- ግብፅ ግድቡን የሚከታተል ቢሮ በአዲስ አበባ ለመክፈት ጠየቀች:: የኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን ግድቡን በተመለከተ እያደረጉት የሚገኘውን ድርድርና በግብፅ በኩል እስካሁን እየተነሱ ያሉ ጉዳዮችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ቀረበ፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑና በሚኒስቴሩ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ አነሳሽነት በተፈጠረው መድረክ የግብፅ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ የውኃ ሚኒስትሮች ግድቡን በተመለከተ መግባባት ላይ ለመድረስ በድርድር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ድረስም የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮችና የባለሙያዎች ቡድን ሁለት ጊዜ በሱዳን በመገናኘት መደራደራቸውን አቶ ፈቅ ገልጸዋል፡፡ በሁለት ዙር በተደረገው የሦስቱ አገሮች ድርድር፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጥቅም በሚያስከብሩ ሐሳቦች ላይ መስማማታቸውን አቶ ፈቅ ተናግረዋል፡፡
ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊነት የሚከታተል ኮሚቴ በሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ብቻ እንዲሆንና የኮሚቴው ሥልጣንና ኃላፊነት ይገኝበታል፡፡
ድርድሩ በቀጣይም የሚከናወን ሲሆን፣ በግብፅ በኩል እየቀረቡ የሚገኙና ኢትዮጵያ በጭራሽ ልትቀበላቸው የማትችላቸው ሐሳቦችም ለምክር ቤቱ ሪፖርት ተደርገዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ግብፅ የቀድሞው የውኃ ድርሻዋ እንዲከበርላት አሁንም በድርድሩ ውስጥ እያነሳች ሲሆን፣ የህዳሴው ግድብን ራሷ መከታተል እንደምትፈልግና ይህንንም የሚያስፈጽም ቢሮ በአዲስ አበባ ለመክፈት መጠየቋ ይገኝበታል፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር እየተወጡ ያለውን ተግባር ፓርላማው አድንቋል፡፡ በተለይም ለብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን መላ አባላትና ለዋና ሰብሳቢው ዶ/ር ስለሺ በቀለና ለምክትል ሰብሳቢው ዶ/ር ያቆብ አርሳኖ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የኢትዮጵያ ተወካይ ለሆኑት ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው ከፍተኛ ምሥጋና ከፓርላማው ተችሯቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ በማያያዝም የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሩዋንዳ ማፅደቋን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታንዛኒያ ለፓርላማ መላኳን የኬንያ፣ የብሩንዲና የኡጋንዳ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment