- አመራሩ በታገደበት ቆይቶ የኑፋቄ ውዝግቡ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል
- አመራሩ ኑፋቄው በአግባቡ እንዳይጣራ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ሲፈጥር ቆይቷል
- ብዙኀኑ የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት በውሳኔው ቃለ ጉባኤ ላይ አልፈረሙም
- ‹‹ከዚህ በኋላ ለሚፈጠረው ችግር ሓላፊነቱን የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ይወስዳል፡፡›› /ሰበካ ጉባኤው/
በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሕዋስ በመጠለፉና በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ለሰበካ ጉባኤው መመሪያ ባለመገዛቱ የመዘጋት ርምጃ የተወሰደበት የድሬዳዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት እንዲከፈትና ነባሩም አመራር እንዲቀጥል የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ በድምፅ ብልጫ ወስኖ ያስተላለፈውን መመሪያ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር እንደማይቀበለው አስታወቀ፡፡
‹‹የሃይማኖት ጉዳይ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በሊቃውንትና ካህናት ጉባኤ እንጂ በአስተዳደራዊ መንገድና በድምፅ ብልጫ አይወሰንም›› ያሉት የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ ውዝግቡ ከሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ውጭ በገለልተኛ ጉባኤ እንዲታይ አልያም ሰበካ ጉባኤውንና ማኅበረ ካህናቱን ከታገደው የሰንበት ት/ቤቱ አመራር ጋራ አቀራርቦ በማነጋገር፣ ጥፋተኛውን በመለየትና በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ እንዲፈታ አሳስበዋል፡፡
የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ለሀ/ስብከቱ ውሳኔ ምላሽ ለመስጠት ነሐሴ ፲፰ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ እንደተገለጸው÷ ከግማሽ በላይ የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት አጣሪም ወሳኝም ኾነው በተሳተፉበትና በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሕዋስ የተጠለፈው የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር ችግር በግልጽ በታወቀበት ኹኔታ በድምፅ ብልጫ የተላለፈው ውሳኔ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፤ የታገደውን አመራር የተሳሳቱ ሐሳቦችም የሚደግፍ ነው፡፡
የሰበካ ጉባኤው የተቃውሞ ውሳኔ እንደሚያብራራው የሰንበት ት/ቤቱ አመራር÷ በኑፋቄ በመጠርጠሩ ከሓላፊነትና አባልነት ታግዶ ማጣራት እየተካሄደበት ለሚገኘው ሊቀ መንበሩ ጥብቅና በመቆም ማጣራቱ በአግባቡ እንዳይከናወንና እንዲድበሰበስ አባላቱን ለዐድማና ዐመፅ በማንቀሳቀስና የዐውደ ምሕረት አገልግሎት እንዲያቆሙ ያለፈቃዳቸው በማስገደድ ጫና ፈጥሯል፤ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ከሰበካ ጉባኤው የሚሰጠውን መመሪያ ‹‹ሰበካ ጉባኤ አያዘንም›› በሚል አይቀበልም፤ በካቴድራሉ የሚደቡለትን መምህራን ይንቃል፤ ካህናቱን ያቃልላል፤ አባላቱም ከማኅበረ ካህናቱ ጋራ በአባትና ልጅ መንፈስ እንዳይተያዩ እየቀሰቀሰ በካቴድራሉ ከፍተኛ ብጥብጥና ንትርክ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
አመራሩ በዚህ አካሄዱ እንዲቀጥል ከተፈቀደለት የዐመፅና ብጥብጥ ተግባሩን እያሰፋ የሚሄድ በመኾኑ፣ በኑፋቄ በተጠረጠረው የሰንበት ት/ቤቱ ሊቀ መንበር ላይ በጉባኤ ካህናት የሚካሄደው ማጣራት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ጽ/ቤቱን የማሸግ፣ አመራሩንም ከሓላፊነት የማገድ ርምጃ መወሰዱ ተገልጧል፡፡ የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ በአጣሪ አካሉ አማካይነት ይህን የሰንበት ት/ቤቱን አመራር ችግርና ከመመሪያ ውጭ መኾን አረጋግጦ ሳለ ባለጉዳዮችን አቀራርቦ ለማነጋገር እንኳ ሳይሞክር የታሸገው ሰንበት ት/ቤት እንዲከፈትና የነበረው አመራር እንዲቀጥል መመሪያ መስጠቱ አግባብነት እንደሌለው የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ በተቃውሞ ውሳኔው ገልጧል፤ ከዚህ በኋላም ለሚፈጠረውም ችግር ሓላፊነቱ የሀ/ስብከቱ እንደሚኾን አሳስቧል፡፡
ሰበካ ጉባኤው በደረሰበት የጋራ አቋምና ስምምነት መሠረት የታገደው የሰንበት ት/ቤቱ አመራር የአስተዳደሩን መመሪያ ካለመቀበል ባሻገር ለካቴድራሉ አገልጋይ ካህናትና መምህራን ያለው አመለካከት ዝቅ ያለና ምንም እንደማያውቁ የሚቆጥር በመኾኑ፣ የሚመደቡለትንም መምህራን በቀናነት ስለማይመለከት እንዲቀጥል ሊፈቀድለት አይገባም፤ ሓላፊነቱን ማስረከብና በአዲስ ሥራ አመራር መተካት ይኖርበታል፡፡ በመኾኑም የሀ/ስብከቱን ውሳኔ ተቀብሎ ለማስፈጸም እንደሚቸገርና ጉዳዩ ከአስተዳደር ጉባኤው አባላት ውጭ በኾነ ገለልተኛ አካል ዳግመኛ እንዲታይ ጠይቋል፡፡
የሀ/ስብከቱ ምንጮች በበኩላቸው፣ በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አማካይነት ለካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ የተላለፈው መመሪያ ሰባት አባላት ያሉት የሀ/ስብከቱ አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የአስተዳደር ጉባኤው አባላት ተወያይተው ውሳኔ ያሳለፉበትን ቃለ ጉባኤ ተመልክተው ሳይፈርሙበት በችኮላ የወጣ ነው፤ በውሳኔያቸውና በተላለፈው መመሪያ መካከል ልዩነት በመኖሩ በድምፅ ብልጫ ተወስኖበታል በሚባለው መመሪያም አይስማሙም፤ ከሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከካህናት አስተዳደር ክፍል፣ ከልማት ክፍል እና የሰንበት ት/ቤቱን አመራር ከጠለፈው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሕዋስ አንዱ ናቸው ተብለው ከሚጠረጠሩት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል ሓላፊው በቀር የሚበዙት ሓላፊዎች በቃለ ጉባኤው ላይ አለመፈረማቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሰንበት ት/ቤቱን ለመታሸግ፣ አመራሩን ለመታገድ ያበቃው የኑፋቄ ውዝግብ የተቀሰቀሰው የሰንበት ት/ቤቱ ሊቀ መንበርና በሰበካ ጉባኤው የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹‹ያለወላዲተ አምላክ አማላጅነት ዓለም አይድንም የሚለው አባባል የማይሞች ነው›› ብሎ ማስፈሩን ተከትሎ ነው፡፡ ተቃውሞው በዚያው በፌስቡክ ገጽ ላይ ትችታቸውን በሰነዘሩ የካቴድራሉና ሌሎች አጥቢያዎች ሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ሰባክያንና ካህናት ተጀምሮ ሲስፋፋ ሊቀ መንበሩ በሰበካ ጉባኤው ውሳኔ ታግዶ ጽሑፉ የሰፈረበት ኹኔታ እንዲጣራ እየተደረገ ሳለ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር አባላት በሙሉ ‹‹የእርሱ አቋም/ሐሳብ ሐሳባችን ነው›› በማለታቸው ለውዝግቡ መጠናከር መንሥኤ ኾኗል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት የውዝግቡ መንሥኤ ወይም አጋጣሚ ይህ ይኹን እንጂ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር ከዚህም ሥር በሰደደ የጥርጥር ማዕበል የተመቱ መኾናቸውን ይመሰክራሉ፡፡ ለዚህም የቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ማርያም እና የክብረ ቅዱሳን አስተምህሮ ‹‹የዐጤ ዘርዐ ያዕቆብ ሸክም ነው››፤ ‹‹በቀጥታ ኢየሱስን እንጂ የምን ዙርያ ጥምጥም እንሄዳለን››፤ ‹‹ኦርቶዶክስ ባለሥልጣን እንጂ ሊቅ የላትም›› ማለታቸውን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
No comments:
Post a Comment