Sunday, January 12, 2014

የመንግሥት ሠራተኞችን የደመወዝ ስኬል ለማሻሻል አገር አቀፍ ጥናት ተጀመረ

‹‹አሁን ያለው የደመወዝ ስኬል ለሠራተኞች መልቀቅ ምክንያት ነው›› አቶ ሙክታር ከድር
የመንግሥት ሠራተኞች በአንድ ተቋም ተረጋግተው ያለመሥራታችው መሠረታዊ ምክንያት በሥራ ላይ ያለው የደመወዝ ስኬል አነስተኛነት መሆኑን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ሙክታር ከድር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጹ፡፡
የመንግሥት ሠራተኞችን የደመወዝ ስኬል ለማሻሻል አገር አቀፍ ጥናት ተጀመረ
የደመወዝ ስኬሉን ለማሻሻል አገር አቀፍ ጥናት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ 
በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ሙክታር ከድር ባለፈው ሐሙስ የሚኒስቴሩን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች በመለሱበት ወቅት፣ የደመወዝ ስኬሉ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑንና በጥናት ላይ በመመሥረት መከለስ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች ፍልሰት ምክንያት ምን እንደሆነና ችግሩን ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ምን እያደረገ እንደሆነ ተጠይቀው፣ ‹‹የደመወዝ ስኬል ችግር ባልተፈታበት ሁኔታ የፍልሰት ችግሩን መቅረፍ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡
 አሁን በሥራ ላይ ያለው የደመወዝ ስኬል ከ69 በላይ ደረጃዎች እንዳሉትና ይህም የችግሩ መገለጫ እንደሆነ አቶ ሙክታር አስረድተዋል፡፡
‹‹ለመንግሥት ሠራተኞች በአንድ ተቋም ውስጥ ያለ መርጋት መሠረታዊ ምክንያት የደመወዝ ስኬል ስለሆነ መስተካከል ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡ 
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ከፌዴራል መንግሥትና ከክልል ሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ተመሥርቶ ጥናት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ 
የጥናቱ ዓላማ የሠራተኞች ደመወዝ ስኬልን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓትን መዘርጋት ያለመ እንደሆነ ማለትም ሠራተኞች የሚመዘኑበት፣ ደረጃ የሚሰጥበት፣ ከዚህም ጋር የተያያዘ ደመወዝ የሚፈቅድበት ዘመናዊ አሠራርን መፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 
የተደራጀው ቡድን ጥናቱን የሚያከናውነው በአገር አቀፍ ደረጃ በመሆኑ የጥናቱ ውጤት በውጭ ባለሙያዎች ተገምግሞ ቀጣይነት ካገኘ በኋላ፣ የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ሥራ ውስጥ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ለፓርላማው አስረድተዋል፡፡ 
የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ተግባር በቀጣዩ ዓመት እንደሚጀመር አቶ ሙክታር አውስተው፣ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘው የሲቪል ሠራተኞች የደመወዝ ስኬል 69 ደረጃዎች ስላሉት፣ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ደረጃዎቹ ከአምስት እስከ አሥር ብቻ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ 
ይህ የደመወዝ ስኬል ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ለከፍተኛ ወጪ የተዳረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ፣ የትራንስፖርት ኤጀንሲ በመንግሥት እንዲቋቋም ተወስኖ ወደ ሥራ እየተገባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 
የትራንስፖርት ኤጀንሲው 1.5 ቢሊዮን ብር ተመድቦለት በአሁኑ ወቅት 460 አውቶቡሶችን ለመግዛት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ 
የትራንስፖርት ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ለሚገኙ የመንግሥት ሲቪል ሠራተኞች (የፌዴራልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ተቋማት) አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነና አገልግሎቱም ከወጪ መቀነስ አንፃር ብቻ ሳይሆን ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡  
  

No comments:

Post a Comment