Saturday, January 25, 2014

የኖርዌይ መንግሥት ለኢትዮጵያ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ ዕድል ሰጠ

የኖርዌይ መንግሥት ከኢትዮጵያ ወደ አገሮቹ ለሚገቡ ምርቶችና ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ ዕድል ሰጠ፡፡ የኢትዮጵያ ምርቶችና ዕቃዎች ወደ ኖርዌይ ገበያ ለመግባት የሚያስችል የቀረጥ ነፃ ዕድል ያገኛሉ፡፡ 
የኖርዌይ ገበያዎች ታክስ መሥሪያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር ሴሲሊ አልናስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ በኖርዌይ መንግሥት የተሰጠው ከቀረጥ ነፃ ዕድል ማንኛውንም ዓይነት ምርት የሚመለከት ነው፡፡ ዕድሉም የጊዜ ገደብ እንደሌለውና ኢትዮጵያ ከበለፀጉት አገሮች ተርታ እስከምትሰለፍ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጋሻው ደበበ በበኩላቸው፣ በኖርዌይ መንግሥት ከኢትዮጵያ ወደ አገሪቱ ለሚገቡ ምርቶችና ዕቃዎች የተሰጠው የቀረጥ ነፃ ዕድል፣ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ከመደገፉም በተጨማሪ፣ ዘላቂ ልማትና የተጠናከረ የውጭ ንግድ እንዲኖር ይረዳል ብለዋል፡፡ ይህ ከበለፀጉ አገሮች ለታዳጊ አገሮች የሚደረግ የቀረጥ ነፃ ድጋፍ ከዓለም የንግድ ድርጅት መርሆዎች ነፃ በመሆኑ፣ የሚከናወነውም አገሮችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 
ኖርዌይ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ባትሆንም፣ የአውሮፓ ነፃ የንግድ ቀጣናን ከመሠረቱ አገሮች አንዷ ናት፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ነፃ የንግድ ቀጣና አባል አገሮች ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ አይስላንድና ሌይስትንስታይን ናቸው፡፡ 
የኢትዮጵያና የኖርዌይ የንግድ ልውውጥ ብዙም ያልዳበረ በመሆኑ፣ አገሮቹ እ.ኤ.አ. በ2012 የተገበያዩት የንግድ መጠን 58 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ 
ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው የንግድ እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. በ2004 ከነበረበት 4.2 ሚሊዮን ዶላር፣ እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ 2.7 ሚሊዮን ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም የንግድ ግንኙነቱ በ35 በመቶ ማሽቆልቆሉን ያመለክታል፡፡ 
ኖርዌይ በዋነኛነት ከኢትዮጵያ የምትገዛቸው ምርቶች አበባ፣ ቡና፣ ማርና ስኳር ናቸው፡፡ 
 source:www.ethiopianreporter

No comments:

Post a Comment