Monday, February 4, 2013

የሚድሮክ ልዑክ ለአባዱላ ያቀረቡት ጥያቄ

የአላሙዲ ድርጅቶችን የግብር እዳ ማህደሮች ዝርፊያ ድራማ
alamudi and abadula
በወቅቱ የተላለፈውን ውሳኔና የውሳኔውን ትግበራ በቅርበት የሚያውቁ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንዳሉት የሚድሮክ ሃላፊዎች አባዱላ ቢሮ በመሄድ ስም በመጥቀስ የተወሰኑ የክልሉ ቢሮ ሃላፊዎች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ጠይቀዋል። ምንጮቹ እንደሚሉት በሙስና ሰበብ በእስር ላይ የሚገኙትን የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ቀዳሚው ተጠቃሽ ናቸው።
የሚድሮክ ስምና የባለሃብቱ ስም በሚዲያ እንዲጎድፍ አድርገዋል ያሏቸውን ክልሉን ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው እንዲያነሱላቸው የጠየቁት የሚድሮክ ሃላፊዎች አባዱላ በሰጡት መልስ ተበሳጭተው ነበር። አባዱላ ግብር መክፈል ግዴታ እንደሆነ፣ ይህ አቋም በካቢኔ ታምኖበት እንዲተገበር ከውሳኔ ላይ የተደረሰበት መሆኑንና ባለስልጣኖችን የመሾምና የማንሳት ጉዳይ የሚድሮክ ሳይሆን የክልሉ ስራ መሆኑንን ገልጸው የሚድሮክ ሰዎችን እንዳሰናበቱ ምንጮቹ አስታውቀዋል።
በኦህዴድ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው አባዱላ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነታቸው የተነሱበት ዋና ምክንያት በሼኽ መሐመድ ላይ ባላቸው አቋም የተነሳ እንደሆነ የሚጠቁሙት ክፍሎች፣ አባዱላ ለሚድሮክ ሰዎች “የሚያጥወለውል” መልስ ሲመልሱ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተጠየቁት መካከል የተወሰኑት ባለሥልጣኖች በተገኙበት መሆኑ የጀመሩትን የግብር ማስከፈል ስራ አጠናክረው እንዲሰሩ ሞራል ሆኗቸው እንደነበር ይናገራሉ።

ጨለለቅ አልሳም ታወር (ፎቶ:የሰነድ ምዝገባ)
በዚሁ መሰረት አላሙዲ በኢንቨስትመንት ስም አጥረው ባኖሩዋቸው ሰፋፊ መሬቶች፣ በኤልፎራ ዶሮ ርቢ፣ በኤልፎራ ቄራ፣ በተለያዩ የከብት ማደለቢያ ኳራንቲዎችና በመልጌ ወንዶ፣ የሆራ ሃይቅ ወዘተ በወቅቱ ለክልሉ ገቢ ያላደረጉት የአስራ አንድ ዓመት የመሬት ግብር እንዲከፍሉ የሂሳብ ሰነድ ይዘጋጃል። ከሌሎች በክልሉ የመሬት ግብር ካልከፈሉ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ጋር ባንድነት ተመርምሮ የተዘጋጀው የግብር ተመን የሂሳብ ሰነድ ሜክሲኮ ጨለለቅ አልሳም (ታወር) ህንጻ በነበረው የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዘንድ ለውሳኔ እንደደረሱ ያልተጠበቀ ወሬ ተሰማ።
በወቅቱ የገቢዎች ቢሮ ህግ ክፍል ይሰሩ ከነበሩት መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ በመጠየቅ እንዳሉት “የሃላፊው ቢሮ ሳይሰበር በሩ ተከፍቶ ሰነዶቹ ተዘርፈዋል” ጉዳዩን ህግ ዘንድ እንዴት እንደተያዘ ሲከታተሉ ከነበሩት መካከል አንዱ ለጎልጉል እንደተናገሩት “የበርካታ ባለሃብቶችና ድርጅቶች የሂሳብ ምርመራ ሰነዶች አንድ ላይ ከተቀመጡበት የቢሮው ሃላፊ ውስጥ ተመርጦ የተዘረፈው የሼኽ መሀመድ ንብረት የሆኑት ድርጅቶች የሂሳብ ማህደሮች ብቻ መሆናቸው ነው፡፡”
“ቢሮው በቁልፍ ተከፍቶ ስለመዘረፉ ከበቂ በላይ ምልክቶች ነበሩ” የሚሉት እነዚህ ክፍሎች ሃላፊው ቢሯቸውን ቆልፈው ከወጡ በኋላ ዝርፊያው ሲከናወን ቁልፍ ከየት ተገኝቶ ቢሮው ተከፈተ? የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር። የመጠባበቂያ ቁልፍ ያለው የህንጻው ባለቤት በሆነው አልሳም ኢንተርናሽናል ዘንድ ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት እነዚህ ክፍሎች፣ “ተራ ማምታቻ ተፈጽሞ ስናይ አፈርን” ሲሉ የሚገልጹት ጉዳይም አላቸው።
የቢሮው የኮሪደር መስታወት ሆን ተብሎ እንዲሰበር መደረጉን በአግራሞት ሲገልጹ “የተሰበረው የቢሮው የኮሪዶር ዳር መስታወት ከፍ ያለና እንኳን በር ሰባሪ ማጅራት መቺዎችን የሚጠባ ህጻን የማያስገባ ነው፡፡” ሃፍረት የተሞላበትን የዝርፊያ ድራማ ማመን እያቃታቸው የሚገልጹት ለጉዳዩ የቀረቡት ክፍሎች ምርመራው የተያዘው በፌዴራል፣ በክልሉና በልደታ ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ ቢሆንም አንድ ርምጃ ሳይራመድ ተድበስብሶ መቅረቱን ይገልጻሉ።
ለእነዚሁ ክፍሎች ቅርብ የሆኑ የክልሉ ፖሊስ አንድ ሃላፊ የዝርፊያው ድራማ “የመጠባበቂያ ቁልፉን ማግኘት የሚችለው ማን ነው?” በሚል የተጀመረው ምርመራ ቀዳሚ ተጠርጣሪዎችን ቢለይም ጉዳዩ እንዲድበሰበስ በመደረጉ ዝርፊያውን ያካሄዱት ክፍሎች ሳይጋለጡ ቀርተዋል።
ባለሃብቱን በቀጥታ ተጠያቂ ያላደረጉት ክፍሎች፣ በሳቸው ድርጅት ስም እንዲህ ያለ ዝርፊያ ሲከናወን ጉዳዩ እንዲጣራ የወከሉዋቸው “ትልልቅ ሰዎች” ራሳቸው ከፖሊስ ጋር ሊሰሩ ይገባቸው ነበር ሲሉ ተናግረዋል። እንዲህ ያለ ተራና የወረደ የመንደር ዱርዬ ተግባር ሲፈጸም ዝም ማለት ከተባባሪነት ሊያሸሽ እንደማይችል የትዝብት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በባለሃብቱ ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ማንነት ያሳያል የሚል እምነት እንዳላቸው በመጠቆም አስተያየታቸውን የሰጡት የኦህዴድ ሰዎች ድርጅታቸው ኦህዴድ ይህንን ጉዳይ በቸልታ መመልክቱ ሌላው አሳፋሪ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
የተዘረፉት የሂሳብ ማህደሮች ቅጂ በሚገባ ተቀምጦ ስለነበር ወደ አፈጻጸሙ ለመግባት ምንም እክል እንዳላጋጠማቸው በወቅቱ ስራው አካባቢ የነበሩ ለጎልጉል አስረድተዋል። ዝርፊያው እንዲከናወን ትልቁን ሚና ተጫውቷል የሚባል አንድ “ልማታዊ  ጋዜጠኛ” ስለመኖሩ በቂ መረጃ ስላለ ሁኔታዎች ሲመቻቹ የህግ ጥያቄ እንደሚነሳ አመላክተዋል።

No comments:

Post a Comment