Tuesday, December 31, 2013

ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሐሙስ በአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ይሰበሰባል

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት ስምንት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ፣ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሐሙስ እንደሚሰበሰብ ፍርድ ቤት ትናንትና አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ የአቶ መላኩ ፈንታን ክስ የማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት የትኛው እንደሆነ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም በመስጠት እንዲያሳውቀው ለሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን ትዕዛዝ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በመሆኑም ሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተግባራዊ ማድረጉንና ያጣራውን ጉዳይ ተጠሪ ለሆነበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን ለፍርድ ቤቱ ማሳወቁን ተከትሎ፣ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን በቀረበለት ሪፖርት ላይ ውሳኔ አሳልፎ እንዲያሳውቀው ለማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለፍርድ ቤቱ ታኅሣሥ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን አቶ መላኩ ፈንታን አስመልክቶ በደረሰው ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ለሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙን እንዳሳወቀው ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ለጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment