(ኢትዮ-ምኅዳር ቅጽ 01 ቁጥር 34፤ ረቡዕ ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋራ በመተባበር በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ከነሐሴ ፳፩ – ፳፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ‹‹የሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር እሴት በማጎልበትና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የሀገራችንን የሕዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባኤ ላይ ‹አቦይ› ስብሐት ነጋ በመገኘት አነጋጋሪ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ አንጋፋው የህወሓት/ኢሕአዴግ መሥራችና የጀርባ ሰው የሚገልጹት ሐሳብ የመንግሥትን ቀጣይ ርምጃ ያመላክታል በሚል በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አክራሪነት ይዘቱ ሃይማኖታዊ እንዳልኾነ ሕዝቡም የተገነዘበው ጉዳይ መኾኑ ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ ሃይማኖትን የፖሊቲካ መድረክ የሚያደርጉት የሽብርተኝነት ተግባር ለመፈጸም መኾኑ ግልጽ የኾነልን ይመስለኛል፡፡
አክራሪነትና ጽንፈኝነት በሃይማኖት ውስጥ ማስገባት የመጀመሪያው አደጋ ሲኾን በዚህ ኹኔታ ሃይማኖቱም ሃይማኖት አይኾንም፡፡ አማኞች፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት በየሃይማኖታቸው ውስጥ ሲታይ ሃይማኖታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡
አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን (የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ) እንዳለውም፣ በጣም አስደናቂ የኾነውን የኢትዮጵያ ዕድገት ማደናቀፍ ከማንኛውም ወንጀል በላይ በሕዝብ ላይ ከባድ ወንጀል መፈጸም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዓመታት ሲሠቃይ የነበረ በመኾኑ አሁንም ሕዝቡን ለሥቃይ መዳረግ ተወዳዳሪ የሌለው ወንጀል ነው፡፡
በማንኛውም ሃይማኖታዊ አክራሪነት እና ጽንፈኝነት፣ በምንም ዐይነት ኹኔታ አንድም ሰው ለአንድ ደቂቃ እንኳ ተዘናግቶ መተኛት የሌለበት ሲኾን በተለይ ይህን ነገር በጥብቅ በሁሉም መንገድ መታገል አለብን፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ዕድገት የሚቀናቀነው የውጭ ተቀናቃኝ ነው፡፡ የእነዚህን ተቀናቃኞች ዓላማ በመያዝ በአክራሪነትና በጽንፈኝነት መልክ ታላቅ ክሕደት መፈጸም ከባድ አገራዊ ክሕደት ነው፡፡ የውጭ ጠላት ቀላል ስላልኾነ አንድም ሰው ሳይቀር በጣም ተጠናክረን መመከት ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ የፖሊቲካ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ዝንባሌ ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥቱ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጸደቀው የራሱ ሕገ መንግሥት ስለኾነ ሕዝብ በመራራ ትግል ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት መጣስ የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ነው፡፡
በዚህ ስብሰባ ከፍተኛ ግንዛቤ መያዙ በጣም የሚያስደስት ነው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ተስፋ ነው፡፡ ለውጭ ጠላት ደግሞ ሲጠብቀው የነበረ ብጥብጥ መቅረቱ ሕዝብን የሚያስደስት፣ ጠላትን ደግሞ የሚያሳፍር ነው፡፡
ሌላው ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተነሣ ነበር፡፡ አንድ አባታችን ካነሧቸው ብዙ ነገሮች አንዱ፣ ‹‹መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጁን ያስገባል›› የሚል ነው፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ በእስልምናም ይኹን በኦርቶዶክስ እጁን አያስገባም፡፡ በዚህ ጉዳይ የመጀመሪያ ተጠያቂው እምነቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሰጠው መብት ሲጣስ፣ መንግሥት እጁን ሲያስገባ ለምን ዝም አለ? ለሕገ መንግሥታዊ መብቱ ለምን አልታገለም? ሁለተኛው ተጠያቂ ደግሞ መንግሥት ይኾናል፡፡
ስለዚህ በሩን ከፍቶ ሲያንቀላፋ መንግሥት እጁን ካስገባበት እምነቱ ይጠየቃል፡፡ ይኹን እንጂ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት እጁን እንዳላስገባ መቶ በመቶ አምናለኹ፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ሰዎች ግን እጃቸውን አስገብተው ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መመከት ነበረበት፡፡ በመጀመሪያ ተጠያቂው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ራሱ ሲኾን እጃቸውን ያስገቡ ሰዎች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ ይኾናሉ፡፡
ሁለተኛ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ወጣት*የተነሣ ሐሳብ አለ፡፡ አክራሪነት አደጋ ነው ብሏል፡፡ በኋላ በእስልምና ሃይማኖት አካባቢ በአንዳንድ ሰዎች የሚታየው አክራሪነት አደጋ ነው፤ ዋናው ግን በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተቀበረው ፈንጅ ነው ትልቁ የአክራሪነት አደጋ ብሏል፡፡ አክራሪነት ማለት እምነቱን ለፖሊቲካ ጥቅም ማዋል፣ እምነቱን ለፖሊቲካ ጥቅም ክፍት ማድረግ ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ማኅበራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የፖሊቲካ መድረክ እያደረጓት ነው፤ ማኅበሩ** እንኳ ባይኾን አንዳንድ ሰዎች ብሎ ጠቅሷል፡፡ ይህን ተጠንቅቆ ያቀረበው ይመስለኛል፡፡ ማኅበሩ ነው አክራሪ ወይስ በማኅበሩ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ናቸው? መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ማኅበር ያሉ አንዳንድ ሰዎች ማኅበሩ ጤናው የተበከለ እንዳይኾን ማጣራት፣ ተጠንቅቆ መያዙ፣ እንደተባለው ፈንጅ ከኾነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ወጣቱ* እና ዶክተር ሽፈራው ተክለ ማርያም (የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር) ሁለቱም ከባድ የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
እንደተባለው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በእውነት የፖሊቲካ መድረክ እየኾነች ከኾነ፣ በዚህ አገር የትኛው አክራሪነት ነው ከተባለ፣ ትልቁ አደጋ ያለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነው የተባለው ትክክል ነው ወይስ ትክክል አይደለም የሚለው መጣራት የሚኖርበት ቢኾንም በሁለቱ ሰዎች የተጠቆመው ግን የሚያስተኛ አይደለም፡፡ ከእምነቱ ቦታ የኾንም መተኛት የለብንም፤ የሌሎች እምነት አማኞችም መተኛት የለባቸውም፡፡
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=7086
No comments:
Post a Comment