የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ኩባንያ ለሆነው ለሁዳ ሪል ስቴት ሰጥቶት የነበረው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መምከኑንና መሬቱም ወደ መሬት ባንክ መግባት ቢኖርበትም፣ ኩባንያው ፈቃደኛ ሆኖ እንዳልተገኘ ምንጮች ገለጹ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኅዳር 2005 ዓ.ም. የሁዳ ሪል ስቴት መሬት እንዲነጠቅ የጻፈውን ደብዳቤ መሠረት በማድረግ፣ የልደታ ክፍለ ከተማ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘውን የኩባንያውን መሬት አምክኗል፡፡
ክፍለ ከተማው ለኩባንያው ተሰጥቶ የነበረው መሬት ከአሥር ዓመታት በላይ ታጥሮ ሳይሠራበት በመቆየቱ ለሌላ ልማት ለማዋል ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም፣ ሁዳ ሪል ስቴት ፈቃደኛ ባለመሆኑና ቅሬታውንም ለከተማው አስተዳደር በማቅረቡ ጥረቱ ሊሳካ እንዳልቻለ ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ካርታው ሊመክን የቻለበትን ምክንያትና የሁዳ ሪል ስቴትን ቅሬታ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክፍለ ከተማው ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ሁዳ ሪል ስቴት በ1997 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከተማ አተዳደር ሜክሲኮ አደባባይ ፊት ለፊት ከዋቢ ሸበሌ አጠገብ 6,400 ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቦ ነበር፡፡
ሁዳ ሪል ስቴት በዚህ ቦታ ላይ ከፍታቸው 20 ፎቅ የሆኑ መንታ ሕንፃዎችን ለመገንባት አቅዶም ነበር፡፡ የሕንፃዎቹ ዲዛይን ከመሠራቱ በተጨማሪ የሁዳ ሪል ስቴት እህት ድርጅት ሚድሮክ ፋውንዴሽን አልፎ አልፎ ቁፋሮ ሲያካሂድ ነበር፡፡
ነገር ግን ፕሮጀክቱ ላለፉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ መሆን አልቻለም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜክሲኮ አደባባይን መሬት ጨምሮ የዚሁ ኩባንያ ይዞታ የሆነው መሀል ፒያሳ ላይ የሚገኘው መሬት ላለፉት 16 ዓመታት ታጥሮ ቢቀመጥም፣ ዝምታን መምረጡ ከነዋሪዎች ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፍትሕ ሚኒስትር የሆኑት የቀድሞው የከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አምባዬ በተለይ ሜክሲኮ አደባባይ የሚገኘው የሁዳ ሪል ስቴት መሬት እንዲነጠቅ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን እንዲነጠቅ ትዕዛዝ ከተላለፈ አንድ ዓመት ቢቆጠርምና ክፍለ ከተማውም በዚህ ውሳኔ መነሻ ካርታውን ቢያመክንም፣ ይዞታው ወደ አስተዳደሩ መሬት ባንክ ገብቶ ለሌላ ልማት ዝግጁ አለመሆኑ ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተሉ አስገራሚ ሆኗል፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ምንጮች እንደሚጠቅሱት፣ አንድ ቦታ ካርታው ከመከነ ባለቤትነቱ ወዲያውኑ ያበቃል፡፡ ነገር ግን የሁዳ ሪል ስቴት መሬት እንዲህ ዓይነት አሠራር ውስጥ ሊገባ አልቻለም ይላሉ፡፡
ይህንኑ ሲያጠናክሩም የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት በቡናና ሻይ ሕንፃ በኩል ያልፋል፡፡ ለግንባታው መንገዱ በመፍረሱ ነዋሪዎች እየተጠቀሙ ያሉት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት ያለውን መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በነዋሪዎች በመጨናነቁ ሁዳ ሪል ስቴት ያጠረውን አጥር በተወሰነ ደረጃ ወደ ውስጥ አስገብቶ እንዲያጥር ቢነገረውም ፈቃደኛ መሆን አልቻለም፡፡
በሁዳ ሪል ስቴት ፈቃደኛ አለመሆን ደስተኛ ያልሆነው የልደታ ክፍለ ከተማ ኃይል ተጠቅሞ መንገዱን እንዳሰፋው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment