Sunday, January 19, 2014

የጄነራል ኤሌክትሪክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዲስ አበባ ይመጣሉ

የአሜሪካ ኩባንያ የሆነው ግዙፉ ጄነራል ኤሌክትሪክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄፈሪ ኢሜልት በቅርቡ ለጉብኝት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ታወቀ፡፡ 
ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጄፈሪ ኢሜልት ከሁለት ሳምንት በኋላ በአፍሪካ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክና ናይጄሪያን ይጎበኛሉ፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ እንደሚጀምሩ የገለጹት ምንጮች፣ በአዲስ አበባ ከከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል ልማትና በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ውይይት ያካሂዳሉ ብለዋል፡፡ ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት እንደሚፈራረም የገለጹት ምንጮች፣ የፕሮጀክቱን ምንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ 

ጄኔራል ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራና የሰብ ስቴሽን ግንባታ ላይ ለመሳተፍ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍም ተካፋይ ለመሆን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ 
ጄኔራል ኤሌክትሪክ በዓመት 150 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያለው ትልቁ የአሜሪካ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ኩባንያው በዘርፍ የተከፋፈሉ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች በማምረት ይታወቃል፡፡ በኢነርጂ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮች፣ የውኃና ንፋስ ተርባይኖች፣ በአቪዬሽን መስክ የአውሮፕላን ሞተሮች፣ ወርልፑል ማቀዝቀዣና የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ በጤናው ዘርፍ የተለያዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም ድፍድፍ ነዳጅ ከመሬት ውስጥ የሚስቡ ማሽኖችና ባቡሮችን በማምረት ይታወቃል፡፡ 
ጄኔራል ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የጠነከረ ግንኙነት አለው፡፡ ለአየር መንገዱ የተለያዩ ሞተሮች የሚያቀርብ ሲሆን፣ የድሪምላይነር አውሮፕላኖች በሙሉ ‹‹ጂኢ›› በመባል የሚታወቁ ሞተሮች የተገጠሙላቸው ናቸው፡፡ በቅርቡም የሞተር ጥገና አገልግሎት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ 
ሚስተር ኢሜልት በኢትዮጵያ በሚያደርጉት የአንድ ቀን ቆይታ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ በኢኮኖሚ ቀውስ ከተመቱ በኋላ ጄኔራል ኤሌክትሪክ ለአፍሪካ ትኩረት መስጠት እንደጀመረ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ኩባንያው በናይጄሪያ ለበርካታ ዓመታት በነዳጅ ዘይት ማውጫ ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን በሞዛምቢክ፣ በአንጐላና በኬንያ በስፋት ይሠራል፡፡ በኬንያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከሦስት ዓመት በፊት ሲከፍት፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ከሰባት ወራት በፊት ከፍቷል፡፡ ይህም ኩባንያው ለአፍሪካ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል ምንጮች፡፡ 
ኩባንያው በአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት መክፈቱና ዋና ሥራ አስፈጻሚው የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ለመምጣት ማቀዳቸው፣ ምን ያህል ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ይላሉ ምንጮች፡፡ 
 

No comments:

Post a Comment