Saturday, September 21, 2013

ከሚሊዮን ብር በላይ ለአረጋውያን ያወረሱ ኢትዮጵያዊት

  Written by  መንግሥቱ አበበ http://www.addisadmassnews.com

ከሚሊዮን ብር በላይ  ለአረጋውያን ያወረሱ ኢትዮጵያዊት ባለፈው ረቡዕ ነው - የዘመን መለወጫ ዕለት፡፡ ሁዋዌ የተባለው የቻይና ቴክኖሎጂ ግሩፕ የኢትዮጵያ ቢሮ፣ ለክብረ አረጋውያን ምግባረ ሰናይ ድርጅት የተለያየ ቁሳቁስ ስጦታ ሲያበረክትና የምሳ ግብዣ ሲያደርግላቸው፣ ስጦታውን ከተረከቡት መካከል ሲ/ር ዘመናዊት ታዬ አንዷ ነበሩ፡፡ ሲ/ር ዘመናዊት ከአረጋውያኑ ጋር አብረው እየኖሩ በሙያቸው የመጀመሪያ ዕርዳታ ይሰጣሉ፡፡ ሲ/ር ዘመናዊት ቤታቸውን አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ብር ሸጠው፣ ከአረጋውያኑ ጋር እየተጦሩ መሆኑን ሰማሁ፡፡ የሰማሁትን ማመን ከበደኝ፡፡ እውነት መሆኑን ለምን ከአንደበታቸው አልሰማም ብዬ አነጋገርኳቸው፡፡ የሰማሁት ነገር እውነት ነው፡፡ ሲ/ር ዘመናዊት አሁን የ76 ዓመት አረጋዊት ናቸው፡፡ ጎንደር ተወልደው እዚያው ነው ያደጉት፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ አዲስ አበባ መጥተው የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በያኔው እቴጌ መነን፣ በዛሬው የካቲት 12 አጠቃላይና መሰናዶ ት/ቤት ተማሩ፡፡ 12ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ፣ ነርሲንግ ለመማር ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል (የዛሬው ጦር ኃይሎች ሆስፒታል) ገቡ፡፡
ተመርቀው ትንሽ እንደሠሩ፣ በ1952 ዓ.ም ከክቡር ዘበኛ ጦር ጋር ኮንጐ ዘመቱ፡፡ እዚያ አንድ ዓመት ቆይተው ሲመለሱ፣ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አንድ ዓመት ከሠሩ በኋላ አሜሪካ ሄዱ፡፡ አሜሪካ ዋሽንግተን ኮሎምቢያ ሆስፒታል ፎር ውመንስ በተባለ ሆስፒታል በሙያቸው ለአምስት ዓመት ሠርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድም ለሶስት ዓመት ሠርተዋል፡፡ ከአሜሪካ እንደተመለሱ በምኒልክ ሆስፒታል ለአንድ ዓመት ሠሩ፡፡ ከዚያም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተዛውረው፣ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ለ25 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ሲ/ር ዘመናዊት፣ የረር አካባቢ በ280 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ጥሩ ቤት ነበራቸው፡፡ ባለቤታቸው ሞተዋል፤ ልጆችም የላቸውም፡፡ ከወንድማቸው ልጅ ጋር ነበር የሚኖሩት፤ እሱም ሞተ፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ከንቱ ሆነባቸው፡፡
ለብዙ ጊዜ ካሰቡበት በኋላ በመጨረሻ ቤታቸውን ለክብረ አረጋውያን ምግባረ ሰናይ ድርጅት አወረሱ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ከአረጋውያን ጋር መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት ከአራት ወር ሆኗቸዋል፡፡ የድርጅቱ መሥራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ ሙኒኤ፤ ሲ/ር ዘመናዊት ያወረሷቸውን ቤት 1.1 ሚሊዮን ብር ሸጠው፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር በሰጣቸው ቦታ ላይ ለአረጋውያኑ ቤት ሠርተው ከ15 ቀን በኋላ እንደሚገቡበት ገልጸዋል፡፡ “ሲ/ር ዘመናዊት ታዬ ትርፍ ቤት ሳይኖራቸው አንድ ቤታቸውን ለአረጋውያን በማውረሳቸው በጣም የማደንቃቸው ሴት ናቸው” ብለዋል፤ ወ/ሮ ወርቅነሽ።

2 comments:

  1. egzabher mengset smyaten yawershachew melkamne maderge mnhe yaklhe bezhe meder yasedesetalhe!!!!

    ReplyDelete
    Replies
    1. Amen, yetmwerk ewnet new melkam madreg kemanmbelay le ras erkatan yestal yetchgruten degmo yetadgachwal, thank you for your postive comment sis. keep in touch

      Delete