Saturday, September 7, 2013

መኢአድ የእስር፣ የድብደባና የወከባ ጥቃት ደረሰብኝ አለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
የወረዳ ካቢኔ ባለስልጣናት በወረዳው ፍ/ቤት መቶ መቶ ብር ተቀጥተዋል
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፣ በደቡብ ክልል 45 አባላት፣ በቤኒሻንጉል ሁለት እንዲሁም በአፋር ሰባት አባላት እንደታሰሩበት ገልፆ፣ መሬት የተነጠቁ ከመቶ የፓርቲው አባላት ክስ አቅርበው የወረዳ ባለስልጣናት ቅጣት ቢወሰንባቸውም የገበሬዎቹ መሬት እንዳልተመለሰ ሰሞኑን ተናገረ፡፡ 
በአዲስ አበባ መኢአድን እንዲሰልሉ የተጠየቁ አባላት ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡ 
በደቡብ ክልል ጐፉ ዞን መብታቸው እንዲከበር የጠየቁ 35 ነዋሪዎች፤ በሰኔ ወር አጋማሽ ታስረው እየተሰቃዩ ናቸው ብሏል - መኢአድ፡፡ 
ከዚህም በተጨማሪ 104 ነዋሪዎችና አባላት የእርሻ መሬታቸውን በህገወጥ መንገድ በወረዳ ካቢኔ ሹሞች እንደተነጠቁ መኢአድ ገልፆ፣ ተበዳዮች ፍትህ ለማግኘት ለወረዳ ፍ/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን አውስቷል፡፡ የካቢኔ ሹሞች መቶ መቶ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል የሚለው መኢአድ፣ የተበዳዮቹ የእርሻ መሬት ግን አልተመለሰላቸውም ብሏል፡፡ 
መሬት የተነጠቁ ገበሬዎች በግዳጅ ከብት እየሸጡ ማዳበሪያ እንዲገዙ እየተደረገ ነው ሲልም አውግዟል መኢአድ፡፡ 
በቤንች ማጂ ዞን እስከ ነሐሴ ወር ድረስ መሬታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ የታዘዙ የጉራፋርዳ ወረዳ ነዋሪዎች፤ “ህፃናት ልጆቻችንን ይዘን በክረምት የት እንውደቅ?” በማለት ጥያቄ በማቅረባቸው ድብደባና እስር እንደተፈፀመባቸው መኢአድ ገልጿል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ ዘጠኝ ሰዎችን በስም ዘርዝሮ ያቀረበው መኢአድ፤ ሦስት ሰዎች መሬታቸውን ለማስመለስ ሁለት ሺ ብር እንዲከፍሉ ታዝዘዋል ብሏል፡፡ 
በሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ ወረዳዎች በርካታ የመኢአድ አባላት ፓርቲውን ለቀው እንዲወጡ ከዛቻና ማስፈራሪያ በተጨማሪ ድብደባ እንደደረሰባቸው የገለፀው መኢአድ፤ የሰባት ተበዳዮችን ስም ጠቅሷል፡፡ ሦስት አባላትም ከስራ እንዲባረሩ መደረጋቸውን ፓርቲው አውግዟል፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ በቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል የመኢአድ አባላት አቶ አህመድ ደረሰ እና አቶ ተስፉ ሞረዳ ታስረው እንሚገኙ መኢአድ ገልፆ፣ በሌሎች አባላትና ተወካዮች ላይ ዛቻና ድብደባ እየተፈፀመ ነው ብሏል፡፡ 
በምስራቅ ኢትዮጵያ አፋር ክልል፣ በሳይታ ወረዳ ሳታስፈቅዱ መሬት አርሳችኋል የተባሉ ነዋሪዎች፤ በሃምሌ ወር አጋማሽ ታስረዋል በማለት አቶ ኑር ያሲንና አቶ ሙዲ አበራን ጨምሮ የሰባት ሰዎችን ስም ዘርዝሯል - መኢአድ፡፡ 
በአዲስ አበባ አምስት የመኢአድ አባላት ፓርቲውን እንዲሰልሉ በደህንነት ሠራተኞች አማካኝነት እንደተጠየቁና እምቢተኛ በመሆናቸው ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው በስም ጠቅሶ ይገልፃል - መኢአድ፡፡

No comments:

Post a Comment