መስከረም ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ካለፉት 8 ቀናት ጀምሮ ስብሰባ ላይ ሲሆኑ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ታውቋል።
ሰሞኑን በመካሄድ ላይ ባለው ከጄኔራል በታች ማእረግ ባላቸው መኮንኖች ስብሰባም የደሞዝ ጭማሪና የኑሮ ውድነት ዋና አጅንዳ ሆኖ ቀርቧል።
በምስራቅ አካባቢ ባለው እዝ አንዳንድ መኮንኖች ” እኛ ቤተሰቦቻችንን ምግብ አብልተን ለማኖር አልቻልንም፣ እናንተ በሙስና በዘረፋችሁት ገንዘብ ልጆቻችሁን ውጭ አገር ልካችሁ ታስተምራላችሁ” በሚል አለቆቻቸውን በድፍረት መተቸታቸውን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል። መኮንኖች ያቀረቡትን ጥያቄ የመደረክ መሪዎች ለመመለስ ሲቸገሩ ታይቷል።
መኮንኖቹ ስብሰባቸውን ሲጨርሱ ከተራ ወታደሮች ጋር የሚደረገው ስብሰባ ይቀጥላል ተብሎአል።
ከፍተኛ ቅሬታ እየተስተናገደበት ባለው ስብሰባ፣ ወታደሮቹ እንደ መኮንኖቹ ሁሉ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ወታደራዊ ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ሻምበል የወለደውን ልጅ በእሳት ማቃጠሉ ታውቋል። በምስራቅ እዝ የሚገኘው ሻምበል ፈቃዱ በዳዳ ከሳምንታት በፊት በልጁ ላይ ቤንዜን በማርከፍከፍ ያቃጠለው ሲሆን፣ ልጁም ወዲያውኑ ህይወቱ ሲያልፍ አባቱ ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል ተኝቷል። ሻምበል ፈቃዱ በልጁ ላይ ይህን አሰቃቂ እርምጃ ለምን እንደወሰደ አልታወቀም።
No comments:
Post a Comment