Sunday, December 1, 2013

የንሥሐ አባት አዲሱ ሚና

በትግራይ ክልል ከመቐለ ከተማ በደቡብ ምሥራቅ 35 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ሕንጣሎ ወጀራት ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ሞቃታማዋና ነፋሻማዋ ሃገረ ሰላም ቀበሌ አዝመራዋ ሰምሮላታል፡፡
“እህልን በጥቅምት ልጅን በጡት” እንደሚባለው ጤፍን ጨምሮ ሌላው ሰብል ለመታጨድ የሳምንታት ጊዜ ቀርተውታል፡፡ በአጨዳው የአካባቢው ፀጥታ አስከባሪዎች፣ እናቶችና አባቶችን ጨምሮ አቅሙ ያላቸው በሙሉ በቡድን እየወጡ እጃቸው የተላላጠበትን ፊታቸው በነፋስና በፀሐይ የጠቆረበትን አዝመራ ይሰበስባሉ፡፡
ይህ ትብብራቸው ለአዝመራና በአዝመራ ጊዜ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያንም ሆነ ክልሉን ለምእት ዓመታት ሲፈታተን የከረመውን የእናቶችና የሕፃናት ሞት ለመቀነስ ጭምር ከእያንዳንዱ የቀበሌዋ ነዋሪ ቤት ዘልቆ የሚገባ ነው፡፡

በሃገረ ሰላም ከጥቂት ዓመታት በፊት እርጉዝ እናቶችን ወደ ጤና ጣቢያ እንዲሄዱ መምከር ከባድ ነበር፡፡ የተመከሩትም ቢሆኑ ወደ ዘመናዊ ሕክምና መሄዱን ፈጣሪን እንደማስቀየምና በፈጣሪ ሥራ ጣልቃ እንደመግባት ስለሚቆጥሩት አያደርጉትም፡፡ ቤት ውስጥ መውለድ ክብራቸውም፣ መከራቸውም ነበር፡፡ እናት በምጥ ስትያዝና ስትጨነቅ ጭስ እያጨሰ፣ ገንፎ እያገነፋ አምላክን እየተለማመነ ዘመናትን ባሳለፈ ማኅበረሰብ ውስጥ እናቶች ከቤት ወጥተውና ገላቸውን አጋልጠው በጤና ባለሙያ እንዲወልዱ ማስገንዘብና እንዲቀበሉት ማድረግ ፈተና ነበር፡፡ 
በጤናው ዘርፍ ለብዙ ዘመናት ሰፍነው የቆዩትን ችግሮች ለመፍታት መከላከልን መሠረት ያደረገ ፖሊሲ በመቅረፅ፣ ፖሊሲውን ለማስፈፀም ስትራቴጂዎች በመንደፍና እንደ አንድ ስትራቴጂ ጤና ኤክስቴንሸን ሠራተኞችን በመጠቀም መንግሥት በስፋት እየሠራበትና ለውጥ እያስመዘገበ ቢሆንም ከወሊድ ጋር የተያያዘውን የእናቶች ሞት መቀነስ ከባድ የቤት ሥራ ሆኖበታል፡፡ በተለይ በእናቶች በኩል ጤና ተቋማት ሄዶ ለመውለድ ያለውን ፈቃደኝነት ማግኘት የጤና ተቋማት ግብዓቶችን ከሟሟላት ጐን ለጐን ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ክልሎች የልማት ሰራዊትና የሴቶች ልማት ቡድን በማደራጀት ጭምር እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡
ሕዝቡ ለንሥሐ አባቱ ቃል ተገዢ መሆኑን የተገነዘበው የሕንጣሎ ወጀራት ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ደግሞ ለዘመናት በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰርጾ የቆየውን እናቶች በቤት ውስጥ መውለድ አለባቸው የሚለውን አመለካከት ለመቀየር ከዚህ ቀደም ለየት ባለ መልኩ ከሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀትና ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተጨማሪ የንሥሐ አባቶችን መጠቀም ጀምሯል፡፡ በክርስትና እምነታቸው ለጸኑት የሃገረሰላም ነዋሪዎች የንሥሐ አባት ቃል ክቡር ነው፡፡ ይፈጸማልም፡፡ ንሥሐ አባቶችም ከወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት የቀረበላቸውን “የተባበሩን” ጥያቄ በአዎንታ ነበር የተቀበሉት፡፡ 
ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ በተካሄደው የጤናው ዘርፍ ልማት መርሐ ግብር 15ኛው ዓመታዊ ግምገማ ዋዜማ በሀገረ ሰላም በተካሄደው የመስክ ጉብኝት ላይ ያገኘናቸው ቄስ ሃፍቱ ገብሩ የሃገረ ሰላም ጣቢያ ተወካይ ሊቀ ካህናትና የበለሳት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሁሉም እናቶች በጤና ተቋም መውለድ አለባቸው የሚለውን እቅድ ለማስፈጸም እያገለገሉ ከሚገኙ ካህናት አንዱ ናቸው፡፡ 
‹‹ሴቶች ከቤት ሲወልዱ መከራ ነበር፡፡ ምጥ ሲይዛቸውና ሲጸናባቸው ብረት እየተተኮሰ፣ ጅራፍ እየተመታ እኩላቸው ሲወልዱ እኩላቸው ይሞቱ ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ቀርቷል›› የሚሉት ቄስ ሃፍቱ የአካባቢው ካህናት በቤተ ክርስቲያን ከመቀደስ፣ በየንሥሐ ልጆቻቸው ቤት ፀበል ከመርጨት፣ የተጣላ ከማስታረቅና ወንጌል ከመስበክም ባለፈ ጽዳትን ጨምሮ በቀበሌዋ ልማት ሙሉ በሙሉ ተሳታፊና ማኅበረሰቡን ለልማት አንቀሳቃሽ ሆነዋል፡፡ በተለይም የንሥሐ ልጆቻቸው ልጅ ሲወልዱ በክርስትና በሞት ሲለዩ በፍትሐት ከመገኘት አልፈው በእርግዝና ጊዜ የወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ፣ በምጥ ጊዜ ጤና ጣቢያ ሄደው እንዲወልዱ እየመከሩ ነው፡፡ ይህም የጤና ኤክስቴንሽና የሴቶች ልማት አደረጃጀቶች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ይበልጥ አጠናክሮታል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከማንም በላይ ንሥሐ አባቱን ይሰማልና፡፡
አራት ልጆቻቸውን በቤት አምስተኛውን በጤና ጣቢያ የተገላገሉት የ35 ዓመቷ ወ/ሮ መብርሂት ዓለሙ ጤና ጣቢያ ሄደው ለመውለድ የቻሉት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ያስተማሯቸውን ንሥሐ አባታቸው የመከሯቸውን በመቀበል እንደሆነ ባስተርጓሚው ተስፋ ተክሌ በኩል ነግረውናል፡፡
“የንሥሐ አባቶች እየዞሩ እያስተማሩ ነው፡፡ መፀዳጃ እንድንቆፍር በጤና ጣቢያ እንድንወልድ ይመክሩናል”  ብለዋል ወይዘሮ መብርሂት፡፡
በወረዳው ከሚገኙት 22 ቀበሌዎች አንዷ የሆነችው ሃገረ ሰላም ላለፉት አራት ዓመታት አንድም እናት ከወሊድ ጋር በተያያዘ እንዳልሞተባት የሁለት ሕፃናት በማያውቁት ሁኔታ እንዳመለጣቸው የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ ገብረመድህን ፍሡሕ ተናግረዋል፡፡
እሳቸው ቀበሌውን ማስተዳደር ከጀመሩበት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ እንዳይሞቱ ለተደረገው ርብርብ የሃይማኖት አባቶችና ጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ትልቁን ሚና እንደሚወስዱ፣ የአካባቢው ነዋሪም ማንም እናት በቤት ውስጥ እንድትወልድ ዕድል መስጠት ማቆሙን ገልፀዋል፡፡ 
በ22 ቀበሌዎችና በ78 ጐጦች የተከፋፋለችው የሕንጣሎ ወጀራት ወረዳ ዋና ከተማ አዲጉደም ደግሞ ልዩ ተሞክሮ አላት፡፡ በከተማዋ የሚገኘው የአዲጉደም ጤና ጣቢያ ከክሊንተን ፋውንዴሽን ባገኘው ሶፍትዌር አማካይነት ስለ እያንዳንዷ እርጉዝ እናት የሕክምና ቀጠሮ ቀን ለጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የሞባይል መልዕክት ያደርሳል፡፡ ጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛዋ በአጋጣሚ ያላስታወሰቻት፣ በመረጃ ደብተሩዋ ቀጠሮዋን ያዛነፈችባት እናት ብትኖር እንኳን በሞባይሏ በሚመጣላት የጽሑፍ መልዕክት እያንዳንዷ እናት በቀጠሮዋ ቀን ወደ ሕክምና እንድትሄድ የሚያስታውስ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ 
ባህላዊ አምቡላንስ፣ ነፍሰጡር እናቶች የሚወያዩበት “የእናቶች የብርሃን ቀን” እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በንሥሐ አባትነት ለያዙዋቸው ነፍሰጡር እናቶች ኃላፊነት መውሰድ በወረዳዋ ከወሊድ ጋር የተያያዘ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ ብሎም ጠቅላላ የጤና ሽፋኑን 87 በመቶ ለማድረስ አስችሏል፡፡ 
በትግራይ ክልል የሚገኙት 52 ወረዳዎች መከላከልን መሠረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ለመተግበር የሚጠቀሟቸው አዳዲስ ተሞክሮዎች በትግራይ ክልል በጤናው ዘርፍ ለመጣው አጠቃላይ መሻሻል መሠረት መሆናቸው በሰማዕታት አዳራሽ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ተገልጿል፡፡ ክልሎችም ከክልሉ መልካም ተሞክሮዎችን በመቅሰም የእናቶች ሞትን እንዲቀንሱ ብሎም አጠቃላይ የጤናውን ዘርፍ እንዲያሻሽሉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
via:

No comments:

Post a Comment