በእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ፕሬዚዳንትና ተቀናቃኛቸው በኢጋድ ሸምጋይነት በአዲስ አበባ ድርድር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሰሜንዋ ሱዳን ነፃ ከወጣች ሁለት ዓመት የሆናት ደቡብ ሱዳን፣ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በቀድሞው ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳው ቀውስ፣ የጐሳ ቅርፅ ይዞ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ከ200 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ተፈናቅለዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት በግንባር ቀደምትነት እየተንቀሳቀሰ ያለው ኢጋድ፣ ሁለቱም ወገኖች ተኩስ አቁመው ችግራቸውን በድርድር እንዲፈቱ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ለዚህም የአራት ቀናት ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር፡፡
ቀነ ገደቡ ታኅሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ መሪዎቹ ለድርድሩ ፈቃደኛ መሆናቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲዘገብ፣ የሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪ የልዑካን ቡድን ማክሰኞ ሌሊት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ቦር የተባለችውን ስትራቴጂካዊ ከተማ በወታደራዊ ኃይል በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ሪክ ማቻር አስታውቀው፣ በቀድሞው የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር መሪ ጆን ጋራንግ ባለቤት ርብቃ ጋራንግ የሚመራ የልዑካን ቡድን እንደሚልኩ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ሳምንት ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በመሄድ የዕርቅ ድርድር ጥረት በማድረግ ላይ ሲሰነብቱ፣ አማፂው ሪክ ማቻር በመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ተጠርጥው የታሰሩት አሥራ አንድ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሥዩም መስፍንን ተቀናቃኞቹን ለማደራደር በኢጋድ አማካይነት ልዩ ልዑክ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግጭቱ ሰለባ መሆናቸው እየተነገረ ሲሆን፣ ሰሞኑን 650 ሰዎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አምባሳደር ዲና ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ ቁጥራቸው አሥራ አምስት ሺሕ የሚደርሱ ዜጐች በደቡብ ሱዳን ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግጭት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች የማስወጣቱ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ማረጋገጥ ባይችልም ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን በግጭቱ ሳቢያ ሕይወታቸው እንዳለፈ በአንዳንድ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment