ሁለት የጎዳና ልጆች የገና ዋዜማ አመሻሽ ላይ፣ ጎዳና ዳር ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚው ለዓመት በዓሉ ሲራወጥ ያያሉ፡፡ ዶሮ ያንጠለጠለ፣ በግ የሚጎትት፣ ቄጤማ የቋጠረ፣ በሬ የሚነዳ፣ እህል ያሸከመ፣ ‹የገና ዛፍ› የተሸከመ፣ አብረቅራቂ መብራት የጠቀለለ፣ ዋዜማ ሊቆም ወደ ቤተ ክርስቲያን ነጭ ለብሶ የሚጓዝ፣ ምሽቱን በዳንስ ሊያሳልፍ ሽክ ብሎ ወደ ጭፈራ ቤት የሚጣደፍ፣ ብቻ ምኑ ቅጡ፣ ከተማዋ ቀውጢ ሆናለች፡፡
እነርሱ ደግሞ የተበጫጨቀች ልብስ ለብሰው፣ የደረቀ ዳቦ ይዘው፣ በቢል ቦርድ ላይ የተለጠፈውን የጥሬ ሥጋ ሥዕል እያዩ፣ መጣሁ መጣሁ የሚለው የገና ብርድ እያቆራመዳቸው፣ የቆሸሸ ሰውነታቸውን እየፎከቱ፣ የቀመለ ፀጉራቸውን እያከኩ፣ በታኅሣሥ 15ና በታኅሥ 29 መካከል ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው፣ የበግ ድምጽ እንጂ ሥጋው ርቋቸው፣ የበሬው ፎቶ እንጂ ሥጋው ጠፍቶባቸው፣ ያገኙትን ወረቀት እያነደዱ ጎዳናው ዳር ተቀምጠዋል፡፡
‹‹ቆይ ግን ገና ምንድን ነው?›› አለ አንደኛው ሰውነቱን እየፎከተ፡፡
‹‹የክርስቶስ ልደት ነዋ፤ በማይክራፎን ሲሰብኩ የሰማሁት እንደዚያ ነው››
‹‹እኛምኮ እንደርሱ የሚያስጠጋን አጥተን ነው ጎዳና የወደቅነው፡፡ እንደርሱ ራቁታችንን ነን፤ እንደርሱ የሚበላ የለንም፤ እንደርሱ እኛንም የሚያሞቁን እነዚህ ውሾች ናቸው፤ እንደርሱ እንደርሱ እኛም በተናቀው ቦታ ላይ ነን›› አለ ሁለተኛው ልጅ ውሻውን እየደባበሰ፡፡
‹‹የሚገርምህ ነገር ጌታ የተወለደው በከብቶች በረት ዋሻ ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ጥድ የለም፤ በረት እንጂ፡፡ ጌታኮ ጫካ ውስጥ አልተወለደም፡፡ ያኔ ከረሜላ የለም፤ ያኔ ጥጥ የለም፣ ያኔ ፖስት ካርድ የለም፣ የሰብአ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ እንጂ፡፡ አሁን ይኼን ሁሉ ከየት እንዳመጡት እንጃ፡፡ ይልቅስ ራቁታችንን ሆነን፣ የሚበላ ናፍቆን፣ በእንግዶች ማረፊያ ሥፍራ የሚሰጠን አጥተን፣ ከእንስሳት ጋር ተኝተን እኛ አለንላቸው፡፡ ገናኮ መከበር የሚገባው ከእኛ ጋር ነበር፡፡ ገና የሀብታሞች ሳይሆን የድኾች፣ የተከበሩ ሳይሆን የተዋረዱ፣ ቤት ላላቸው ሳይሆን ማደርያ ያጡ፣ ዘመድ ያላቸው ሳይሆን ወገን ያጡ ሰዎች በዓል ነው፡፡ ገና የሚወርዱበት እንጂ የሚወጡበት በዓል አልነበረም፡፡››
‹‹እኔም እሱን እያሰብኩ ነበር፡፡ ተመልከት ያኔ የዘመሩትን እረኞች አሁን ማንም አያስታውሳቸውም፡፡ ያኔ የቤተልሔም ሰዎች በጥጋብና በዕንቅልፍ ተወስደው አላስጠጋው ሲሉ በረታቸውን የሰጡት ከብቶች ነበሩ፡፡ አሁን የእነርሱ ዋጋ መታረድ ሆነ፡፡ በዓሉኮ የከብቶች በዓል ነበረ፡፡ እኔ ከብቶች ውለታ በዋሉበት፣ ከሰው የሚበልጥ ሥራ በሠሩበት በገና ቀን መታረዳቸው ይገርመኛል፡፡››
‹‹አይግረምህ፤ በሰው ልጅ ታሪክ ሁሉ እንደዚህ ነው፡፡ ታሪክ የሠሩትና መሥዋዕትነት የከፈሉት ምንጊዜም መሥዋዕት እንደሆኑ ናቸው፡፡ በኋላ የሚጠቀመው ታሪክ ሠሪው አይደለም፤ ታሪክ ተራኪው ነው፡፡ ‹የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ› የተባለው ዝም ብሎ እንዳይመስልህ፡፡ አንተ በሠራኽው ታሪክ አንተን አርደው ያንተን በዓል የሚያከብሩ ሞልተዋል፡፡››
‹‹እርሱማ አታይም እንዴ፤ በኛ በድኾች ስም ይለመናል፤ ብር ይሰበሰባል፤ እኛ በፊልም እየተቀረጽን ታሪኩን እንሠራዋለን፤ በኋላ ግን እኛው ራሳችን በድህነት ቢላዋ እንታረድና የኛን በዓል ሌሎች ያከብሩልናል፡፡ ታሪኩን የሚሠሩት እረኞች፣ አበሉንና ደመወዙን የሚበሉት ግን የቤተልሔም ሰዎች፡፡ አንተ ፖስት ካርድ ብቻ ሆነህ ትቀራለህ፡፡ እስኪ የገናን በዓል ተመልከት፡፡ እረኞቹ የታሉ፤ በረቱ የታለ፤ ከብቶቹ የታሉ፤ ከሩቅ ሀገር የመጡት የጥበብ ሰዎች የታሉ፤ ጌታ የተኛበት የእንጨት ርብራብ የታለ፡፡ ሁሉም የሉምኮ፡፡ የእረኞቹን ቦታ ተኝተው የነበሩት የቤተልሔም ሰዎች ወስደውታል፤ የበረቱን ቦታ የገና ዛፍ ወስዶታል፤ የጥበብ ሰዎችን ቦታ የገና አባት ተረክቦታል፤ የከብቶቹን ታሪክ ሰባኪዎቹና ዘማሪዎቹ፣ ፓስተሮቹና ቄሶቹ ወስደውታል፤ የመላእክቱ ዝማሬ በጭፈራ ቤቶቹ ዘፈን ተተክቷል፡፡ ከብቶቹንም፣ እረኞቹንም፣ ሰብአ ሰገልንም፣ በረቱንም፣ መላእክቱንም፣ የምታገኛቸው ፖስት ካርድ ላይ ብቻ ነው፡፡››
‹‹የሚገርመኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ፤ በዚህ መንገድ ዳር በተሰቀለ ትልቅ ቴሌቭዥን ላይ ሳይ፣ የሃይማኖት አባቶች ‹በዓሉን ከተቸገሩት ጋር በማክበር አሳልፉት› ሲሉ እሰማለሁ፡፡ አንዳቸውም ግን ከመናገር ባለፈ ከተከበረ መንበራቸው ወርደው ከእኛ ጋር ሲያሳልፉ አይታዩም፡፡ ‹ክርስቶስ ከሰማያት ወረደ› ማለት እንጂ መውረድ ለካስ ከባድ ነው፡፡››
‹ካመጣኸውማ ገናኮ የመውረድ በዓል ነበር፡፡ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወረደ የሚባልበት በዓል ነበር፡፡ አሁን ግን የሚወጣ እንጂ የሚወርድ የለም፡፡ ወደ እኛ የሚወርድ የለም፡፡ ሰው አምላክ መሆን ቢያቅተው አምላክ ሰው ሆነ ይላሉ፡፡ እኛ እንደነርሱ መሆን አቅቶናል፤ ታድያ ምናለ እነርሱ እንደኛ ቢሆኑ፡፡ በጣም የሚገርመው ሰብአ ሰገል ስጦታ የሰጡት ራቁቱን ለነበረው፣ ቤት ላጣው፣ የቤተልሔም ሰዎች አላስጠጋ ላሉት፣ ከሰው ወገን ጠያቂ ላልነበረው ለክርስቶስ ነበረ እንጂ ሁሉ በእጃቸው፣ ሁሉ በደጃቸው ለሆኑት ለቤተልሔም ሰዎች አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ስጦታው ለቤተ ልሔም ሰዎች ሆነ፡፡››
‹አንድ ቀን አንድ ሰው ሲያስተምር ምን ሰማሁ መሰለህ፡፡ ክርስቶስ ‹ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም› ይላል፡፡ የሰሙት ሰዎች ‹የት አግኝተን እናብላህ እናጠጣህ› ቢሉት ‹ለታናናሾቹ ካላደረጋችሁ ለእኔ አላደረጋችሁትም፣ ለታናናሾቹ ካደረጋችሁ ለእኔ አድርጋችሁታል› አላቸው አሉ፡፡ ታድያ ከኛ የባሰ ታናሽ ማን አለ? ያኔምኮ ክርስቶስ ተራ፣ ድኻ፣ እዚህ ግባ የማይባልና የተናቀ መስሎ ስለመጣ ነው የቤተልሔም ሰዎች ያላስጠጉት፡፡ ዛሬስ ድንገት ከእኛ መካከል ቢኖርስ፣ እዚህ ጎዳና ዳር ከውሾቹ ጋር ተኝቶ ቢሆንስ፤ በገዛ የልደቱ ቀን ሰዎች እርሱን ንቀው እያለፉ፣ ተጸይፈው እያለፉ፣ በጽድና በከረሜላ፣ በበግና በዶሮ፣ በጠላና በጠጅ፣ በፖስት ካርድና በስጦታ የራሱን በዓል እያከበሩለት ቢሆንስ፤ ››
‹ማን ያውቃል ወዳጄ፤ ሰው እንደሆነ በዓሉን እንጂ ራሱን ክርስቶስን የሚፈልገው አልመሰለኝም፡፡ ቢፈልጉት ኖሮማ አንድ ጥድ የሚገዙበት እኛን አልብሶ ‹ታርዤ አላለበሳችሁኝም› ከሚለው ያወጣቸው ነበር፤ የአንድ ፖስት ካርድ ዋጋ ለኛ የወር የቤት ኪራያችን ነበር፤ በጉን በልተው እንኳን ቆዳውን ቢሰጡን ለኛ የዓመት ቀለብ ነበር፤ ለከረሜላው የሚወጣው ገንዘብ የኛን የዓመት ጤና ይጠብቅ ነበር፡፡ አሁንማ የበዓሉ ምክንያት ተረስቶ በዓሉ ብቻ ቀርቷል፡፡››
‹‹እና አሁን ገና እየተከበረ ይመስልሃል››
‹‹ምን እየተከበረ ነው፤ እየተቀበረ ነው እንጂ››
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው
Source: Danielkibret
No comments:
Post a Comment