Saturday, February 22, 2014

በኤልኩራን የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ የነዳጅ ፍሰት ታየ

በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኤልኩራን በተሰኘ አካባቢ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ‹‹ኒው ኤጅ›› የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ፣ በቆፈረው ‹‹ኤልኩራን ሦስት›› የተባለው ጉድጓድ ውስጥ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ፍሰት ታየ፡፡

ኩባንያው ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ጉድጓዱን በመቆፈር ላይ ይገኛል፡፡ የኩባንያው ዕቅድ 2,850 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ መቆፈር ነው፡፡ ታማኝ ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው 1,200 ሜትር ጥልቀት ላይ ሲደርስ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ፍሰት በጉድጓድ ውስጥ ተመልክቷል፡፡
ከጉድጓዱ ውስጥ በቂ የሆነ ናሙና ለመውሰድና የነዳጅ ፍሰት ሙከራ ለማካሄድ ቁፋሮው መቋረጡን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አክለውም በመጀመሪያ በዕቅድ ከተያዘው 2,850 ሜትር በላይ ዘልቆ ለመቆፈር መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ የነዳጅ ፍሰቱ መጠን ከፍተኛ እንዳልሆነ የተናገሩት ምንጮች፣ የፍሰቱን መጠን ለመጨመር የሚያስችሉ የተለያዩ የጂኦሳይንስ ሥራዎች መሠራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1972 በኦጋዴን የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ያካሂድ የነበረው ቴኔኮ የተሰኘ የአሜሪካ የፔትሮሊየም ኩባንያ በኤልኩራን አካባቢ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ የነዳጅ ክምችት እንዳገኘ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ክምችቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማስገኘት የሚበቃ መጠን የለውም በማለት ተትቶ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
‹‹በዚያን ወቅት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 14 ዶላር ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የነዳጅ ፍለጋ ቴክኖሎጂ አሁን ካለው ጋር ሲነፃፀር ኋላቀር ነበር፡፡ አሁን በዓለም አቀፍ ገበያ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 120 ዶላር ነው፡፡ የነዳጅ ፍለጋ ቴክኖሎጂውም ተራቋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኒው ኤጅ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አዋጪ የሆነ የነዳጅ ክምችት መኖሩን ሊያረጋግጥ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
አንድ ከፍተኛ የፔትሮሊየም ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኦጋዴን በተለይም በሂላላና ኤልኩራን አካባቢ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ፍሰት መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ፍሰቱን መመልከት በራሱ አዋጪ (Commercial Deposit) ክምችት መኖሩን አያረጋግጥም፡፡ ‹‹ብዙ ተጨማሪ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
ኒው ኤጅ አፍሪካ ኦይል ከተሰኘው የካናዳ ኩባንያ ጋር በመጣመር በብሎክ 7፣ 8 እና አዲንላ አካባቢዎች የነዳጅ ፍለጋ ሥራ የሚያካሂድ ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካና ኮንጐ ብራዛቪል በነዳጅ ፍለጋ መስክ የተሰማራ ነው፡፡ ኒው ኤጅ እ.ኤ.አ. በ2007 የተመሠረተ ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነ በአፍሪካ ላይ አተኩሮ የሚሠራ የነዳጅ ኩባንያ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment