Sunday, March 17, 2013


መንግሥት ፖሊሶች በሚፈጽሙት ድብደባና የመብት ጥሰት ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ                17 MARCH 2013 ተጻፈ በ    
•    የዜጐችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ረቂቅ መርሐ ግብር አቅርቧል

ሕግ የማስከበር ሥልጣን የተሰጣቸው አንዳንድ የፖሊስ አባላት የዜጐች የአካል ደኅንነት መብትን በመጣስ ድብደባና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለሚፈጸሙ፣ ይህንንና ሌሎች የዜጐች መብቶችን ለማስከበር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ መንግሥት ይፋ አደረገ፡፡
መንግሥት ይህንን ይፋ ያደረገው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የቀጣይ ሦስት ዓመታት ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ረቂቅ ዶክመንት ነው፡፡

‹‹የአካል ደኅንነት መብትና ኢሰብዓዊ አያያዝ ክልከላ›› በሚለው በዚህ የሦስት ዓመታት የድርጊት መርሐ ግብር ክፍል ውስጥ› የአገሪቱ ሕጐች ለዚህ መብት ጥበቃ ማድረግ የሚያስችል ድንጋጌዎችን እንደያዙ ይገልጻል፡፡

ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ የአካል ደኅንነት መብት ያለው መሆኑን፣ እንዲሁም ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን ይገልጻል፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብት በማስከበር ረገድ ብዙ ርቀት መሄድ ቢቻልም፣ ሙሉ ለሙሉ መተግበር እንዳልቻለ መንግሥት ግንዛቤ ያለው መሆኑን ይገልጻል፡፡


ሕጋዊ የእርምት ዕርምጃዎችን መውሰድ የሚቻል ቢሆንም፣ በአንዳንድ የፖሊስ አባላት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሁንም እየተፈጸሙ ይገኛሉ ሲል ረቂቅ የድርጊት መርሐ ግብሩ ያትታል፡፡ በመፍትሔነትም የአካል ደኅንነት መብትንና ኢሰብዓዊ አያያዝ ክልከላን በይበልጥ ለማረጋገጥ በሥራ ላይ ያሉ የፖሊስ አባላትን የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ የማዳበርና የማስረፅ፣ እንዲሁም የተዘረጋውን የሕግ ተጠያቂነት የበለጠ በማጠናከር ችግሩን ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ሥርዓት አስይዛለሁ ይላል፡፡

ይህ የመብት ጥሰት ተጠርጥረው በፖሊስ እጅ በሚገኙ እንዲሁም ፍርድ ቤት ቀርበው በምርመራ ላይ ያሉ ዜጐች ላይ የሚፈጸም በመሆኑ፣ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በሕግ አስከባሪው አካል ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ዜጐችን በተመለከተ በመጀመርያ በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ሰዓት ጀምሮ በቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ለመረጡት ቤተሰባቸው፣ ለሕግና ለሃይማኖት አማካሪዎቻቸው ወይም ለሌላ ለመረጡት ሰው ስላሉበት ሁኔታ እንዲያሳውቁ ይደረጋል፡፡ ስልክ በሌለበት አካባቢ በመረጡት ሰው ወይም በሌላ የመገናኛ ዘዴ መልዕክት እንዲልኩ ይደረጋል፡፡ ለዚህም ፖሊስ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ግዴታ እንደሚጣልበት ይገልጻል፡፡

የወንጀል ምርመራ በሚደረግባቸው ወቅትም በምርመራው ላይ የተገኙ የፖሊስ አባላት ስም፣ የምርመራው ትክክለኛ ሥፍራና ሰዓት የሚመዘገብበት መዝገብ ይዘጋጃል፡፡ ፍርድ ቤት በጠየቀ ጊዜም እንዲቀርብ ይደረጋል ሲል በቀጣዮቹ ዓመታት በዚህ ረገድ መንግሥት ለመፈጸም የተዘጋጀበት መሆኑን ያስረዳል፡፡

የቅድመ እስር ጊዜን ለማሳጠርም የወንጀል ድርጊቶችን እንደክብደታቸው በመለየት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የወንጀል ምርመራው ሊጠናቀቅ የሚገባበት የጊዜ ገደብ በሕግ እንዲቀመጥ ይደረጋል ሲል ዕቅዱን ያስረዳል፡፡ በተለይ በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት ሳይፈረድባቸው በምርመራ ላይ የሚገኙ ወራትን ያስቆጠሩ በርካታ ዜጐች ከመኖራቸው አንፃር የመንግሥት መነሳሳት ለየት ያለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በፖሊሶች እየተደበደቡ ወደ ጣቢያ እንዲሄዱ የሚደረጉ ዜጐችን በአደባባይ መመልከትና እንዲሁም ከጣቢያ በጠባብ ክፍት መኪኖች እጃቸው በካቴና ታስሮና ታጭቀው ወደ ፍርድ ቤት የሚጓዙ ተጠርጣሪዎችን ማየት የዘወትር ገጠመኝ በሆነባት አዲስ አበባ፣ ይህንን ለማስቀረት መንግሥት ያቀረበው የድርጊት መርሐ ግብር ቁርጠኝነትን መኖሩን ለተጠያቂነት መሰናዳቱንም እንደሚያስረዳ እየተነገረ ነው፡፡

የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብሩ ከዚህ ውጭ በመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ የመጠጥ ውኃ፣ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎቶችና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶችን ዜጐች ሊያገኙ እንደሚገባ በማመን፣ መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ያሉበትን የአፈጻጸም ችግሮች በመለየት ዝርዝር የአፈጻጸም ዕቅድ አውጥቷል፡፡

የድርጊት መርሐ ግብር ሰነዱን የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዝርዝር እይታ ለሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡  

No comments:

Post a Comment