ለፓትትሪያርክነት ይታጫሉ
ተብለው የተጠበቁ ሊቃነጳጳሳት አልተካተቱም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ÷ በፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ተለይተውና ተጣርተው በሚቀርቡለት አምስት ዕጩ
ፓትርያሪኮች ላይ ዛሬ መወያየት ይጀምራል፡፡ ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ በሀገር ውስጥና በውጭ የተመደቡ የቅዱስ ሲኖዶስ
አባላት የሚገኙ ሲኾን አስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው የምርጫ መሪ ዕቅድ መሠረት፣ ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ ያገኙ አምስት ዕጩ
ፓትርያሪኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝቡ ይፋ የሚደረጉበት ውሳኔ የሚተላለፍበት ይኾናል፡፡
የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና
ምእመናን የተገኙትን ጥቆማዎች እንደ ግብአት በመያዝና በፓትርያሪክ ምርጫ ሕጉ የሰፈረውን ድንጋጌ በመጠቀም እንደለያቸው
የተነገሩትን ዕጩ ፓትርያሪኮች ዝርዝር ለቅ/ሲኖዶሱ የሚያስረክበው በዛሬው ዕለት እንደኾነም ታውቋል፡፡ ኮሚቴው የዕጩዎቹን
ዝርዝር ለቅ/ሲኖዶሱ ከማቅረቡ ቀደም ብሎ የወጡ መረጃዎች በዕጩ ፓትርያሪክነት የተመረጡት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት÷ በኢየሩሳሌም
የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ የባሌ
ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ
አቡነ ሕዝቅኤል እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ናቸው፡፡
በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ ለፓትርያርክነት ይበቃሉ ተብለው
ከታሰቡት ሊቃነ ጳጳሳት÷ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ መካከል
የተወሰኑት አለመካተታቸው የምርጫውን ሂደት የሚከታተሉ አካላትን አነጋግሯል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ የሚጠበቁት አባቶች
በዝርዝሩ ላለመካተታቸው በምርጫው ዙሪያ ያሳስበናል የሚሉትን የቡድን እንቅስቃሴዎች በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
No comments:
Post a Comment