Sunday, January 19, 2014

ለመንግሥት አቤቱታ ያቀረቡ የቻይና ኩባንያዎች ምላሽ ተሰጣቸው

-ገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አስጠነቀቀ
መንግሥት ከቻይና የፋይናንስና የኮንስትራክሽን ድርጅቶች የቀረበለትን ቅሬታ ተቀብሎ እንደሚያስተካክል ቃል በመግባት፣ ችግር ፈጥረዋል ያላቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፡፡ 
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የቻይና መንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ለሆኑት ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (ኤግዚም ባንክ) እና ቻይና ኤክስፖርት ክሬዲት ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን (ሲኖሹር) በቅርቡ በላከው ደብዳቤ፣ ተፈጠረ የተባለውን ችግር ለማስተካከል ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ የግዥ ሥርዓት እንደሚዘረጋና የመሠረተ ልማት ተቋማት ኮንትራት አስተዳደር አሠራር እንደ አዲስ እንደሚያዋቅር ገልጿል፡፡ 

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ በቅርቡ በጻፉት ደብዳቤ፣ አዳዲስ የቻይና ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሥራ የሚያገኙበትን አሠራር መንግሥት እንደሚያመቻች፣ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ያላቸው የቻይና ኩባንያዎችም ግልጽ በሆነ የጨረታ አካሄድ ሥራ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያለ ጨረታ ሥራ የሚሰጠው ልዩ ክህሎት ለሚጠይቁ ግዢዎችና ጥናት አጥንተው ወደ ሥራ ለመግባት ፍላጎት ላላቸው ኩባንያዎች ብቻ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ 
እነዚህን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር በዘርፉ ሥልጣን የተሰጠውን የመንግሥት ንብረት አስተዳደርና ግዢ ኤጀንሲ አቅም እንደሚገነባና የመሠረተ ልማት ተቋማት የሆኑት የኃይል፣ የመንገድ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የኬሚካል፣ የስኳርና የቴሌኮም ተቋማትን የኮንትራት አስተዳደር ለማሻሻል በዓለም አቀፍ ተቋም ጥናት እየተጠና መሆኑ ታውቋል፡፡
ሁለቱ የቻይና የገንዘብ ተቋማትና 18 የቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በቅርቡ ለኢትዮጵያ መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ፣ አዳዲስ የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸው ነበር፡፡ በተለይ ቀደም ብለው የገቡ የቻይና ኩባንያዎች ከተወሰኑ ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች ጋር በመመሳጠር አዳዲስ ኩባንያዎች ሥራ እንዳያገኙ እንቅፋት መሆናቸውን፣ መንግሥትም፣ ችግሩን ተገንዝቦ የእርምት ዕርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በቅርቡ አዲስ አበባ ለጉብኝት የመጡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መክረዋል፡፡ መንግሥት ለቻይናውያኑ ቅሬታ ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ በወቅቱ ቃል መግባቱ ተገልጿል፡፡ 
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከዚህ በመነሳት ለቻይና መንግሥትና ኩባንያዎች ዝርዝር ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠቱም ባሻገር፣ አንዳንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በመውቀስ ማስተካከያ እንዲያደርጉ መመርያ መስጠቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
በቅርቡ ለሁለት ተከፍለው ራሳቸውን በቻሉ ሁለት ኢንተርፕራይዞች በመዋቀር ላይ የሚገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኮንትራት አስተዳደር ደካማነት ተወቅሷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሥራ አፈጻጸማቸው ደካማ ለሆኑ ኩባንያዎች ሥራ በመስጠቱ ምክንያት፣ ተስፋ የተጣለባቸው ፕሮጀክቶች ደካማ አፈጻጸም ባላቸው ኩባንያዎች እጅ እንዲወድቁ በመደረጉ ፕሮጀክቶቹ በታለመላቸው ጊዜ ውስጥ እየተጠናቀቁ አይደሉም ተብሏል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለተመሳሳይ ኩባንያዎች ሥራ እየተሰጠ ከመሆኑም በላይ፣ ሥራ ያገኙት ኩባንያዎች ሌሎች ኩባንያዎችን እየገፉ በብቸኝነት የኮርፖሬሽኑን ሥራ እየተቆጣጠሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኮንትራት አስተዳደር ጥንካሬው ባይታማም፣ በአማካሪ ድርጅት መረጣ ላይ ወቀሳ ቀርቦበት የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ መመርያ እንደተሰጠው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለቻይና ኮንትራክተር ለሰጠው መንገድ የቻይና አማካሪ እንደሚቀጥር ተገልጾ ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ከሚጠቀሱት መካከል ከአዲስ አበባ አዳማ እየተገነባ ያለው የፍጥነት መንገድና ከድሬዳዋ ደወሌ ድረስ የተፈረመው የመንገድ ፕሮጀክት ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል፡፡ 

No comments:

Post a Comment