Saturday, January 25, 2014

የደቡብ ሱዳን ተደራዳሪዎች ተኩስ ለማቆም ተስማሙ


በኢጋድ አደራዳሪነት ለ20 ቀናት ያህል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ሱዳን ግጭት ድርድር፣ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ 
የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሥዩም መስፍን በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ስምምነቱ የተኩስ ማቆምና የእስረኞች ጥያቄን የተመለከተ ነው፡፡ 
‹‹ከዚህ በተጨማሪም ይህ አሁን የደረስንበት ስምምነት የመጨረሻው መጀመርያ ነው፤›› በማለት በቀጣይም ድርድሩ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ዋና ተደራዳሪ ኒያል ዲያንግ ኒያል በበኩላቸው፣ በስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ ምንም ጥርጥር የለም ከማለታቸው በተጨማሪ፣ ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ ለመሥራትም ቃል በመግባት የድርድሩን ውጤት አድንቀዋል፡፡ 
የአማፂያኑን ቡድን የወከሉት ጄኔራል ታባን ዴንግ ጉይ ይህ ስምምነት በደቡብ ሱዳን ለሚደረገው ሰላምን የማምጣት ሥራ ወሳኝ ግብዓቶችን ያካተተ ነው በማለት የድርድሩን ውጤት ፋይዳ ገልጸዋል፡፡ 
የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሥዩም መስፍን በሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች ይህ ስምምነት የመጀመርያው ደረጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለስምምነቱ መሳካት ሁለቱም ወገኖች በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ 
አምባሳደሩ ሁሉም ወገኖች በተለይ በአራት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ በአጽንኦት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እነዚህም ሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች በቅን ልቦና የፈረሙትን ስምምነት ለመተግበር በቁርጠኝነት ወደ ተግባር እንዲቀይሩት፣ በግጭቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ አፋጣኝ ሥራዎችን መሥራት፣ ፖለቲካዊ ውይይቶችን በማካሄድ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ላይ በመድረስ ብሔራዊ ዕርቅ ለማምጣት መጣርና በኢጋድና በአፍሪካ ኅብረት የተላለፉትን ውሳኔዎች ማክበር ናቸው፡፡ 
ይህን ስምምነት በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አሜሪካና ቻይና የመሳሰሉ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ የተቀበሉት ነው፡፡ ቀጣይ ሥራዎችንም ለመሥራትና በግጭቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጐቿን ለማቋቋም ቃል ገብተዋል፡፡ ለ20 ቀናት ያህል በፈጀው ድርድር ላይ በአማፂያኑ በኩል እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦ የነበረው የእስረኞች ጉዳይ፣ ከሳምንት በኋላ በሚጀመረው ሁለተኛው የድርድር ምዕራፍ እንደሚካተት የኢጋድ ሴክሬታሪያት አምባሳደር ተወልደ ገብረ መስቀል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
source: http://www.ethiopianreporter.com/  

No comments:

Post a Comment