ታሪኳ ለማ፣ በጉዲፈቻ አሜሪካ የተወሰደችው ጉብል
በአሁን ጊዜ በዓለም ላይ ኢትዮጵያን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ከሚያስነሳት ጉዳይ አንዱ ጉዲፈቻ ነው፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች አሳዳጊ የሌላቸው ተብለው የሚታሰቡ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ወደ ተለያዩ አገሮች ይሄዳሉ፡፡ ‹‹የተሻለ ሕይወት›› ይኖራቸዋልም በሚል እሳቤ ቤተሰብ ያላቸውን ሕፃናትም ሕገወጥ በሆነ ሰርቆ መስጠት እንዲሁም በደላሎች አማካይነት የሚሠሩ ሥራዎችም እንዳሉበት በርካታ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ሲኤንኤን መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ያወጣው ይህንኑ አስከፊ እውነታ የሚመሰክር ነው፡፡
ታሪኳ ለማ የ19 ዓመት ዕድሜ ያላት ወጣት ናት፡፡ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ነበር ከሁለት ታናናሽ እህቶቿ ጋር ትምህርታቸውን በአሜሪካ እንደሚከታተሉና ትምህርት በማይኖርበት በማንኛውም የዕረፍት ጊዜ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ እየመጡ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያዩ ቃል ተገብቶላቸው እናት አገራቸውን የለቀቁት፡፡
ዛሬ ማይኒ የምትኖረው ታሪኳ ለማ የኮሌጅ ተማሪ ስትሆን፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ የመሆን ህልም አላት፡፡ በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ተወስደው ስላለፉት የሕይወት ውጣ ውረድ እንደሚከተለው ተርካዋለች፡፡
‹‹የተሸጥኩት አሥራ ሦስት ዓመቴ ላይ ነበር፡፡ ከቤተሰቤ ተሰርቄ የተወሰድኩት፡፡ እኔና እህቶቼን ለትምህርት ወደ አሜሪካ ሊልከን እንደሚገባ አባቴን ያሳመኑት የአባቴ ጓደኞች ነበሩ፡፡ እኤአ በ2006 በተገባልን የሐሰት ቃል ኪዳን ወላጅ አባቴን አሞኝተው እንድንሄድ ተገደድን፡፡ ይህንን የሚያደርጉት የአባቴ ጓደኞች በሙስና እጃቸው የተጨማለቀና አጭበርባሪ የጉዲፈቻ ወኪል ውስጥ የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ይህም ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡
‹‹አባቴም ሆነ እኛ ስለ ጉዲፈቻ የምናውቀው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ወላጅ አባታችን የላከን ለትምህርት፣ እኛም ለመማር እንደመጣን ነበር የምናውቀው፡፡ እውነታው ግን የተገላቢጦሹን ሆኖ ነበር ያገኘነው፡፡ ዋሽተውናል፤ የዋሹት ግን እኛን ብቻ ሳይሆን በጉዲፈቻ የወሰዱንን አሳዳጊ ቤተሰቦቻችንን ጭምር ነበር፡፡ ያመጣንላችሁ ወላጆቻቸውን በኤድስ ያጡ ሦስት ሕፃናትን ነው፤ ትልቋ ዘጠኝ ዓመቷ ነው ብለው ነበር ሴራውን ያቀነባበሩት፡፡ ይሁንና እውነታው ግን እኔ የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊ ነበርኩ፡፡ የቤተሰቤም የበኩር ልጅ ነኝ፡፡ ታናሾቼ የአሥራ አንድና የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎች ነበሩ፡፡
‹‹አዲሶቹ ‹ቤተሰቦቻችን› ስማችንን ቀየሩትና በአፍ መፍቻ ቋንቋችን በአማርኛና በወላይትኛ ማውራት እንደማንችልና ካወራንም ቅጣት እንደሚጠብቀን አስጠነቀቁን፡፡ እናም በስተመጨረሻ አፍ በፈታንበት ቋንቋ መናገር ተሳነን፤ እስከነ አካቴውም ረሳነው፡፡
‹‹በጣም ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ከዚህ ካለሁበት የእሥር ቤት ሕይወት ጠፍቼ ብወጣ ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ተመልሼ የምገባ ይመስለኝ ነበር፡፡ እነኚህ ቀጣፊዎች ከትውልድ አገሬ፣ ከባህሌና ከቤተሰቤ እንደነጠሉኝ ሳስበው ውስጤ በሐዘንና በምሬት ይሞላል፡፡
‹‹ከስምንት ወራት በኋላ ከእህቶቼ ተነጥዬ ወደ ሌላ ቤት እንድጓዝ ተደረግኩኝ፡፡ አዲሱ መኖሪያዬ የተደረገው ከአሳዳጊ እናቴ ቤተሰቦች ጋር ነበር፡፡ ያም ወደ መካከለኛው ምዕራብ ነበር፡፡ እህቶቼን ለመጐብኘት የታደልኩት በጣት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ነበር፡፡ አሁን ባለሁበት አገር መኖር ይከብዳል፡፡ ከአገሬ ኢትዮጵያና ከእህቶቼ ተነጥያለሁ፡፡ አጋጣሚዎች ክፉ ቢሆኑብኝም እጅ መስጠት አልፈለግኩም፡፡ ያለኝን አቅም ሁሉ አሰባስቤ ከአገር ውጪ በሚደረግ ጉዲፈቻ ምን ዓይነት ብልሹ አሠራርና የሰው ልጆች ንግድ እየተካሄደ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ ወሰንኩ፡፡
‹‹ከአገር ውጪ የሚደረግ ጉዲፈቻን የሚያበረታቱ አካላት 151 ሚሊዮን ወላጅ የሌላቸው ታዳጊዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ወላጅ ያጡ ሕፃናት 18 ሚሊዮን ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ከእናት ወይም ከአባት ጋር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ወላጅ የሌለው ብሎ መጥራት እጅግ የሚከብድ ነው፡፡ እኔ ወላጅ አልባ አይደለሁም፡፡ በእርግጥ እናቴ ሞታለች፤ ነገር ግን አባት አለኝ፣ እህቶች ወንድሞች እናም ሌሎች የሚወዱኝና የሚናፍቁኝ ቤተሰቦች አሉኝ፡፡
‹‹ውሸቱም ሆነ ማጭበርበሩ ለገንዘብ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ዛሬ ዛሬ ለገንዘብ ሲሉ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናት መፍጠር ጀምረዋል፡፡ ለዚህም የገንዘብ ክፍያ አላቸው፡፡ ክፍያውም ከአገር አገር ይለያያል፡፡ ከፍ ዝቅ ይላል፣ ነጭ ሕፃን በጉዲፈቻ ለመውሰድ የሚከፍሉት ክፍያ ከፍ ያለ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የጥቁር ዝቅ ያለ ነው፡፡ ተመልከቱ ምን ያህል አስከፊ ሕይወት እንደሆነ፡፡
‹‹ዛሬ ውጣ ውረዶች ጠንካራ አድርገውኛል፡፡ ይህም በሕይወቴ አንድ ጥሩ ነገር እንድሠራ አነሳስቶኛል፡፡ በጉዲፈቻ ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት እየሠሩ ያሉትን ንግድ የሚያጋልጥ መጽሐፍ በመጻፍ ላይ እገኛለሁ፡፡ ወደ አገሬም ለመመለስ የሚበቃኝን ገንዘብ እያጠራቀምኩ ነው፡፡ በቅርቡም ወደ ፍርድ ቤት በመሄድም ትክክለኛ ስሜን ለማግኘት እሞክራለሁ፡፡››
source: minilik-salsawi
No comments:
Post a Comment