Wednesday, November 13, 2013

ዛሬም ከሳዑዲ አረቢያ የጣር ድምጽ እየተሰማ ነው

(ዘ-ሐበሻ) በሳዑዲ አረቢያ ከሪያድ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትርሃም በሚባል ቦታ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራችሁ ትላካላችሁ በሚል ካለ ምግብ፣ ካለመኝታ፣ ካለ መታጠቢያ እየተሰቃዩ መሆኑን ኢትዮጵያውያኑ ለዘ-ሐበሻ ተናግረዋል። ትናንት በመካ ከተማ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራችን ላኩን በሚል መንገድ በመዝጋት ሲጮሁ እንደነበር ያስታወቁት የዘ-ሐበሻ የሳዑዲ ዘጋቢዎች ፖሊሶች ኢትዮጵያውያንኑን “ሙጂሪም” (ነብስ አጥፊ) በሚል እንደሚደበድቧቸው ተናግረዋል።


ከሪያድ ከተማ በስልክ በደረሰን መረጃ መሠረት ወደ ሃገራችሁ ትላካላችሁ ከተባሉትና ስትርሃም በሚባል ቦታ ከተቀመጡት ውስጥ ነብሰ ጡር ሴት ካለምንም የህክምና እርዳታ መውለዷን ገልጸዋል። የሳዑዲ አረቢያ የቧንቧ ውሃ እንደማይጠጣ እየታወቀ ወደ ሃገራችሁ ትላካላችሁ የተባሉ ወገኖች ንጹህ ውሃ እንደማይቀርብላቸው ገልጸው ከኢትዮጵያ ኢምባሲ አንዳችም ሰው መጥቶ እንዳልጎበኛቸው ተናግረዋል።
ለዘ-ሐበሻ በስልክ አስተያየቷን የሰጠችው ሰናይት የተባለች ወጣት “እኔ ህጋዊ ወረቀት ኖሮኝ እየሰራሁ ቢሆንም በወገኖቼ ላይ የሚደርሰውን በደል የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ስደውል በተለይ ሲራክ ታደሰ የሚባል ኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ የሚሰራ ሰው ማን ኑ አላቸው፤ አርፈው አይቀመጡም እንዴ? እኛ ከሃብታም ጋር መጣላት አንችልም እንዳላት” ገልጻለች። ወጣቷ ፓስፖርት ለማሳደስ የሚሄዱ ወገኖችን ይህ ሰው እንደሚያሰቃይ፣ ለፈለገው ሰው ፓስፖርት አድሶ ላልፈለገው እንደሚከለክል ገልጻ የሳዑዲ መንግስት ሰጥቶት የነበረው የሥራ ፈቃድ ማደስ ዕድል ለብዙ ኢትዮጵያውያን ያመለጠው በኢትዮጵያ ኢምባሲ የፓስፖርት ክልከላና አለማደስ ምክንያት ነው ብላለች። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢምባሲ ስልክ ደውሉ ብሎ ለፕሮፓጋንዳ ቢጠቀምም ኢምባሲው ውስጥ ስልክ እንደማይነሳ፤ ከተነሳም የሚስተናገዱ ሰዎች እየተመረጡ ነው የሚሉ አስተያየቶች ደርሰውናል።
ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስም አብዛኞቹ የጠቆሙት ‘በተለያዩ ሃገራት ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ጥሩ ነው። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች መካከል በተለይ በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ በ100ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በ እስር ቤት ካለፍርድ ከዓመት በላይ ታሰረው ይገኛሉ። የነዚህን ጉዳይ በተለያዩ ሃገራት በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ፍትህ እንዲያገኙ ህዝብ ይጠይቅልን” የሚል ነው
ተጨማሪ መረጃዎች እንደመጡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዘገባዎችን እናቀርባለን።

No comments:

Post a Comment