Sunday, March 3, 2013

በሙስሊሙ ሕብረተሰብ ላይ እየደረሰያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ያሳስበናል

አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህገመንግስት፣ መንግስት በሃማኖት የውስጥ ጉዳይ እንዳይገባ ቢከለክልም፣ የኢህአዴግ መንግስት ግን እንዳሻው በሁሉም ሃይማኖቶች ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ያለከልካይ ገብቶ እያቦካ ይገኛል፡፡
የዕምነት ነፃነት አምልኮን በነፃነት ማካሄድን፣ ዕምነትን ማስፋፋትንናየእምነት ተቋማትን በነፃነት ማስተዳደርን የሚያካትት ነው፤ አንዱ ሃይማኖታዊ አላባ ተከብሮ ሌላኛው አላባ እየተጣሰ የሃይማኖት ነፃነት ተከብሯል ቢባል ከመንግስት ውጪ
ማንንም የሚያሳምን አይሆንም፡፡
ኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርአቱን ለማስቀጠል ሲል የዕምነት ተቋማትንና መሪዎቹን በቁጥጥሩ ስር ሲያደረግ ኖሯል፡፡ ይህ አንባገነናዊ ድርጊት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይም ተግባራዊ በመደረጉ ምዕመናኑ የመንግስትን ድርጊት በመቃወም ከአንድ አመት ለበለጠ ጊዜ ጠንካራ ሰላማዊ ትግል አድርገዋል፤
እያደረጉም ይገኛሉ፡፡
መንግስት አለመግባባቱን ለመፍታት የቀረቡለትን ሶስት ጥያቄዎች ከመፍታት ይልቅ በማን አለብኝነት የትግሉን ግንባር ቀደም መሪዎች ከማሰር ባለፈ በምዕመናኑ ላይ
ኢሰብአዊ ጥቃቶችን ማድረሱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ለኢህአዴግ ህገመንግስትን የመጣስ ድርጊት አዲስ ባህሪው ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣውን
ማጠናከሩ ያሳስበናል፡፡
ለፍኖተ ነፃነት ምስክርነታቸውን የሰጡ ሰለባዎች እንዳረጋገጡት ባለፉት ሳምንታት
ቤታቸው ያለፍርድ ቤት ማዘዣ በሌሊት ተበርብሯል፣ እንግልት ተፈፅሞባቸዋል እንዲሁም የንብረት ዝርፊያም ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ለዝግጅትክፍላችን የደረሱ ሌሎች ታአማኒመረጃዎች እንደሚያመላክቱትም የፍርድ ቤት ብርበራ ወጣባቸው
የተባሉትም ግለሰቦች ስማቸው የተሞላው በፍርድ ቤት ሳይሆን
ብርበራውን ባካሄዱትፖሊሶች ነው፡፡
ይህ የመንግስት ሀይሎች ድርጊት ችግሩን ከማባባስ ባለፈ የሚያመጣው
መፍትሄት አይኖርም ብለን እናምናለን፡፡
መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለበት፤ ስለሆነም ይህ አይነቱ ህገወጥና ሀላፊነት የጎደለው ድርጊት እንዳይቀጥል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት
የተበደሉ ዜጎችን ቅሬታ በማጣራትም በህገወጥ ድርጊት በፈፀሙ ሃይሎቹ
ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡
ብርበራው የተካሄደባቸው ግለሰቦች በተጨባጭ ወንጀል ተጠርጥረውም ከሆነ ብርበራው በቀን መካሄድ ነበረበት ብለን እናምናለን፡፡ በጠራራ ሌሊት የግለሰቦችን ቤት መበርበሩ ህዝብን ከማሸበር ያለፈ ውጤት የለውም፡፡
ሆኖም መንግስትም ሆነ ብርበራውን ያካሄደው ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት አለመፈለጋቸው ተግባሩ እንደተለመደው ፖለቲካዊ አንደምታ እንዳለው ያስረዳል፡፡ ይህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ገለልተኛ ነን በሚሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋም መጣራትና መጋለጥም ነበረባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላነሷቸው ግልፅ የመብት ጥያቄዎች ብልሀት
የተሞላበት ምላሽ መስጠት ያቃተው የኢህአዴግ መንግስት እየወሰዳቸው
ያሉት ኢህገመንግስታዊ እርምጃዎች ያሳስቡናል፤ በሙስሊሙ ሕብረተሰባ
ላይ እየደረሰያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለመድረሱ
ከመንግስት ሌላ ተጠያቂ የሚደረግ አካል አይኖርም፡፡
ፍኖተ ነፃነት

No comments:

Post a Comment