Friday, January 17, 2014

ጁባ የደቡብ ሱዳን ውጊያ ቀጥሏል

የደቡብ ሱዳን ውጊያ ዛሬም ተባብሶ ቀጥሏል ። በዛሬው እለት  ቁልፍ በሆነችው በማላካል ከተማ የመንግስት ጦር ኃይል በከተማይቱ ካሉት ወታደሮቹ ጋር ግንኙነት ማድረግ አለመቻሉን አስታውቋል ። በከተማይቱ  የስልክ ግንኙነት  ተቋርጧል ። አማፅያንም መንግሥትም በነዳጅ ዘይት የበለፀገችውን ማላካልን ተቆጣጥረናል ይላሉ ። የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት በበኩሉ ሁለቱንም ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ዘግናኝ ግድያ ይከሳል ።  በቅርቡ ደቡብ ሱዳንን የጎበኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሃፊ ኢቫን ሲሞኖቪክ  በደቡብ ሱዳን ሰሜናዊ አካባቢ ቤንቱ በተባለው ከተማ ጎዳና ታስረው የተረሸኑ ሰዎች አስከሬኖች ማየታቸው ተናግረዋል ። የቤንቱ 40 ሺህ ነዋሪዎች በአማጥያን ጥቃት ከተማይቱን ለቀው በመውጣታቸው አሁን ባዶዋን ቀርታለች ። አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው የመንግሥትና የአማፅያን የተኩስ አቁም ንግግር በነበረበት እንደተገታ  ነው  ። አማፅያን የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ መልስ አላገኘም ። በሌላ በኩል በግጭቱ ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱት ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር ከ 100 ሺህ ሊበልጥ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ አስታውቋል ። ከአንድ ወር በፊት በተቀሰቀሰው የደቡብ ሱዳን ግጭት ሰበብ በየቀኑ ከ አንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገራት ይገባሉ ። ወደ ጎረቤት ሃገራት ከተሰደዱት ሌላ 468,000 ሰዎች በሃገር ውስጥ ተፈናቅለዋል ።
source:http://www.dw.de/

No comments:

Post a Comment