Sunday, September 29, 2013

“መስቀል የሚያቃጥል (አይደለም)”

ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ሲኖዶሡ ውሣኔ ይሰጣል - አቡነ እስጢፋኖስ

abune estifanos

በአቃቂ ቃሊቲ ገላን ጉራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ እስኪያስተላልፍ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ የአዲስ አበባና የጅማ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አሣሠቡ፡፡ “መስቀል ከሠማይ ወርዷል አልወረደም? ትክክለኛ ነው አይደለም?” የሚለውን ለመመለስ የግድ ቅዱስ ሲኖዶሡ ጉዳዩን መርምሮ ውሣኔ ሊያስተላልፍበት ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ይህን ለማድረግም ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቋሚ አባላት እንዳሣወቁ ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ እንደተባለው ከሠማይ የወረደ አለመሆኑ ከተረጋገጠም የቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች ይጠየቁበታል ብለዋል-ብፁዕነታቸው፡፡
መስቀሉ ከሠማይ ወረደ በተባለ በ4ኛው ቀን ነሐሴ 27 ቀን 2005 ከሠአት በኋላ ወደ ስፍራው በማቅናት ተገቢውን የፀሎት ስርአት ከካህናቱና ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋር ካደረሡ በኋላ መስቀሉን ከወደቀበት መሬት አንስተው ወደ ቤተመቅደሡ እንዲገባ ማድረጋቸውን የገለፁት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ መስቀሉ ከሠማይ ስለመውረዱ በአይናችን አይተናል ካሉት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደማንኛውም ሠው መስማታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት መሬት ያነሱት ብፁዕነታቸው፤ “መስቀሉ ያቃጥላል፤ ብርሃናማ ነፀብራቅ አለው” የሚባለውን አለማስተዋላቸውን ጠቁመው፤ “መስቀል የሚያቃጥል ሣይሆን የድህነት ሃይል ነው ያለው፣ የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ ከመሬት ላይ ማንሣት ባልተቻለ ነበር” ብለዋል፡፡ ወረደ የተባለውን መስቀል ለመመልከት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ምዕመናን ለምን እንዳይመለከቱት ተከለከለ የሚል ጥያቄ ያነሣንላቸው ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶሡ ተጣርቶ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያጤነው በማሠብ ነው” ብለዋል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)

No comments:

Post a Comment