Saturday, December 28, 2013

ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት የፌዴራል ፖሊስ አባል ቅጣት ተወሰነባቸው

-ለ30 ዓመታት ማገልገላቸውን ተናገሩ
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 449(1)ሀን በመተላለፍ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛን በማመነጫጨቅ፣ የፍርድ ቤትን ክብር በመንካትና ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት የፌዴራል ፖሊስ አባል ኢንስፔክተር ሙሉ አሰፋ፣ በስድስት ወራት ቀላል እስራት እንዲቀጡ ታኅሣሥ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ውሳኔ ተላለፈባቸው፡፡ 
የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውንና ላለፉት 30 ዓመታት ከበረሃ ጀምሮ በውትድርና ዓለም ተሰማርተው በነበሩበት ወቅት፣ አንድም የወንጀል ድርጊት ፈጽመው እንደማያውቁ፣ የቅጣት ውሳኔውን ላስተላለፈባቸው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር የቤተሰብ ችሎት ያስረዱት ኢንስፔክተር ሙሉ፣ በወቅቱ (ታኅሣሥ 11 ቀን 2006 ዓ.ም.) ከሥራ ጋር በተያያዘ ተበሳጭተው በነበሩበት ወቅት ችሎቱን መረበሻቸውን አምነዋል፡፡
‹‹ለችሎቱ መታዘዝና ክብሩንም መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ይኼንን ባለማድረጌ ጥፋተኛ ነኝ፤ ተፀፅቻለሁ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፤›› በማለት ችሎቱን ተማፅነው ነበር፡፡ 
ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ መሆናቸውን ብይን የሰጠበት የወንጀል ሕግ 449(1)ሀ፣ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ቀላል እስራት ወይም ከ3,000 ብር ባልበለጠ የገንዘብ ቅጣት የደነገገ በመሆኑ፣ ኢንስፔክተር ሙሉ ጥፋተኛ ለተሰኙበት ፍርድ ቤት የመድፈር ወንጀል ድርጊት፣ በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት ላይ ብይን ከተሰጠ በኋላ የሚያዋጣው ጥፋትን አምኖ [ተፀፅቻለሁና ይቅርታ ይደረግልኝ ሳይሆን ተገቢ የሆነ የቅጣት ማቅለያ ማቅረብ ነው]  በሚል የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

በመሆኑም ኢንስፔክተር ሙሉ የሚያዋጣቸውንና ጥፋተኛ ለተባሉበት ወንጀል ቅጣት ማቅለያ ያግዘኛል ያሉትን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ለፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ከጥፋቴ ተምሬያለሁ፡፡ የሦስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ እስካሁን ለ30 ዓመታት ስሠራ አንድም ቀን የወንጀል ድርጊት ፈጽሜ አላውቅም፤›› ብለው የቅጣት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ የዘወትር ፀባያቸው መልካም እንደነበር፣ ጥፋት የፈጸሙትም ባልታሰበና በድንገተኛ አጋጣሚ መሆኑን ለመረዳት መቻሉንና ይኼም በወንጀል ሕግ 82(1)ሀ መሠረት በቅጣት ማቅለያነት እንደሚያዝላቸው አስታውቋል፡፡ የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውንም ከግምት ውስጥ ማስገባቱን አክሏል፡፡
የፍርድ ቤቱን ሕገ መንግሥታዊ ክብር ለመጠበቅና ለማስጠበቅ፣ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ (በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት) ተገኝተው የነበሩት ኢንስፔክተር ሙሉ፣ ተቃራኒ ተግባር በመፈጸማቸው ችሎቱን አውከው እንደነበር አስታውሶ፣ ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ ከግምት ውስጥ በማስገባት ያርማቸዋል፣ ያስተምራቸዋል በማለት ባመነበት በስድስት ወራት ቀላል እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ኢንስፔክተር ሙሉ ታኅሣሥ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር የቤተሰብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 208437 ላይ ምስክሮችን በመስማት ላይ እያለ፣ ከፊት ለፊቱ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊሶች መቆያ ክፍል በረንዳ ላይ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከፍተኛ ድምፅ እያሰሙ በማወካቸው፣ ፍርድ ቤቱ ድምፅ እንዲቀንሱ ሲጠይቃቸው ለፍርድ ቤቱ ታዛዥ ባለመሆናቸው በችሎት ቀርበው እንዲነገራቸው ቢጠሩም፣ ‹‹አንቀርብም›› ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ፍርድ ቤቱ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በመንገር እንዲያቀርቧቸው ቢያዝም፣ ከመቅረብ ይልቅ ኢንስፔክተር ሙሉ ችሎት ገብተው ለዳኛ ተገቢ ያልሆነ ምላሽ በመስጠት ‹‹አልፈተሽም፣ ስሜንም አልናገርም፤›› ብለው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ በዕለቱ በከፍተኛ ጥረት ቀርበው ቃል እንዲሰጡ ከተደረጉ  በኋላ ወዲያው ፍርድ ቤቱን በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ብይን እንደተሰጠባቸውና በእስር ላይ እንደሚገኙ ባለፈው ረቡዕ ዕትም ጋዜጣ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
via: 

No comments:

Post a Comment