Friday, September 27, 2013

በ10 ቀናት ውስጥ አንድ ባለ አንድ ፎቅ ተገነባ

መስከረም ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ሕንጻ ግንባታ እና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት ከጀርመኑ ባዉሃዉስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዊመር እና ከደቡብ ሱዳኑ ጁባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከሶስቱም ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ተማሪዎች አማካይነት 10 ቀናት ውስጥ  የባለ አንድ ፎቅ ተገጣጣሚ ሕንጻ ገነባ፡፡
ይህ በዓይነቱ አዲስ የሆነውን ቴክኖሎጂ በነገው ዕለት ይፋ ለማድረግ ፕሮግራም ተይዞአል፡፡ ቴክኖሎጂው በተለይ በጀርመን አገር የሚሰራበትና ጊዜና ወጪን በመቆጠብ ረገድ ወደር የሌለው ነው ተብሎለታል፡፡

በልደታ አካባቢ በሚገኘው የቴክኖሎጂ ፋክልቲ በነገው ዕለት በሚካሄደው የማስተዋወቂያ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የውጭ አገር አምባሳደሮችና  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎአል፡፡የአዲስአበባ የቤቶች ልማት ድርጅት በዚህ ቀላል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የከተማዋን የቤት ችግር የሚቀርፍበት አንድ አማራጭ ይሆናል ተብሎ የተገመተ ሲሆን ድርጅቱም ለቴክኖሎጂው ስኬት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ታውቆአል፡፡

No comments:

Post a Comment