-ባለ ሪከርዱ አፀዱ ጸጋዬ በፕራግ ግማሽ ማራቶን ይሳተፋል
የሦስት ኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ቀነኒሳ በቀለ ከሁለት ወር በኋላ በሚካሄደው የፓሪስ ማራቶን እንደሚወዳደር ታወቀ፡፡ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ኢአፌማ) በድረ ገጹ እንደገለጸው፣ የወርቅ ደረጃ ባለው ‹‹ሺኔይደር ኤሊክትሪክ ማራቶን ደ ፓሪስ›› ላይ ቀነኒሳ የሚወዳደረው መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት የመም (ትሪክ) እና የአገር አቋራጭ ውድድሮችን በተደጋጋሚ በማሸነፍ የሚታወቀው ቀነኒሳ ከሦስት ዓመት ወዲህ በ10 ሺሕ ሜትር ውድድር ውጤት ማጣቱ፣ ይህም በዴጉ ያለም ሻምፒዮና (2003 ዓ.ም.) ውድድሩን ማቋረጡ፣ በለንደን ኦሊምፒክም (2004 ዓ.ም.) ከሜዳሊያ ውጭ ሆኖ በአራተኛነት ያጠናቀቀበት ነበር፡፡
የ5 ሺሕ ሜትርና 10 ሺሕ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን የሰበረው ቀነኒሳ ወደ ጎዳና ላይ ሩጫ ፊቱን ካዞረ ወዲህ ባለፈው መስከረም በግሪት ኖርዝ ራን (ግማሽ ማራቶን ውድድር) የዓለምና ኦሊምፒክ ሻምፒዮኑን ሞህ ፋራህና በኩር አትሌት ኃይለ ገብረሥላሴን አስከትሎ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ቀነኒሳ በፓሪስ ማራቶን ስኬታማ መሆን ከቻለ ከሁለት ዓመት በኋላ በሪዮ (ብራዚል) በሚካሄደው ኦሊምፒክ ተሳታፊነት ስንቅ ይሆነዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በዘንድሮው የስፖርቲሲኖ ፕራግ ግማሽ ማራቶን ውድድር የቦታውን ሪከርድ የጨበጠው ኢትዮጵያዊው አፀዱ ጸጋዬ እንደሚካፈል ማረጋገጣቸውን አዘጋጆቹ ባለፈው ሐሙስ (ጥር 8) አስታወቁ፡፡
በኢአፌማ የወርቅ ደረጃ ባለው ግማሽ ማራቶን አፀዱ በ2004 ዓ.ም. የቦታውን ሪከርድ 58 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ ሮጦ በማሸነፍ መያዙ ይታወሳል፡፡ ይህም ክንውኑ አፀዱን አራተኛው የዓለም ፈጣን ሯጭ ሲያደርገው ክብረወሰኑንም ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰበረውም አልተገኘም፡፡ በጉዳት ሰበብ ከውድድር ርቆ የነበረው አፀዱ ባለፈው ወር የኒው ዴልሂን ግማሽ ማራቶን በ59 ደቂቃ 12 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አሸንፏል፡፡
ኢአፌማ በድረ ገጹ እንደዘገበው በመጪው መጋቢት በሚካሄደው ውድድር የአፀዱ ተቀናቃኝ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል የ2003 ዓ.ም. የፕራግ ግማሽ ማራቶንና የአምናው የቼክ ማቶኒ ግማሽ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊው ፊልሞን ሊሞ ይገኝበታል፡፡
በሴቶች ምድብ ፕራግ ላይ ለአሸናፊነት የምትጠበቀዋ ኢትዮጵያዊቷ ፍሬ ሕይወት ዳዶ ናት፡፡ ፍሬ ሕይወት የ2003 ዓ.ም. ኒው ዮርክ ሲቲ ማራቶን አሸናፊ ስትሆን፣ በዚያው ከተማ በ2004 ዓ.ም. በተካሄደው ግማሽ ማራቶንም ያስመዘገበችው 1 ሰዓት 08 ደቂቃ 35 ሰከንድ ነበር፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment