Wednesday, February 26, 2014

ወገኖቻቸው መርጃ ግማሽ ሚሊዮን ብር ሰጡ

በዳላስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ ለተጎዱ 

አቶ ብርሃን መኮንን ከዳላስ ፎርት ወርዝ አካባቢ የተዋጣውን ገንዘብ ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው ሲያስረክቡ
አቶ ብርሃን መኮንን ከዳላስ ፎርት ወርዝ አካባቢ የተዋጣውን ገንዘብ ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው ሲያስረክቡ
(ዘ-ሐበሻ) በቴክሳስ ግዛት በዳላስና ፎርት ወርዝ አካባቢ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ኖቬምበር 2013 ዓ.ም ጉዳት ለደረሰባቸውና ወደ ሃገራቸው ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን ወንድም እና እህቶቻቸው ማቋቋሚያ የሚውል 31 ሺህ ዶላር ወይም ግማሽ ሚሊዮን ብር አዋጥተው ሰጡ።

ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ በዳላስና ፎርት ወርዝ አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ቁጣ ሰላማዊ ሰልፍና የሻማ ማብራት ምሽት በማድረግ ቁጣቸውን እና ሃዘናቸውን መግለጻቸው በወቅቱ በዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ የተዘገበ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ከማዘን እና ከመቆጣት ባሻገር ገንዘባቸውን በማዋጣት ወደ ሃገር ቤት ለተመለሱት ኢትዮጵያውያን ማቋቋሚያ እንዲውል በሚል ይህን 31 ሺህ ዶላር አሰባስበው ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM የአሜሪካ ቅርንጫፍ ሰጥተዋል።
የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ብርሃን መኮንን በዳላስ ፎርት ወርዝ የተሰባሰበውን 31 ሺህ ዶላር (በዛሬው የአዲስ አበባ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ 595 ሺህ 150 ብር) ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በማምራት ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በቼክ ካስረከቡ በኋላ እርዳታው እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በሕዝቡ ቃል ተገብቶ ያልተሰበሰበው ገንዘብም በቀጣይ እንደተሰበሰበ ለIOM እንደሚሰጥ ሊቀመንበሩ ጨምረው ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከሳዑዲ የተመለሱ ኢትዮጵያውያንን ለማቋቋም በአዲስ አበባ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ከ160 ሺህ በላይ የሳዑዲ አረቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያውያንን ለማቋቋም ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቅ፤ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ወገኖቻቸውን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያደንቅ ድርጅቱ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።
Source: Zehabesha

No comments:

Post a Comment