዮቹን ጥያቄ
አቀረበ፤ « ዴሞክራሲ አለ
ትላላችሁ፣ ነገር ግን ዴሞክራሲ
የለም፤ በሃሳብ የሚቃወማችሁን
ታስራላችሁ፣ ታንገላታላችሁ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ ታካሂዳላችሁ፤ ከእናንተ የተለየ ሃሳብ ያለውን ትፈራላችሁ፤ ለምንድነው ይህን ሁሉ የምታደርጉት?….በማ.ረ.ት.(ማህበር ረድኤት ትግራይ) በትግራይ ሕዝብ ስም የምትሰበስቡትን ገንዘብ ለአራጣ ብድር እና ለፖለቲካ መጠቀሚያበመሳሪያነት እያዋላችሁት ነው።
ለምን?….ትእምት (ኤፈርት) ማነው ባለቤቱ?..በማን ነው የሚመራው?..ማነው
የሚቆጣጠረው?..ለመሆኑ ኦዲት ተደርጎ ያውቃል ወይ?..እነማናቸው እየተጠቀሙበት ያለው?» የሚሉት ዋና
ዋናዎቹ ጥያቄዎች እንደነበሩ ምንጮቹ የጠቆሙ ሲሆን፣ አባይ ወልዱ « እኔ አልመልስም፣ ተ/ወይኒ መልስ
ይስጥበት» ቢሉም ነገር ግን ግልፅና አግባብ ያለው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ወደ ማመናጨቅና ቁጣ ያመሩት ተ/ወይኒ
በዚህ ድርጊታቸው በርካታ ተሰብሳቢዎችን እንዳሳዘኑ አስረድተዋል። በዚህ የተበሳጨው ተሰብሳቢ « ጥያቄያችን
አልተመለሰም» በማለቱና ሁከትና ያለመደማመጥ በማየሉ ስብሰባው እንዲቋረጥ መደረጉን የጠቆሙት ምንጮች፣
የጥያቄና ተቃውሞው መብዛት ያስደነገጣቸው ባለስልጣናቱ የመረጡት ማምለጫ በላስቬጋስ ተወካያቸው በሆነውና
መድረክ ሲመራ በነበረው አቶ ተወልደ በኩል፥ « አዳራሹን የተከራየንበት ሰአት አብቅቷል፤ ስለዚህም ስብሰባው
አብቅቷል » በማለት በአስቂኝ ሰበብ መቋረጡን አያይዘው ገልፀዋል። እነአባይ ከአዳራሹ ሲወጡ ቀድሞ ውጭ ሆኖ
ይጠብቃቸው በነበረው ተሰብሳቢ ውግዘትና ስድብ እንደደረሰባቸው ያስታወቁት ምንጮች « ሌባ..ሌባ…ሙሰኞች..»
የሚሉ ተቃውሞዎች ጎላ ብለው እንደተሰሙ አመልክተዋል።
ስብሰባዎቹን የታዘቡ ወገኖች በሰጡት አስተያየት እንዲህ ብለዋል፤ « በአንድ በኩል ልማት እያካሄድን ነው፤ እያሉና
ገንዘብ እየጠየቁ በሌላ በኩል “ትግራዋይ አደጋ ተደቅኖብሃል፣ ከጎናችን ሆነህ ተከላከል፤” ማለት እርስ በርሱ
የሚጋጭና ድጋፍ የማግኛ የፖለቲካ የፖለቲካ ቁማር ነው። ያልተጠየቁትን የፓርቲውን ህልውና (ስለ ሕወሐት)
አንስቶ መነገሩም አስገራሚና አጠያያቂ ነው።» ሲሉ ትዝብታቸውን የጀመሩት እነዚህ ወገኖች በማያያዝም፥ « እነዚህ
ሰባት ባለስልጣናት ወደ አሜሪካ የመጡት ከነዘመዶቻቸው፣ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ሲሆን፣ ባለስልጣናቱ የመንግስት
ወኪሎች እንደመሆናቸው – በማን ገንዝብ ነው የሚንቀሳቀሱት?..የሚለው መጠየቅ አለበት። በሕዝብ ገንዝብ
እየተንፈላሰሱ እንደሆነ ግልፅ ነው። የትግራይ ተወላጁን ብቻ ለይተው ስብሰባ የሚጠሩት ለምንድነው?…በእርግጥ
ስላሰቡለት ነው?…የሚሉት ሲፈተሹ .መልሱ በጭራሽ አይደለም ነው። አላማቸውና ትኩረት የሰጡት የትግራይ
ተወላጁን እየተንከባከቡት እንደሆነና ተጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት በመፈለግ፣ እግረ-መንገዳቸውን ከቀሪው
ኢትዮጲያዊ ወገኑ ጋር በመነጠል..ድጋፍ ለማግኘትና በውስጣቸው የተፈጠረውን ቀውስ በዚህ በኩል ቀዳዳውን
ለመድፈን የሚደረግ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ስልት ነው። ..ደግሞስ ሕወሐት “አጋር” ከሚላቸው ብ.አ.ዴ.ን፣
ኦ.ህ.ዴ.ድ.፣ ደቡብ ሕዝቦች ተለይቶ፣ በሕዝብ ገንዘብ ስብሰባ የሚጠራበትና ያሻውን የሚያደርግበት አግባብ
ምንድነው?..የሚለው ከዚህ ጋር መታየት ያለብት ነው። ፖለቲካዊ ፍጆታና ማንአለብኝነት በፓርቲው በመነገሱ
እንደሆነ ደግሞ ግልፅ ነው።» ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ አሜሪካ ከመጡት ሰባት የሕወሐት ባለስልጣናት መካከል- ማለትም አባይ ወልዱ፣ ብርሃነ ኪ/
ማሪያም፣ ተ/ወይኒ አሰፋና ዳንኤል አሰፋ በዋነኛነት ሲጠቀሱ፣ ከሰባቱ ሶስቱ ስብሰባውን ሳያካሂዱ ከቡድኑ
ተገንጥለው በአሜሪካ መቅረታቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል። ቤተሰቦቻቸውን ይዘው (ልጆቻቸውን ጭምር)
በመምጣት አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀው መቅረትን የመረጡት ባለስልጣናት ውስጥ የሕወሐት ማ/ኮሚቴ አባላት
እንዳሉ ያረጋገጡት ምንጮች በቅርቡ ዝርዝሩን ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment