Thursday, January 16, 2014

በትግራይ አፅቢ ግጭት ተፈጠረ(ድርድሩ አልተሳካም፡ ተኩስ ተከፍቷል! ህዝብ ተደበደበ!)

ሃሙስ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 08/05/06 ዓ.ም ከቀኑ 11:30 ጀምሮ፤ በትግራይ ክልል፤ አፅቢ ወንበርታ ወረዳ (ጣብያ ሩባ ፈለግ ቁሸት ሕኔቶ) በህዝብና አስተዳዳሪዎች መካከል (በውኃ አጠቃቀም ምክንያት) በተፈጠረ አለመግባባት ሃይለኛ አምባጓሮ ተፈጥሯል። ፖሊሶች ተኩስ ከፍተዋል (ከ11:30 እስከ 11:40 ሰዓት ባለግዜ ለሰላሳ ሰባት (37) ግዜ ተተኩሷል)። ምልሻዎች በተጠቀቅ ይገኛሉ። የመንግስት የሚድያ ሰዎች ሂደቱ እየቀረፁት ነው። የቆሰለ ወይም የሞተ ሰው ስለመኖሩ ወይም አለመኖሩ በግርግሩ ምክንያት ለማወቅ አልተቻለም። ተኩሱ እየቀጠለ ነው። አብርሃ ደስታ ከትግራይ ያቀረበውን ተጨማሪ መረጃ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ህዝብና አስተዳዳሪዎች መካከል ባጋጠመ ግጭት ፖሊስ ቢተኩስም ችግሩ ከፖሊስ አቅም በላይ በመሆኑ፤ አሁን አስተዳደሩ የመከላከያ ሰራዊትን እርዳታ ጠርቷል። አሁን የመንግስት ምልሻዎች በአከባቢው እየተሰማሩ ይገኛሉ። በግጭቱ የተሳተፈውነዋሪ ህዝብ ከሺ በላይ ይሆናል። እስካሁን ድረስ የነዋሪው ህዝብ ተወካዮች የነበሩ አራት ሰዎች የት እንደገቡ አይታወቅም። ፖሊሶች ህዝቡን ለመበተን ሃይል ቢጠቀሙም ህዝቡ ግን አራቱ ተወካዮቹ ካልተለቀቁ ላለመበተን አድማ መቷል። ህዝብ እየተሰባሰበ ነው። (የተኩስ ድምፅ በስልክ አስደምጠውኛል)።
በኋላ ላይ… በአፅቢ ወንበርታ በተከፈተው ግጭት የመንግስት ፖሊሶች ተኩስ መክፈታቸው፣ አርሶአደሮች መደብደባቸው፣ እንዲሁም አራት የኗሪዎቹ ተወካዮች በሃይል አስረው ወዳልታወቀ አከባቢ በመውሰዳቸው፤ ህዝቡ በምላሹ (የአካባቢው ምልሻዎች ሳይቀሩ) አስራ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የመንግስት ምልሻ ከበው አግተው ይዟቸው ቆይተዋል። አራቱ የህዝቡ ተወካዮች እስካልተለቀቁ ድረስ ፖሊሶቹ እንደማይለቀቁ የአርሶ አደሮቹ ተወካዮች አሳውቀው ነበር። አሁን በተደረገ ድርድር “አራቱ ተወካዮች ይፈታሉ፣ በህዝቡ ታግተው የነበሩ አስራ ሁለት ፖሊሶችም ይለቀቁ” ተብሎ ህዝቡ ያገታቸውን ፖሊሶች ለቅቆ፤ የአራቱን ሰዎች መለቀቅ እየተጠባበቀ ይገኛል። ፖሊሶቹ ተለቀዋል፤ አራቱ ገብሬዎች እስኪፈቱ ድረስ ግን እዛው ይቆያሉ። መከላከያ ሰራዊት ጥሪ ቢቀርብላቸውም (እስከ ምሽቱ 1:30) ባከባቢው አልደረሱም።
ፖሊሶች አራት የነዋሪዎቹን ተወካዮች በሃይል ሲወስዱ የአፅቢ ህዝብም አስራ አራት ፖሊሶችና አንድ ምልሻ አግተው ነበር። ህዝቡ ፖሊሶቹ እንዲለቅ አስተዳደሩ ደግሞ አራቱ ተወካዮች እንዲለቅ ድርድር ተጀምሮ ነበር። በድርድሩ መሃል የወረዳው አስተዳደር አዲስ ሃይል በመጥራት (ከሌላ ወረዳና ከክልል አስተዳደር የፀጥታ ሃይሎች በመላክ) ህዝብ በተሰበሰበብት መተኮስ ጀመሩ (ከምሽቱ 2:30-2:56)።
ምልሻዎቹና ወታደሮቹ የታገቱትን ፖሊሶች ለማስለቀቅ እስከ ሁለት መቶ (በነዋሪዎቹ ግምት መሰረት) የሚደርስ ጥይት በመተኮስ የታገቱት ፖሊሶችን ማስለቀቅ ችለዋል። እስከ ሁለት ሺ የሚጠጋ ህዝብ ተሰብስቦ እየጮኸ ይገኛል። (ከምሽቱ ሦስት ሰዓት) ብዙ ምልሻዎች የጫኑ ብዙ መኪኖች ወደ አከባቢው እየገቡ ነው። በሌላ አቅጣጫ (በስተ ሰሜን በኩል) ደግሞ ሌሎች ብዙ መኪኖች እየገቡ ነው (ምልሻ ወይ ፖሊስ ወይም ወታደሮች መሆናቸው ግን በትክክል አይታወቁም)።
ዘግባውን ከትግራይ ያደረሰው አብርሃ ደስታ እንዳለው ከሆነ፤ “ህዝብ በዱላ መደብደብ ጀምረዋል። ህዝቡ እየጮኸና ፈጣሪው እየለመነ ነው። የህዝቡ ጩኸትና ለቅሶ በስልክ መስማት ችያለሁ። እያናግሩኝ ያሉ ሰዎችም መረጋጋት ተስኗቸዋል።” ብሏል።
ዘገባው እስከ ከምሽቱ 3:05 ከቀጠለ በኋላ እንደገና ቀጥሏል።
ታግተው የነበሩ የመንግስት ፖሊሶች ሌሎች ፖሊሶችና ምልሻዎች በከፈቱት ተኩስ ተለቀዋል። አሁን ህዝቡና የመንግስት ምልሻዎች በሜትሮች ርቀት ተለያይተው ማዶ ለማዶ ይተያያሉ። የአፅቢ ወንበርታ ተወላጆች የሆኑ የመንግስት ምልሻዎች የመንግስት አካላትን ከድተው ከህዝቡ ጎን ተሰልፈዋል (ከአንድ ምልሻ በስተቀር ሁሉም የአፅቢ ወንበርታ ምልሻዎች ከህዝቡ ጎን ይገኛሉ)። ሁለቱም ምልሻዎች (የአፅቢ ወንበርታና አስተዳደሩ ከሌላ ወረዳ ያስመጣቸው) ተፋጠዋል። አሁን 3: 15 በደራ ጣብያ ገብረኪዳን ልዩ ስሙ “አፅገበት” የሚባል ቦታ የነበሩ ወታደሮች (መከላከያ ሰራዊት) ባከባቢው ደርሰዋል። እስካሁን ምንም ዓይነት እርምጃ አልጀመሩም። ፀጥታ ሰፍነዋል። ህዝቡ ግን እንደተሰበሰበ አለ። “ተወካዮቻችን ፍቱልን” እያለ ይገኛል። አሁን ከምሽቱ 3:24 ነው።
በሰባት መኪኖች ሙሉ ተጭነው ወታደሮች ገብተው አከባቢው ተቆጣጥረውታል። “የዞን አስተዳዳሪዎች ነን” ያሉ ባለስልጣናት ህዝቡ “የአሸባሪነት ተግባር” እያከናወነ መሆኑ በርቀት ተናግረዋል። ህዝቡም “አሸባሪዎች እናንተ ናች ሁ፤ ልጆቻችን ፍቱልን” እያለ ሲጮህ ነበር። በመጨረሻም ወታደሮቹ ህዝቡ እንዲበተን ማስጠንቀቅያ ቢሰጡም አራቱ የአፅቢ ወንበርታ ልጆች ካልተፈቱ እንደማይበተን አስታውቀዋል። መከላከያውና አስተዳዳሪዎቹ ቢያስፈራሩም ህዝቡ ግን ለመበተን ፍቃደኛ አልሆነም።
ዘጋባውን ያቀረበው አብርሃ ደስታ በማጠቃለያው ይህን ብሏል። “ዘጋቢዎቼ ወደ ቤታቸው እየተንቀሳቀሱ ነው። ነገ እንገናኝ። አሁን ከምሽቱ 3:55 ነው። ቸር ያሰማን።” EMF ተጨማሪ ዘገባ ካለ በነገው እለት ያቀርባል።
Source: Ethioforum

No comments:

Post a Comment