Tuesday, September 17, 2013

ከአሶሳ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ አውቶቡስ ተገልብጦ 6 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

(ዘ-ሐበሻ) ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ የአንበሳ ጊቢ ጠባቂ በአንበሳ የመበላቱና የመሞቱ ዜና ሲያሳዝነን ውሎ የነበረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ከወደ አሶሳ ሌላ አሳዛኝ ዜና ተሰማ። ከአሶሳ ወደ አዲስአበባ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎችን ይዞ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ተገልብጦ 6 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ከአዲስ አበባ የመጡ ዜናዎች ገለጹ።
ይህ የመኪና አደጋ የደረሰው መስከረም 7 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 12:30 እንደሆነ ሲታወቅ አውቶብሱ ከአሶሳ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኝ ኩርባ መንገድ ላይ ሲደርስ አቅጣጫውን ስቶ 20 ሜትር በሚደርስ ጉድጓድ ውስጥ በመግባቱ አደጋው መከሰቱን የከተማው ትራፊክ ፖሊስ ማስታወቁ ተዘግቧል።
በዚህ አደጋ ወደ 16 የሚጠጉ ወገኖች ምንም ዓይነት አደጋ ያልደረሰባቸው መሆኑን ያስረዳው ዘገባው የ6ቱ ተሳፋሪዎች ሕይወት ግን ወዲያውኑ አልፏል። ፖሊስ ለአደጋው መነሻ የአሽከርካሪውን በፍጥነት መንዳት እንደምክንያትነት ሲጠቅስ አሽከርካሪውን አስሮ በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቋል ሲል ከአዲስ አበባ የመጡ ዜናዎች ገልጸዋል።

ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም የሚከተለውን ዘግባ ነበር፡-
በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የ2012 ሪፖርት መሰረት በዓለማችን በዓመት 1ሚሊየን 3 መቶ ሺ ህዝብ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ሲታወቅ በኢትዮጵያ በተደረገ ጥናት ደግሞ በዓመት ክ2000 ሰዎች በላይ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያልፋል።
ለመኪና አደጋ መንስኤ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በፍጥነት ማሽከርከር፣ ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ የሌሊት ጉዞ፣ ደርቦ ማለፍ፣ ከአቅም በላይ መጫን፣ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምና ጠጥቶ ማሽከርከር ከመንስኤዎቹን መሀል ዋነኞቹ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ጉድለት ወይም ብልሽት፣ የእግረኛ ግራ መንገድ ይዞ አለመሄድና የማቋረጫ ምልክቶችን (ዜብራ) በአግባቡ አለመጠቀም፣ የመንገዶች በጥራት አለመሰራትና የመንገድ ላይ ምልክቶች ተሟልተው አለመዘጋጀት ለአደጋው እንደመንስኤ የቀረቡ ናቸው፡፡

Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=7447

No comments:

Post a Comment