Friday, September 6, 2013

የጋራ ንቅናቄው ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንደሚቆም አስታወቀ

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ነሐሴ 30፤ 2005ዓም
የጋራ ንቅናቄው ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን ይቆማል!
የወጣት አመራሮቹን ሰላማዊ የትግል መስመር ይደግፋል!
ያለፈው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጠርቶ በነበረው የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ በህወሃት/ኢህአዴግ የተወሰደውን ጽንፈኛ፣ አክራሪና አጸያፊ የውንብድና ተግባር የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ይኮንናል፤ ያወግዛል፡፡ ፓርቲው ሰልፉን ለማካሄድ ከሁለት ወራት በፊት ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ቅዳሜ ነሐሴ 25፤2013 የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነት አባላት የፓርቲውን ጽ/ቤት ጥሰው በመግባት የፈጸሙት ተራ የውብንድና ተግባር ብቻ ሳይሆን የህወሃት/ኢህዴግን ማንነት በግልጽ ያሳየ ለመሆኑ ከማንም በላይ ተግባሩ ራሱ ምስክር ነው፡፡
በዕለቱ እንደሆነው የህወሃት/ኢህአዴግ አሸባሪ ፖሊሶች የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤትን ከመውረራቸው በፊት ኤሌክትሪክ መስመሩን ቆርጠዋል፡፡ በቀጣዩም ለእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ዝግጅት እያደረጉ የነበሩትን አመራሮችና ፈቃደኛ ሠራተኞችን ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ከደበደቡና ካሰቃዩ በኋላ ለሰዓታት አስረዋቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ከተፈቱ በኋላ ለእሁዱ ስብሰባ ተመልሰው ዝግጅት እንዳያደርጉ የህወሃት/ኢህአዴግ አሸባሪዎች የፓርቲዉን ጽ/ቤት እስከ እሁድ ድረስ በመቆጣጠር ኮምፒውተሮችን፣ የጽህፈት መሣሪያዎችን፣ ሠንደቅዓላማዎችን፣ መፈክሮችን፣ … በማውደም፤ የሚፈልጉት በመውሰድ ሰልፉ እንዳይካሄድ አድርገዋል፡፡ ይህንን ተግባር የሚመሰክር ከበቂ በላይ የፎቶግራፍ፣ የሰው፣ … ማስረጃ ቢኖርም ህወሃት/ኢህአዴግ ሁሉንም በመካድ ለዓለምአቀፍ ሚዲያ አንዳች ነገር እንዳልተደረገ በመናገር የተለመደውን ዓይን ያወጣ ቅጥፈት ደግሟል፡፡

ጥያቄው ግን ሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ ያሉ ቁርጠኛ ወጣቶች ያነሱት ይህ የመብት ጥያቄ ለምን ህወሃት/ኢህአዴግን ለምን አሸበረው? ለምንስ እንዲህ ያለውን ራሱን የሚያጋልጥ ተግባር እንዲፈጽም አደረገው? መልሱ ህወሃት/ኢህአዴግ ልምድ በሌለውና በማያውቅበት የሰላማዊ ትግል ጠንክረው ስለመጡበት ብቻ ነው! ለዚህ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል በጽናት መብታቸውን ለማስከበር የሚታገሉት ሙስሊም ወገኖቻችንና ሰሞኑን በአንድነት ፓርቲ የተጀመረው ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ማስረጃዎች ናቸው፡፡
ህወሃት/ኢህዴግ ባስቀመጠው ትዕዛዝ መሠረት የሰማያዊ ፓርቲ ለእሁዱ ሰልፍ ከሁለት ወር በፊት ደብዳቤ አስገብቶ ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሰሞን ህወሃት/ኢህአዴግ ባቀናበረው የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ “አሸባሪነትንና አክራሪነትን” ለማውገዝ ሕዝቡ ሰልፍ እንዲወጣ ጥሪ አድርጎ ነበር፡፡ በጥሪ ብቻ ያላበቃው ዘመቻ የከተማው ነዋሪ በግድ፣ በማስፈራራት፣ በጉቦ፣ … ሰልፍ እንዲወጣ የተቀናበረም ነበር፡፡ ይህ ሰልፍ በሚካሄድበት ቀን ታቅዶ የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ትዕይንተሕዝብ ካልተጨናገፈ በስተቀር ህወሃት/ኢህአዴግ በጠራው በራሱ ሰልፍ ላይ የሚደርስበት ክስረት መራራ እንደሚሆን ግልጽ ነበር፡፡
ከሰልፉ ጥሪ በፊት በተካሄደው ጉባዔ ወቅት “በኢትዮጵያ ህዳሴ የሃይማኖቶች ተስማምቶ መኖር” አስፈላጊነት የተሰበከ ሲሆን ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ “የሃይማኖት አክራሪነትን” እንዲያጋልጡ ተሰብሳቢዎቹን በመጠየቅ መንግሥት በዚህ ዙሪያ የሚወስደውን እርምጃ አንደሚቀጥልበት አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ቅዳሜ በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት የተፈጸመው ተግባር አሸባሪና አክራሪ ራሱ ህወሃት/ኢህአዴግ መሆኑን ያጋለጠበት ነው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ ያገባኛል በማለት ጉባዔ የሚጠራው ህወሃት/ኢህአዴግ፤ “በሃይማኖታችን ጣልቃ አትግባ፤ የራሳችንን መሪዎች እንምረጥ፣ መብታችን ይከበር” በማለት ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል እየጮሁ ያሉትን ሙስሊም ወገኖቻችን የመብት ጥያቄ መመለስ ያልፈለገ ወይም ያልቻለ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን የራሱን ካድሬዎች በሃይማኖት መሪነት ሽፋን በመሾምና ሙስሊሙን ኅብረተሰብ በመከፋፈል የአፈናና የመብት ረገጣ ተግባሩን ቀጥሎበታል፡፡ ይህ የህወሃት/ኢህአዴግ አሠራር በሌሎች ሃይማኖቶችም የቀጠለ ለመሆኑ በሃይማኖት ተቋማት ስም የተጠራው ጉባዔና ሰልፍ በቂ ምስክር ነው፡፡
ህወሃት ገና ከጥንስሱ የሃይማኖት ጉዳይ የማይስበው፤ በበረሃው ቆይታ በተደጋጋሚ በአሸባሪነት ተግባር ላይ ለመሠማራቱ የተመሰከረለት መሆኑ፤ ራሱን በፈጣሪ የለሽ የሌኒኒስታዊ ፍልስፍና ያጠመቀ መሆኑ ራሱ የመሰከረውና በግልጽ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ አሁን “በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉዳይ ያገባኛል፤ የሃይማኖት አክራሪነትን እታገላለሁ” ማለቱ ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ የአህያ ቁርበት አንጥፉልኝ ያለው ዓይነት ነው፡፡
በአመሠራረቱ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክለው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ካሉት “የድምጻችን ይሰማ” ሙስሊም ወገኖች፣ የአንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ፣ የሰማያዊ ፓርቲና ሌሎች ወገኖች ጋር ያለውን ኅብረት ይገልጻል፡፡ የጋራ ንቅናቄው ባለው ዓለምአቀፋዊ ዕውቅናና ግንኙነት በመጠቀምም የህወሃት/ኢህአዴግን ቋት ለሚሞሉት ለለጋሽ አገራት፣ ለሕግ ተቋማት፣ ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ለሚዲያ ተቋማት፣ ወዘተ በአገራችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የመብት ረገጣ ያሳውቃል፡፡ የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ እስካሁን የፈጸመውን የሽብር ተግባርና ወደፊት ለሚያደርሰው ማንኛውም በደል በቀጥታ ተጠያቂ እንዲሆን መረጃው በሕግ ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡
በአገራችን በ1997 የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በሟቹ ጠ/ሚ/ር ቀጥተኛ ትዕዛዝ ህወሃት/ኢህአዴግ የፈጸመው የ193 ዜጎች ግድያ፣ የፖለቲካ መሪዎች እስር፣ አፈና፣ የመብት ረገጣ፣ … ያስከተለውን ፍርሃት ለመጀመሪያ ጊዜ በመግፈፍ የፖለቲካ ትዕይንተሕዝብ ያደረገው የሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ “ድምጻችን ይሰማ” የሚያደርጉት በትክክለኛ የሰላማዊ ትግል መርህ ላይ የተመሠረተው እልህ አስጨራሽና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ትግል እንዳለ ሆኖ የሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴም ከዚህ ጋር አብሮ ተጠቃሽ ነው፡፡
አርቆአሳቢና ራሳቸውን በሰላማዊ ትግል ዲሲፒሊን ያነጹ ወጣቶች ተሰባስበው በሰማያዊ ፓርቲ ሥር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሰላማዊ ትግል በትክክለኛው መንገድ ከተከናወነ በኢትዮጵያ እንደሚሠራ በተግባር ያስመሰከረ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን “ሰላማዊ ትግል ከኢትዮጵያ የፖለቲካ አንጻር አይሠራም” የሚለውን ስሜታዊ አስተሳሰብ ከሥሩ የመታ ትግል በመሆኑ የጋራ ንቅናቄው ለሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችንና አመራሮች ከፍ ያለውን አድናቆት ይሰጣል፡፡ በተለይም በሰላማዊ ትግል መስመር ስማቸው በዓለም የሚጠራው መሃትማ ጋንዲ፣ ዶ/ር ኪንግ፣ ማንዴላ፣ … በወጣትነታቸው ይህንን ዓይነቱን የትግል መስመር ከመምረጣቸው አኳያ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች የተጠና እንቅስቃሴና የዓላማ ጽናት ሌሎችም የእናንተን መስመር እንዲከተሉ የሚያደፋፍር እንጂ በምንም ዓይነት መልኩ የያዛችሁትን እርግጠኛ አቋም እንድትመረምሩ ሊያደርጋችሁ እንደማይገባ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በአጽዕኖት ያስታውቃል፡፡ ለመስከረም 12፤ 2006 ዓ.ም. የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ሁሉም ሰላም ወዳድ ወገኖች ድጋፋቸውን እንዲሰጡት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ከዚህ በፊት በሊቢያ በቅርቡ በግብጽ አሁን ደግሞ በሶሪያ ሕዝብን እያስተላለቀና እጅግ ደም እያፋሰሰ ያለውን ዕልቂት ተመልክታችሁ አገራችሁን በምንም ዓይነት መልኩ ወደ ደም መፋሰስና ዕልቂት እንዳትገባ የሚደርግ ሰላማዊ የትግል መስመር መምረጣችሁ የጋራ ንቅናቄው ምስክርነት የሚሰጠው ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ከየትኛውም የአመጽና የሽብር ተግባር ጋር በግድ በማያያዝ ሊኮንናችሁ፣ ሊወነጅላችሁ፣ ወዘተ ቢሞክርና ወደፊትም ይህንኑ ለማድረግ ቢያስብ እስካሁን የፈጸማችሁት ሰላማዊ ሥራችሁና የትግል ስትራቴጂያችሁ በገሃድ የሚመሰክረው ከመሆኑ ባሻገር የጋራ ንቅናቄው ዓለም ሁሉ ይህንን ምስክርነት እንዲያውቅ በማስረጃነት የሚያስመዘግበው ነው፡፡
ትክክለኛውን የትግል መርሆ የተከተለ ሰላማዊ ትግል ከዚህ በፊት የሠራና አሁንም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ መተግበር እንደሚችል ጠንቅቆ ያወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ፤ በሰላማዊ የትግል መስመር የሚነሱትን ሁሉ ገና በእንጭጩ ሲቀጭ ቆይቷል፡፡ ተስፋ በማስቆረጥ፣ በመከፋፈል፣ በማሰር፣ በማሰቃየት፣ በመግደል፣ ወዘተ የፓርቲ አመራሮችን ያስወግዳል፤ ትግሉ ወደ ተራው አባል ከመዝለቁና አባሉ በራሱ አመራርና የትግሉ ባለቤት መሆን ከመቻሉ በፊት ይበታትናል፡፡ ይህንን የሚያደርገው ከባህርይውና ከለመደው የደም ማፍሰስ አገዛዝና ትግል ውጪ ያለ አካሄድ ሥልጣኑን ስለሚያናጋውና መጨረሻውን ስለሚያቃርበው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የትግል መስመር ተጠናክሮ ወደ ሙሉ ህዝባዊ እንቅስቃሴና እምቢተኝነት ከተቀየረ ህወሃት/ኢህአዴግ መመከት የማይችልበት ደረጃ ስለሚደርስ ህልውናው ያከትማል፡፡ “ሥልጣን ወይም ሞት” በማለት የፖሊስና የመከላከያ ኃይሉን እስካፍንጫው በማስታጠቅ ዕድሜውን እየገፋ ያለው ህወሃት/ኢህአዴግን ወደ ሙሉ ህዝባዊነት የተቀየረ ሰላማዊ ትግልን መቆጣጠርም ሆነ ማጨናገፍ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ሰላማዊ ትግል በህዝቡ ዘንድ በሙላት ሳይሰርጽና መርሆዎቹ ተግባራዊ ሳይሆኑና ገና በጅምሩ ማጥፋት፣ ማውደም፣ ማሰቃየት፣ ወዘተ የሚፈልገው፡፡ በወጣቶች የተገነባው የሰማያዊ ፓርቲ ላይ እየረደሰ ያለው ሁኔታ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን የሚታገል እንደመሆኑ በሰላማዊ የትግል መስመር ላይ ያሉ ድርጅቶችንም ሆነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ይደግፋል፤ ያበተረታታል፡፡ በሰላማዊ የትግል መስመር የሚመጣ ለውጥ በአገራችን ያለማቋረጥ ሲፈስ የቆየውን የደም ጎርፍ እንዲቀጥል፤ ቂምና በቀል እንዲስፋፋ፤ መጪውን ትውልድ በፍርሃትና በማያቋርጥ የደም መፋሰስ አዙሪት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ሳይሆን፤ በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ዕርቅ እንዲሰፍን፤ የአንዱን ነጻነት ብቻ የሚያስከብር ሳይሆን “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም” በሚል የጠነከረ ምሶሶ ላይ የሚገነባ ነው፡፡ በአገራችን ለዓመታት የተረጨውንና እስከ ቤተአምልኮዎች የዘለቀውን የዘር ፖለቲካና የዘረኝነት አመለካከት ማምከን የምንችለው በሌላ መንገድ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ” እንስጥ የሚለውን ታላቅ መርህ ከፍ ስናደርግ እንደሆነ የጋራ ንቅናቄው ያምናል፡፡ ይህንን አመለካከት ከሚጋሩ ሁሉ ጋር በጋር ይሠራል፤ ይንቀሳቀሳል፡፡
በአገራችን ላይ እስካሁን በበሽታ፣ በረሃብ፣ በድህነት፣ በእርስበርስ ጦርነት፣ … ብዙ ደም ፈስሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የምንሄድበት መንገድ ይህንኑ እንዲቀጥል የሚያደርግ በጭራሽ ሊሆን አይገባውም፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግም ይህንኑ ሊያስተውልና “በለመድኩት የአፈና አካሄድ እቀጥላለሁ” ከሚለው ዕብሪተኛ አስተሳሰቡ ሊመለስ ይገባዋል፡፡ በውስጡ ያሉት የትግራይ ተወላጆችም ይሁኑ ሌሎች የአገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን በግልጽ የሚወጡበትና የህወሃት/ኢህአዴግ አሠራርን በግልጽ በመተቸት ሁላችንም ወደ ዕርቅ የምንመጣበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ሥርዓቱ “ከእንጥሉ መበስበሱን” ሟቹ ጠ/ሚ/ር የመሰከሩለት በመሆኑ ምንም የሚደበቅ ነገር ስለሌለ ጉዳዩን ይፋ ለማውጣት የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡ የጋራ ንቅናቄው ይህንን የጥሪ ደወል እስካሁን ሲያሰማ ቆይቷል፤ አሁንም ይህንኑ ይደግማል፡፡ ሆኖም ይህ በህወሃት/ኢህአዴግ ውስጥ ላሉትና ለመሰል ድቃይ ድርጅቶች የምንሰጠው “ከሥርዓቱ ተለዩ” የሚለው ጥሪ የሚያቆምበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ምላሽ የመስጫው ጊዜ ነገ ወይም አንድ ቀን ሳይሆን ዛሬ፤ አሁን ነው፡፡ የአፈናና የጭቆና ሥርዓት ጸንቶ አይቆይም፡፡ እንኳን እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ ያለው ዘረኝነትን መመሪያው፤ የአገር ውርደት ክብሩ የሆነ አገዛዝ ይቅርና በህዝባዊነታቸውና ብሔረተኝነታቸው የተመሰከረላቸው አገዛዞችም ጨቋኝ በመሆናቸው ብቻ እንደማይነሱ ሆነው ወድመዋል፤ ፈርሰዋል፡፡
ፈጣሪ ሁላችንንም የማስተዋልና ትክክለኛውን መንገድ የመምረጥ ጥበብ ይስጠን፡፡ የልቦና ዓይናችንን ከፍቶ የዘረኝነትን፣ የጥፋትን፣ የብቀላን፣ የውድመትን አስከፊነት እንድናስተውልና የሰላምንና የዕርቅን መንገድ እንድንመርጥ ይርዳን፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የመረጣችሁትን ሰላማዊ መንገድ በምንም አትቀይሩት፤ ከእርሱ የሚበልጥም ሆነ የሚሻል መንገድ የለምና!! ሌሎች የእናንተን ዓይነት መንገድ አስቀድመው ከጀመሩ ጋር በኅብረትና በመቻቻል ሥሩ፡፡
ለውጥ በአገራችን ይመጣል! ይህ የማይቀር ሃቅ ነው! ኢትዮጵያ ነጻ ትወጣለች፤ ነጻ የምትወጣው ግን በሌላ ነጻ አውጪ ሳይሆን “ነጻ አውጪ ነኝ” የሚለውን ጭምር ነጻ በሚያወጣው እውነትና ፍትህ ነው፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=7108

No comments:

Post a Comment