አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ዓርብ በጽሕፈት ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
በተለይ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሲካሄድ የነበረውና ያለ ውጤት የተበተነው የሦስትዮሽ ድርድር፣ የደቡብ ሱዳን ቀውስና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ስላለው የዕርቅ ሙከራ፣ እንዲሁም በቅርቡ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝትን ምክንያት በማድረግ ከቻይና መንግሥት የተሰጠው የተቃውሞ መግለጫ የውይይቱ ዋና ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ባለፈው ዓርብ የተካሄደውን ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለው የማነ ናግሽ ሪፖርተርን ጨምሮ ከጋዜጠኞች ከተነሱ ጥያቄዎችና በአምባሳደር ዲና ከተሰጡ ምላሾች መካከል የተመረጡትን እንደሚከተለው አቅርቦአል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በተካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ሦስተኛው ስብስባ ያለ ውጤት ተበትኗል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ግብፅ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ፓነል እንዲቋቋም ያቀረበችው ጥያቄ በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለምንድነው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ፓነል እንዲቋቋም የማትፈልገው?
አምባሳደር ዲና፡- ጭብጡ እንደዚያ አይደለም፡፡ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል እንዲቋቋም አንፈልግም አይደለም፡፡ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል ሚና ላይ ነው ልዩነታችን፡፡ በግብፅ በኩል እየተባለ ያለው የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል በሚቋቋመው ኮሚቴ [የባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የተቋቋመ] ጋር ተደርቦ እንደገና ጉዳዩን ይመልከት የሚል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል የተጠኑ ነገሮች እንደገና እንደ አዲስ እንዲታይ ነው የሚፈልጉት፡፡ እልባት ባገኙ ጉዳዮች ላይ ማለት ነው፡፡ እኛና ሱዳን እያልን ያለነው ዓለም አቀፍ ፓነል ይቋቋም፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ፓነል የሦስቱ አገሮች ተወካዮች በሚያቀርቡት ጥናት ላይ መጨረሻ ላይ አስተያየት ይሰጥ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በአስተያየቱ መሠረት ሦስቱ አገሮች በሙሉ መግባባት እልባት ይስጡት ነው፡፡ ግብፆች ግን ከመጀመሪያውኑ እንደገና የዓለም አቀፍ ባሙያዎች ፓነል እንደ አዲስ ተመሥርቶ በሦስቱ አገሮች የተመሠረተው ኮሚቴ የሚሠራውን ሥራ አብሮ ይሥራ ነው የሚሉት፡፡ የልዩነቱ ጭብጥ እሱ ላይ ነው እንጂ የኢትዮጵያ አቋም የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል እንዳይመሠረት የሚል አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ ፓነል ይቋቋም፣ ኮሚቴው ባልተስማማበት ጉዳይ ላይ አስተያየት ይስጥ፡፡ ከዚያም ሦስቱ አገሮች ይስማሙበት የሚል ነው የግብፆች ፍላጐት፡፡ የእነሱ አስተያየት የመጨረሻ ተፈጻሚ እንዲሆን ነው፡፡ ይኼ አይሆንም፤ የአገሮችን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የቻይና መንግሥት የጃፓንን ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት ተቃውሟል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ምንድን ነው?
አምባሳደር ዲና፡- ይኼ የቻይና መንግሥት ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ የእኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁሉም አገር ከራሱ ጥቅም አንፃር የሚፈልገው ስሜት ሊኖረው ይችላል፡፡ የሚፈልገውን አስተያየት መስጠት ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በእኛ ደረጃ መተቸት አግባብነት አይኖረውም፡፡
አንድ ነገር ግን አለ፡፡ እኛ ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በዚህም ልክ ከጃፓንም ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ ይህንን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ እኛ በአገሮች ልዩነት መካከል አያገባንም፡፡ ሁሉንም በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት ከአገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በዓለም አቀፍ ሕጐች ላይ ተንተርሰን ማዳበር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የጃፓንን ጠቅላይ ሚኒስትር እዚህ መምጣት የማይወድ ኃይል ካለ መብቱ ነው፡፡ መውደድ አለብህ አንልም፡፡ ነገር ግን ከአገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በአንዱ ኪሳራ አናራምድም፡፡ ለምሳሌ ከጃፓን ጋር ባለን ግንኙነት ምክንያት ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት አንገፋም፡፡ በዚህ ደረጃ ነው ማየት ያለብን፡፡
የተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች የተለያዩ ነገሮች እያሉ ነው ያሉት፡፡ ለዚህም መነሻው ከማንም የተሰወረ ነገር አይደለም፡፡ በቻይናና በጃፓን መካከል በደሴቶች ምክንያት እየተነሳ ያለው አለመግባባት ነው፡፡ ያ በራሳቸው ጊዜና ቦታ ሊሄዱበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እምብዛም እኛን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡ እኛን የሚመለከተው በተናጠል ከአገሮቹ ያለን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን እንዴት እንጠብቅ የሚል ነው፡፡ እሱም ሲባል በጣም በስግብግብነት መንፈስ አይደለም፡፡ የእነሱንም ጥቅም ከግምት በማስገባት ግንኙነታችንን በመርህ ላይ ተመሥርቶ ማጠናከር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በደቡብ ሱዳን ቀውስ ላይ ኢጋድ ሁለቱን ተቀናቃኝ ቡድኖች የማስታረቅ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ አንዳንዶች በኃይል ጣልቃ ገብተዋል የሚባል ነገር አለ፡፡ ይህ የኢጋድን ጥረት አያደናቅፈውም ወይ?
አምባሳደር ዲና፡- አንዳንዶች ወደ ደቡብ ሱዳን ጦር እየላኩ ነው የሚባለውን ሁላችንም በሚዲያ የምንሰማቸው ነገሮች አሉ፡፡ የኢጋድ አቋም በተቻለ መጠን አንድ ዓይነት ነው የነበረው፡፡ ሁለቱንም በእኩልነት ማስተናገድ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መሀል እንደተነገረው አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች ይጠፋሉ አይባልም፡፡ ይኼ ግን የኢጋድን አቋም የሚፃረር ነው፡፡ የኢጋድን ጥረት የሚያሳንስ ነው የሚሆነው፡፡
ለኢጋድ አቋም ገና ከጅምሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ሰጥቶታል፡፡ አፍሪካ ኅብረት የኢጋድን አቋም እንዳለ ወስዶ ከእሱ ጋር የሚጣጣም መግለጫ ነው ያወጣው፡፡ የኢጋድ ጥረት መጠናከር አለበት የሚል ነው፡፡ ሁሉም ጥሪ የሚያደርጉ የኢጋድን አቋም ሲያንፀባርቁ ነበሩ፡፡ በአስቸኳይ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ፡፡ ምክንያቱም ይህ እያስከተለ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ለአገሩም ለአካባቢውም ጠንቅ ነው የሚል ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ብዙ ጊዜ በዋና ፀሐፊው በኩል ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል፡፡ የኢጋድን ጥሪ በመድገም ማለት ነው፡፡
የአውሮፓ ኅብረትም በተለይ ደግሞ ዓለም አቀፍ የአጋሮች ኅብረት ወደዚህ [የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር] ልዑክ በመላክ ጭምር እንደዚሁ የኢጋድን ጥረት ደግፏል፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ልዩ ልዑክ በመመደብ በተቻለ መጠን ሁለቱም ላይ ጫና በመፍጠር የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ቻይናም እንዲሁ፡፡
በአጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢጋድን አቋምና ጥረት በመደገፍ በአንድ ድምፅ እየተናገረ ነው ያለው፡፡ ይህ ሁሉ ጥሪ አንድና አንድ ነው፡፡ ኢጋድ የሚያደርጋቸው ጥረቶችን ሁሉ እንደግፍ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ በጥባጮች እንዳይኖሩ ነው፡፡ የኢጋድን ስሜት የሚፃረር ስሜት መደረግ የለበትም የሚል ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን እንደተጠቀሰው አንዳንድ ኃይሎች በጉዳዩ ጣልቃ መግባታቸው እምብዛም የኢጋድን ጥረት የረዳ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ድርድሩ ተቋርጧል ይባላል፡፡
አምባሳደር ዲና፡- ድርደሩ አሁንም ቀጥሏል፡፡ የፕሬዚዳንቱም ሆነ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ልዑካን በሙሉ እዚሁ ሸራተን አዲስ ነው ያሉት፡፡ አሁን ሁለት ሳምንት ሆኖአቸዋል፡፡ መጀመሪያ አደራዳሪዎቹን የሚያገኟቸው በተናጠል ነበር፡፡ አጀንዳውንና የድርድሩን አካሄድ ካፀደቁ በኋላ ድርድሩን በጋራ ነው የሚያደርጉት፡፡ በዚህም አደራዳሪዎቹ በመሀል ወደ ጁባ በመሄድ ከአንዴም ሁለቴ ሁለቱን መሪዎች በአካል እያገኙ አነጋግረዋል፡፡ እነዚሁ አደራዳሪዎች ባቀረቡባቸው ምክረ ሐሳቦች በተለይ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል በሚል በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዲለቀቁ እንደ ቅድመ ሁኔታ የቀረበው ሐሳብ አንድም ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ያገደ ነገር ነው፡፡ በመንግሥት በኩል በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተመረጠ መንግሥት በመጣል ሕገወጥ የሚባል መፈንቅለ መንግሥት ያደረጉ ስለሆነ መቀጣት አለባቸው የሚል አቋም ነው ያለው፡፡ በዚያኛው ወገን በኩል የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ አልተደረገም የሚል ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ድርድሩና መገናኘቱ ቀጥሏል፡፡ ግን እንደሚጠበቀው እየሄደና የተፈለገውን ውጤት በሚፈለገው ጊዜ እያመጣ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ኢጋድ አንድ አቅጣጫ ያስቀመጠው፡፡ ከተሳካለት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ይፈራረማሉ የሚል ተስፋ ነበረ፡፡ አሁን ሳምንቱ እየተገባደደ ነው ያለው፡፡ [መግለጫው የተሰጠው ዓርብ ጠዋት ነበር]፡፡ በሌላ በኩል ኢጋድ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው፡፡ ድርድሩን ማቋረጥ አማራጭ አይደለም፡፡ ድርድሩ አልተቋረጠም፡፡ ቀጥሏል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢጋድ አባል የሆነው የኡጋንዳ መንግሥት በደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈጸሙ እየተነገረ ነው፡፡ ኢጋድ ምን ያህል የጋራ አቋም አለው?
አምባሳደር ዲና፡- አጠቃላይ ሥዕል አለ፡፡ ሁሉም አገሮችና እዚህ አካባቢ ያሉት ኃላያን አገሮች በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተለያየ ጥቅም አላቸው፡፡ ለቅድስና ጣልቃ የሚገባም አይኖርም፡፡ የሚሰላ ጥቅም አለ፡፡ ከዚያ አንፃር እንቅስቃሴያቸው የሚያተኩረው ማን ያሸንፋል? ሚዛኑ ወዴት ያጋድላል? ላይ መሠረት ያደረገ የተለያየ አካሄድ ነው ያላቸው፡፡ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ሁሉንም አንድ የሚያደርግ ነገር በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መኖር አለበት፡፡ ለኢነርጂም ሆነ ለሌላ የፖለቲካ ፍላጐት፣ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቅርበት ይኑረው ወይም ከተቃዋሚውም ጋር ቅርበት ይኑረው፣ ቅድሚያ የሚሰጫቸውና ሁሉንም የሚያስማሙ ነገሮች ኢጋድ እያላቸው ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ሰላም መኖር አለበት፤ ተኩስ መቆም አለበት፡፡ የፖለቲካ መፍትሔ መደረግ አለበት የሚል ነው፡፡ ይህ ለሰሜን ሱዳንም የኢጋድ አባል አገር ሆኖ ጣልቃ ገብነቱ እየተወራበት ላለው አገርም [ኡጋንዳ] ይሠራል፡፡ ምክንያቱም ለሰሜን ሱዳን ከ90 በመቶ በላይ የነዳጅ ፍጆታ የሚመጣው ከዚሁ ከግጭቱ አካባቢ ነው፡፡ አካባቢው ላይ ግጭት ካለ የነዳጅ ዘይት ፍሰቱ ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ሱዳኖች መካከል [በተለይ ኢትዮጵያ ብዙ የመሸምገል ሥራ የሠራችበት] አንዱ ትልቁ ችግር ሲፈጥር የነበረው የዘይት መስመሩ ነው፡፡ ይኼ ከተዘጋ ሰሜን ሱዳን ቀውስ ውስጥ ነው የሚነሳው፡፡ እናም የእያንዳንዱ አገር ጥቅም ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ ዞሮ ዞሮ ለኢጋድ የጋራ የሆነው ጉዳይ የደቡብ ሱዳን መረጋጋት ነው፡፡ አለበለዚያ አንድ አገር የፈለገ አጀንዳ ቢኖረው ምንም ማሳካት አይቻልም፡፡ ያንን ለማምጣት ግን መንገዱ ሊለያይ ይችላል፡፡ በኃይል እንሂድበት የሚል ወገን አለ፡፡ አንዱ ወገን እንዲያሸንፍ የሚጣጣርም አለ፡፡ በኢጋድ አቋም ደግሞ ወገንተኝነቱ አያዋጣም የሚል ነው፡፡
ሌላው ይኼ ችግር የጐሳ ገጽታ በመያዙ ደግሞ አደጋው ከፍተኛ ነው፡፡ በጐሳ ጦርነት ውስጥ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም፡፡ ሁለቱም ናቸው የሚሸነፉት፡፡ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ደቡብ ሱዳን አዲስ አገር ከመሆኗ አንፃር ደግሞ ግጭቱ ሙሉ ለሙሉ ከቀጠለ ራስን ማጥፋት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ላይ ጫና እየተፈጠረ ያለው ራስን ማጥፋት አትፈጽሙ የሚል ነው፡፡ ተቃዋሚም መንግሥትም ራሳችሁን እየገደላችሁ ነው የሚለውን ነገር ነው ኢጋድ እየገፋበት ያለው፡፡ የኢጋድ ጥንካሬ እንደምታውቁት ከሌሎች የአፍሪካ አካባቢ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ልዩነት አለው፡፡ በውስጡ ግን ብዙ በጥባጮች አሉ፡፡ ወጥቶ ከዳር ሆኖ የሚመለከት አካልም አለው፡፡
ሪፖርተር፡- እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጐች እንዲወጡ በእስራኤል በኩል ግፊት እየተደረገ ነው፡፡ ዜጐቹም ለተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተዋል፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ ነው?
አምባሳደር ዲና፡- ይህንን በተመለከተ ይህን ያህል ቁጥር በውል እንዲወጣ ተብሎ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ በውል የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በደቡብ ሱዳንም በሳዑዲ ዓረቢያም እንደተደረገው ኢትዮጵያ ዜጐቿን የመቀበል ኃላፊነት አለባት፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment