Monday, March 18, 2013

አዲስ አበባ፡ የጀርመን ፕሬዚደንት የኢትዮጵያ ጉብኝት

ዜና | 18.03.2013 | 17:04

የፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵያን ለአራት ቀናት ለመጎብኘት ትናንት አዲስ አበባ ለገቡት የጀርመኑ ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ ዛሬ በብሔራዊ ቤተመንግሥት አቀባበል አደረጉ። የ 73 ዓመቱ ፕሬዚደንት ጋውክ ትናንት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋ ሀሳብ ከተለዋወጡ በኋላ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ቢያሞግሱም፡ በሀገሪቱ የሚታየው የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።

« የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስራቸውን ለማከናወን ችግር ያለባቸው መሆኑን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ረገድ መንግሥት አብረውት መስራት ከሚፈልጉትን ወገኖች ጋ ተባብሮ ለመስራት አቅሙ አለው። ስለሆነም ይህን የሚያደርግበትን ስልት ያዳብራል ብየ እጠብቃለሁ። »
ጀርመናዊው ፕሬዚደንት ወደኢትዮጵያ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በሀገራቸው የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋ እንዲነጋገሩ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል። ከነዚህም አንዱ በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፡ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ እና በምክር ቤቱ የኤኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር ቲሎ ሆፐ ናቸው።
« በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነት፡ የሰብዓዊ መብት፡ የመሰብሰብ፡ የፕሬስ፡ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት በጉልህ ገደብአርፎበታል። ትችት የሚያቀርቡ ብዙ ጋዜጠኞች፡ ብዙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖለቲከኞች በእስር ላይ ይገኛሉ። እና ፕሬዚደንቱ ለዚሁ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ስለዚሁ መጥፎ ገፅታ በግልጽ እንዲያነሱ እና በዝምታ እንዳያልፉ እማፅናለሁ። »  
ጀርመን ኢትዮጵያ ለጀመረችው ዴሞክራሲያዊው ሂደት ርዳታ ለመስጠት ዝግጁ መሆንዋን ፕሬዚደንት ጋውክ ለአስተናጋጃቸው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ገልጸዋል። ሥልጣን ከያዙ ልክ በዛሬው ዕለት አንድ ዓመት የሆናቸው ጀርመናዊው ፕሬዚደንት ዘንድሮ ሀምሣኛ የምሥረታ ዓመቱን በሚያከብረው የአፍሪቃ ህብረት ባደረጉት ንግግር አፍሪቃውያን መንግሥታት ዴሞክራሲን እና የሕግ የበላይነትን እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል።  በአፍሪቃውያቱ ሀገራት በጠቅላላ ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ እና በምክር ቤት ቁጥጥር የሚደረግባቸው መንግሥታት ብቻ ሥልጣን መያዝ እንዳለባቸውም ፕሬዚደንት ጋውክ አሳስበዋል።  የአፍሪቃ ህብረትም በሙስና አንፃር እንዲታገል እና በአህጉሩ የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር ጥረት እንዲያደርግ ፕሬዚደንት ጋውክ አክለው ተማፅነዋል። ጋውክ በአፍሪቃ ህብረት ንግግራቸውን ከማሰማታቸው በፊት ከህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ጋ ተወያይተዋል። ከቀትር በፊት ፕሬዚደንት ጋውክ በአዲስ አበባ፣ በአመለካከታቸው ምክንያት ደርግ ሳይገድላቸው አልቀረም በሚባሉት የቀድሞ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስትያን ቄስ ጉዲና ቱምሳ መካነ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

No comments:

Post a Comment