Wednesday, January 1, 2014

ሥራ ማግኘት አልቻልንም ያሉ የቻይና ኩባንያዎች ቅሬታቸውን ለመንግሥት አቀረቡ

ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተን እንዳንሠራ እንቅፋት ተፈጥሮብናል የሚሉ 18 የቻይና ኩባንያዎች ቤጂንግ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡ ኩባንያዎቹ የቅሬታቸው መሠረት የሆነው ቀደም ብለው ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡ የቻይና ኩባንያዎች፣ ከአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ሥራ እንዳናገኝ እንቅፋት ፈጥረዋል የሚል ነው፡፡

ኩባንያዎቹ ታኅሣሥ 9 ቀን 2006 ዓ.ም. የጻፉት ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ በግልባጭ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ለቻይና ንግድ ሚኒስቴር ተልኳል፡፡ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ በእነዚህ 18 ኩባንያዎች ይፋ የተደረገውን ይህንን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥንቃቄ እንደያዘው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢ ኩባንያዎቹ የተሰማሩባቸው መስኮች የኃይል፣ የመስኖ፣ የመንገድና የንፁህ የመጠጥ ውኃ ግንባታዎች ናቸው፡፡
በእነዚህ የመሠረተ ልማት ዘርፎች የተሰማሩት የቻይና ኩባንያዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰኑ ባለሥልጣናት ቀደም ብለው ለገቡ የቻይና ኩባንያዎች ያለ ውድድር ሥራ እንደሚሰጡዋቸው፣ ደካማ የሥራ አፈጻጸም እያለባቸውም አንዱን ሥራ ሳይጨርሱ ተጨማሪ ሥራዎችን በላይ በላዩ ይሰጧቸዋል የሚል ቅሬታቸውን ለመንግሥት አቅርበዋል፡፡
ጥቂት ነባር የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን የመያዝ ከቻይና መንግሥት በሚገኝ ብድር የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን የመቆጣጠር አዝማሚያ እያሳዩ ነው ሲሉ፣ አዳዲሶቹ ኩባንያዎች በዚህ ምክንያት ሥራ ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡
እነዚህ ጥቂት ኩባንያዎች ሥራዎችን የሚያገኙት ከተወሰኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ነው የሚሉት እነዚህ ኩባንያዎች፣ ለሌሎች ኩባንያዎች ክፍት ሳይደረግ በቀላሉ በቢሊዮን የሚቆጠር ዋጋ ያለው ሥራ ይሰጣቸዋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ይህንን ጉዳይ በቅርበት የሚያውቁ ምንጮች፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት አንዳንድ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ቻይና ኤምባሲ ውስጥ ቦታ ያላቸው ግለሰቦችም ለተወሰኑ የቻይና ኩባንያዎች እንደሚያዳሉ ያስረዳሉ፡፡
ሌሎቹን በመግፋት የተወሰኑትን የሚተባበሩ በመሆኑ ብዙኃኑ የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ማግኘት እንዳይችሉ መደረጉንም በደብዳቤያቸው ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያጣ ከመደረጉም በላይ፣ ተስፋ የተጣለባቸው ፕሮጀክቶች ደካማ አፈጻጸም ባላቸው ኩባንያዎች እጅ እየወደቁ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
ቅሬታ አቅራቢ የቻይና ኩባንያዎች ከዚህም በጥልቀት በመሄድ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኩባንያዎቹ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡት አብዛኞቹ የቻይና ኩባንያዎች አነስተኛና መለስተኛ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብለው በመግባታቸው በሩን እንደዘጉባቸውና ይህንንም ጉዳይ የቻይናና የኢትዮጵያ መንግሥታት ተረድተው መፍትሔ እንዲሰጧቸው በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment